

የሥነ ተዋልዶ ጤና መረጃ አገልግሎት ፕሮጀክት ይፋ ሲደረግ በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር፣ የጤና ሚኒስትር ደኤታ፣ የአይፖስ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተገኝተዋል
ማኅበራዊ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የተያዘለት የሥነ ተዋልዶ ጤና ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
ቀን: January 19, 2025
በኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተከሰቱ ጦርነቶችና ግጭቶች ምክንያት እየተስተጓጎለ የመጣውን የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት መልሶ ለማጠናከር ያስችላል የተባለ የ1.28 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ፡፡
ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሴቶችን በቀጥታ እንዲሁም ከአምስት ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለውን የሥነ ተዋልዶ ጤና መረጃና አገልግሎት ፕሮጀክት በአማራ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡
በአምስት ክልሎች ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሥነ ተዋልዶ ጤና መረጃና አገልግሎት ተደራሽነት ለማጠናከር የታለመው ፕሮጀክት፣ ለሰባት ዓመታት የሚተገበርም ይሆናል፡፡
ባገባደድነው ሳምንት በአይፓስ ኢትዮጵያ፣ በጤና ሚኒስቴርና የገንዘብ ድጋፉን ባደረገው የካናዳ መንግስት ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት ሴቶች፣ ልጃገረዶችና ማኅበረሰቡ የራሱን ጤና ለመጠበቅ በመረጃና በግንዛቤ ላይ ተመሥርቶ ውሳኔ እንዲያሳልፍ የሚያስችልም ነው ተብሏል፡፡
የአይፓስ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ደመቀ ደስታ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ፕሮጀክቱ አስፈላጊ ሀብት ከማቅረብ ባለፈም ሴቶችና ልጃገረዶች የሥነ ተዋልዶ ጤና አጠባበቅና አገልግሎት ፍላጎታቸው ላይ ለመወያየት ደኅንነቱ የተጠበቀ ድባብ መፈጠርንም የሚያጠናክር ነው፡፡
በፕሮጀክቱ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ በፋብሪካዎችና በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሠሩ ሴቶች፣ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውና በገጠር የሚኖሩ ሴቶችን ጨምሮ የሥነ ተዋልዶ ጤና መረጃና አገልግሎት ይበልጥ የሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ይሆናሉም ብለዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግጭቶች፣ የእርስ በርስ ጦርነት፣ ድርቅ፣ ረሃብና ሌሎችም ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በርካታ ሴቶችንና ልጃገረዶችን ፆታን መሠረት ላደረገ ፆታዊ ጥቃት ይበልጥ ተጋላጭ ማድረጋቸውን በማስታወስም፣ ለእነዚህ አካላት የሚያስፈልጋቸውን የሥነ ተዋልዶ ጤና መረጃና አገልግሎት ማድረስ የፕሮጀክቱ አካል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የሥነ ተዋልዶ ጤና መረጃና አገልግሎት ላይ ያለመው ፕሮጀክት ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ እንዲተገበር ጤና ሚኒስቴር፣ የክልል ጤና ቢሮዎችና አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አብረው ከሚሠሩ ዋና ዋና ተቋማት ውስጥ ተጠቃሽ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ጆሽዋ ታቦህ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ 30 በመቶ ያህል ያልታቀደ እርግዝና እንደሚያጋጥም፣ ለዚህም ዝቅተኛ የወሊድ መቆጣጠሪያ አጠቃቀምና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽ አለመሆን ቀዳሚውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን፣ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃትም ላልተፈለገ እርግዝና ሁለተኛው ዋና ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ከአንድ አራተኛ ሴቶች በላይ አካላዊ ወይም ፆታዊ ጥቃት አስተናግደዋል፤›› ያሉት አምባሳደሩ፣ በጦርነትና በግጭቶች መካከል የሚኖሩ ፣ አካል ጉዳተኞች፣ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ እንዲሁም በፋብሪካዎች ውስጥ የሚሠሩ ሴቶች የፆታዊ ጥቃት ተጋላጭነታቸው ይጨምራል፣ እነዚህን በሥነ ተዋልዶ ጤና መረጃና አገልግሎት መድረስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ይፋ ሲሆን ንግግር ያደረጉት በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ ሕፃናትና አፍላ ወጣቶች ጤና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርያማዊት አስፋው (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ የእናቶችን፣ ሕፃናትንና አፍላ ወጣቶችን ጤና በማሻሻል ረገድ ጉልህ ውጤት ብታስመዘግብም የጤና ዘርፉን በሚፈለገው መጠን ተደራሽ ለማድረግ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
30 ኢትዮጵያውያን ሴቶች መቆጣጠር በሚቻል ምክንያት በየቀኑ እንደሚሞቱ፣ ከአምስት ዓመት በታች ካሉ 1,000 ሕፃናት 47 እንደሚሞቱ፣ በጤናው ዘርፍ በተሠሩ ሥራዎች ከአምስት ዓመት በታች የሚመዘገብ የሕፃናት ሞትን መቀነስ ቢቻልም፣ አሁንም መቆጣጠር በሚቻሉ በሽታዎች ምክንያት በየዓመቱ ከ100,000 በላይ ሕፃናት እንደሚሞቱም ተናግረዋል፡፡
በርካታ አፍላ ወጣቶች መሠረታዊ የሥነ ተዋልዶ ጤና ዕውቀት እንደሌላቸው፣ የሥነ ተዋልዶ ጤና መረጃና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግና ራሳቸውን ከጉዳት እንዲጠብቁ ክህሎት ማስጨበጥ እንደሚያስፈልግም መክረዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው፣ አዲስ የጸደቀው የጤና አዋጅም የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት የማግኘት መብትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡
