መግለጫው በተሠጠበት ወቅት

ዜና መነሻቸውን ከደቡብ አሜሪካ ያደረጉ አደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎች በቦሌ ኤርፖርት ጠንካራ ፍተሻ እንዲደረግባቸው…

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: January 19, 2025

መነሻቸውን በተለይ ከደቡብ አሜሪካ አድርገው በኢትዮጵያ በኩል በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የሚተላለፉ ዕፅ አዘዋዋሪዎች፣ በአካላቸው ውስጥ ይዘውት የሚንቀሳቀሱትን አደገኛ ዕፅ ለመያዝ ጠንካራ ፍተሻ የሚያደርግ ማሽን እንዲተከል ተጠየቀ፡፡

መቀመጫውን ሆንግ ኮንግ ያደረገውና ቮይስ ፎር ፕሪዝነርስ (Voice for Prisoners) የተሰኘውና አደገኛ ዕፅ በማዘዋወር ተይዘው እስር ቤት የሚገቡ ግለሰቦች ላይ የሚሠራው ዓለም አቀፍ ተቋም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትራንዚት የሚያደርጉ ተጓዦች ላይ የሚደረገው ፍተሻ ዝቅተኛ ስለሆነ፣ ከደቡብ አሜሪካ ተነስተው ቦሌ ኤርፖርትን የሚያቋርጡ ተጓዞች ላይ ጠንካራ ፍተሻ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡ በርካታ የደቡብ አሜሪካ ተጓዞች ወደ እስያ ለመጓዝ የቦሌ ኤርፖርትን እንደ አማራጭ ይጠቀማሉ ብሏል፡፡

ጆን ዋትርስፑን የተባሉ የድርጅቱ ኃላፊ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲያደርጉበት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በአመዛኙ ሴት ተጓዦች በሰውነት ክፍላቸው አደንዛዥ ዕፅ ይዘው እንዲጓዙ እየተደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ ወደ አንድ ኪሎ ግራም የሚመዝን አደገኛ ዕፅ እንዲያዘዋውሩ ተደርገው ሆንግኮንግ በደረሱበት ወቅት፣ በፖሊስ ተይዘው እስር ቤት የገቡ በርካታ አፍሪካውያን ሴቶች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርትን አቋርጠው ወደ ሆንግ ኮንግና ሌሎች የሚደረጉ ዝውውሮች እየቀነሱ ቢሆንም፣ አሁንም የቁጥሩ መጨመር አስፋሪ ነው ብለዋል፡፡

የአደገኛ ዕፅ ዝውውሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ቦሌ ኤርፖርትን እንደ ማምለጫ ከሚጠቀሙበት በርካታዎቹ ከደቡብ አሜሪካ የሚነሱ የናይጄሪያ አዘዋዋሪዎች ናቸው ብለዋል፡፡

በቅርቡ የ32 ዓመት ደቡብ አፍሪካዊት 600 ግራም ኮኬይን፣ የ32 ዓመት ሴት ዚንባቡዌያዊት 1.2 ኪሎ ግራም ኮኬይን፣ እንዲሁም ከታንዛኒያና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሌሎች ሴቶች ውስብስብ በሆነ መንገድ ዕፅ እንዲያዘዋውሩ ተደርገው ሆንግ ኮንግ መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡

በቦሌ ኤርፖርት ቢያንስ የሠለጠኑ ውሾችን በማሰማራት ችግሩን በተወሰነ ደረጃ መቀነስ ይቻላል የሚሉት ጆን ዎተርስፑን፣ አዘዋዋሪዎቹ አደገኛ ዕፅ ወደ ሰውነታቸው እንዲያገስገቡ ከተደረገ በኋላ፣ ለቀናት ምግብ እንዳይበሉ እንደሚያደርጉና ኢሰብዓዊ የሆነ ድርጊት እየተፈጸመባቸው ተገደው እንደሚሰማሩ ተናግረዋል፡፡

የእፅ ዝውውሩን በማስቆም በቦሌ አርፖርት ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮችም ትብብር በጋራ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ቁጥጥሩ ካልተጠናከረ በዓለም ዙሪያ የዕፅ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የከፋ አደጋ ሊያስከትል ይችላል ብለዋል፡፡

በተለያዩ ሪፖርቶች የአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎች የቦሌ ኤርፖርትን እንደሚጠቀሙና ተላላፊ መንገደኞች የሚፈተሹበት የተለየ አሠራር ያስፈልጋል የሚል አስተያየት ሲሰጥ ይደመጣል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአደንዛዥ ዕፅና የወንጀል ጉዳዮች ቢሮ (UNODC) ሪፖርት እንደሚያሳየው የቦሌ ኤርፖርት ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ፣ ከደቡብ አሜሪካና ከእስያ የዕፅ ዋነኛ መተላለፊያ መስመር ነው፡፡ በተቋሙ የተሠራው እ.ኤ.አ. የ2023 የዓለም አደንዣዥ ዕፅ ዝውውር ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በብራዚል ከተያዙ 165 ኮኬይን አዘዋዋሪዎች መካከል 64 ያህሉ መዳረሻቸው አዲስ አበባ ነበር፡፡