
Saturday, 18 January 2025 22:06
Written by Administrator

ከአገራዊ የምክክር ሂደቱ ራሱን ማግለሉን ያስታወቀው የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ፤ “አገራዊ የምክክር ሂደቱ መደበኛ ሕዝባዊ ውይይት እየመሰለ ሂዷል” ሲል ተቸ።
ባለፈው ረቡዕ ጥር 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ፓርቲው ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንደገለፀው፤ “አካታች” እና “ገለልተኛ” ምክክር የሚካሄድበት ዕድል ስለሌለ ራሱን ከምክክር ሂደቱ አግልሏል። አክሎም፣ የምክክር ኮሚሽኑ “ከገዢው ፓርቲ ተጽዕኖ” ውጪ መሆን አለመቻሉን ጠቅሷል።
የምክክር ሂደቱ የሃሳብ ልዩነት ያላቸውንና “የግጭቶቹ ተዋናይ የሆኑትን አካላት ያላሳተፈ”፣ “ጦርነቶች እንዲቆሙ በማድረግ አስቻይ ሁኔታን ያልፈጠረ” መሆኑን ፓርቲው አመልክቷል። ይህም ሁኔታ ከአጀንዳ ልየታ ሂደት ጀምሮ ሲስተዋል መቆየቱን ጠቁሟል።
ምክክሩ “መደበኛ ሕዝባዊ ውይይት እየመሰለ ሄዷል” ያለው ፓርቲው፣ አሁን ኮሚሽኑ እየተከተለ ባለው መንገድ “የተወሳሰቡ” ያላቸው የአገሪቱ ችግሮች እንደማይፈቱ በጽኑ እንደሚያምንም ነው ያስረዳው። ፓርቲው ከኮሚሽኑ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመ ወዲህ፣ በመንግስት አካላት በተለይም የክልሉ መንግስት ከዚያ በፊት ከነበረው “በከፋ ሁኔታ” ዕመቃ እንደተፈጸመበት አብራርቷል።
በዚህ ምክክር መሳተፍ ችግሮችን የሚፈታ ውጤት ያመጣል ብሎ እንደማይጠብቅም ፓርቲው አመልክቷል። የምክክር ሂደቱ አሁን ባለው ቁመና “ከገዢው ፓርቲ ፍላጎት ውጪ ለሌሎች አስቻይ ሁኔታ መፍጠር የማይችል፣ አካታችና ሃቀኛ አገራዊ ምክክር በማድረግ ውስብስብ ችግሮቻችን በምክክር ለመፍታት የሚያስችል አቅምና ቁርጠኝነት የሌለው መሆኑን” እንዳረጋገጠ በደብዳቤው ላይ ጨምሮ አትቷል።
ኮሚሽኑ በነሃሴ ወር 2016 ዓ.ም. ባካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት፣ ከፓርቲው ከታገዱ ግለሰቦች ጋር በመተባበር የፓርቲው ተወካዮች ከመድረኩ ተገድደው እንዲወጡ “አድርጓል” በማለትም ፓርቲው ከስሷል። አያይዞም፣ ፓርቲው “ይህም የተደረገው በዲሲፕሊን ከተሰናበቱ የፓርቲውን ሰዎች ቀድሞውኑ በማስገባትና ከእነርሱ ጋር በማበር ነው” ያለ ሲሆን፣ ቦርዱ ችግሩን ለማስተካከል ከፓርቲው አመራር ጋር ተወያይቶ ከስምምነት ላይ የደረሰ ቢሆንም፣ በተስማማው መሰረት ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዱን ነው የጠቀሰው።