
January 19, 2025

የጋራ ጠላትን በአንድ የተባበረ ክንድ ለመዋጋት፣ ቀጣናዊ ጠንካራ የጋራ ኃይል ለመገንባት፣ የጋራ ኢኮኖሚና የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ ግጭቶችን፣ ድንበር ዘለል የሽብር እንቅስቃሴና አዋኪ ኃይልን በኅብረት ለመከላከል በሚል የሁለትዮሽና የሦስትዮሽ ወይም ቁጥራቸው የበዙ የአገሮች ወደ አንድ በመምጣት የወዳጅነት ስምምነት (Pact) ፈጥረው የተሳካ ሥራን ሲያናውኑ የተስተዋሉባቸው ክስተቶች ብዙ ናቸው፡፡
ለአብነት ያህል መረጃዎች እንደሚያሳዩት ውጤታማ ከሚባሉ የመሪዎች ስምምነት መካከል እ.ኤ.አ. በ2015 በሩሲያ፣ በቤላሩስና በካዛኪስታን መሪዎች መካከል የተመሠረተው ድኅረ ሶቭዬት ኅብረት የፖለቲካና ኢኮኖሚክ ትብብር፣ እ.ኤ.አ. በ2021 በቱርኪዬ፣ በአዘርባጃንና በጆርጂያ መሪዎች መካከል በቀጣናዊ ሰላም፣ በኢነርጂና በንግድ ትብብር ለጋራ ኢኮኖሚዊ ልማት በሚል የተካሄደው ስምምነት፣ እ.ኤ.አ. 2021 በፈረንሣይ፣ ጀርመንና እንግሊዝ መሪዎች መካከል የቻይናን የበረታ ተፅዕኖ ለመግታት፣ እንዲሁም በወታደራዊና በቴክኖሎጂ ዘርፍ በጋራ ለመሥራት የፈጠሩት ስምምነት፣ እ.ኤ.አ. 2021 የብራዚል የአርጀንቲናና የፓራጓይ መሪዎች ያደረጉት በኢነርጂ ክፍፍል ላይ የተመሠረተ ስምምነት፣ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ በርካታ አገሮች አባል የሆኑበትና የምዕራባውያን የራስ ሕመም የሆነውን ብሪክስ የተሰኘ ድርጅት ለመመሥረት ስምምነት በማካሄድ ለመጀመረያ ጊዜ የብራዚል፣ የቻይና፣ ይህንድና ሩሲያ የመሪዎች ስምምነት በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ስምምነቶች በአፍሪካ አኅጉር በተለይም የሰላም ዕጦት፣ ሽብርተኝነት፣ ድርቅ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የውስጥ ሽኩቻ፣ እንዲሁም በርካታ ኃያላን አገሮች በተለየ መንገድ እንዲሠለፉ ከማድረግ ባለፈ ዕይታቸው በማይለየው ምሥራቃዊ ቀጣና የአካባቢው መሪዎች ለጋራ ጉዳይ የሚፈጥሩት ትብብር እምብዛም አይታይም፡፡ የተፈጠረውም ኅብረት ይህ ነው የሚባል አዎንታዊ ውጤት ያላመጣና የእርስ በርስ ባላንጣነትን የፈጠረ ስለመሆናቸው ብዙ ተነግሮለታል፡፡
የፖለቲካና የወታደራዊ ጉዳይ ተንታኞች ሲናገሩና ሲጽፉበት እንደሚስተዋለው እርስ በርስ የመጠፋፋት ዓላማን የያዙ ከሚመስሉ ወቅታዊና በስሜት ተለዋዋጭ ከሆኑ ትብብሮች ያለፈ፣ ለቀጣናው የተለየ ፋይዳ ሲያመጡ አልተስተዋልም፡፡ ቀውስ በበዛበት፣ የድህነትና የአለመረጋጋት ተምሳሌት በሆነ የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ የሚስተዋሉ የመሪዎች ትብብር፣ ለአብነትም እ.ኤ.አ. በ2018 አፍሪካ ቀንድን ሊያተራምስ ይችላል በሚል ሥጋት ደቅኖ የነበረው የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ከወቅቱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ጋር ያደረጉት ስምምነት ውጤት ምንም ዓይነት ፋይዳ ሳይመዘገብበት ደብዛው የውኃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ከዚያመ በኋላ ሦስቱም መሪዎች በስምምነታቸው ማግሥት እርስ በርስ በአሉታዊ መንገድ የመፈላለግ አባዜ ውስጥ መግባታቸው ነው ሲነገር የነበረው፡፡
ይህ የቀደመ ስምምነት ውጤት እምጥ ይግባ ስምጥ ሳይታወቅ እ.ኤ.አ. መስከረም 5 ቀን 2018 ለነበረው የአስመራው የሦስትዮሽ የመሪዎች ስምምነት አውራ የነበሩት የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ ሌላ የትብብር አዙሪት ውስጥ ገብተው እ.ኤ.አ. 2024 የግብፅና የሶማሊያን መሪዎች በመያዝ በተመሳሳይ በአስመራ ከተማ አዲስ የሦስትዮሽ የአጋርነት ስምምነት በመፍጠር በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሌላ የፖለቲካ ትኩሳት ግለትና የኃይል ፍጥጫ ፈጥረዋል፡፡
ይህ ስምምነት ለጋራ ቀጣናዊ ጉዳይ ያልተቋቋመ ከመሆኑም በላይ፣ በዚህ ሁሉ ሒደት የትኩረትና የስበት ኃይል በበዛባት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሌላ ራስ ምታት መጨመር ያለመ ስምምነት ነው በሚል በብዙዎች የተነገረለት ጉዳይ ነው፡፡ በተለያዩ መለኪያዎች ሒደቱም ይሁን ውጤቱ በበርካታ እንቅፋቶች ውስጥ አልፎ መጨረሻው፣ በሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የበረታ የዲፕሎማሲ ጫና ወደኋላ የተገፋውና በኢትዮጵያ መንግሥትና ከራስ ገዟ ሶማሌላንድ ጋር የተደረገውን የመግባቢያ ስምምነት አንድ ማስረጃ ማንሳት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ትልም ለማክሸፍ ያለመና በተለያዩ ፖለቲካዊ ሁነቶች ለሚያልፈው ቀጣና፣ ‹‹ከዚያ ማዶ ፀብ አድርሰኝ›› እንደሚባለው ከቀጣናው ውጪ ያለችውን ግብፅ በመጋበዝ ሌላ ትርምስ የመፍጠር ሐሳብ የሰነቀ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡
ኢትዮጵያ ባልተረጋጋ የውስጥ ፖለቲካና የቤት ሥራ ጋር ተዳምሮ ጠንካራ አገረ መንግሥት ለመገንባት ከምታደርገው ግብግብ ባልተናነሰ፣ ለሶማሊያ መንግሥትና ሕዝብ የሰላም ዘብ ለመሆን የሰላም አስከባሪ ወታድሮችን በመላክና በማሰማራት፣ ከማንኛውም የጎረቤትም ሆነ ሌላ አገር የተሻለ ድጋፍ ያደረገችና ልጆቿን የገበረች አገር ናት፡፡ ይሁን እንጂ ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ በቀጣናው በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ከመጣው ሕዝቧ ጋር ለሚያስፈልጋት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የወታደራዊ ቁመና የሚጨምረውን የባህር በር ለማግኘት ያሏትን አማራጮች ለማስፋት መንቀሳቀስ ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ለዚህ ፍላጎት መሳካት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የቀድሞው የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ እ.ኤ.አ. ጥር 2024 የፈረሙት ስምምነት ሶማሊያን ማስቆጣቱ ተገቢነት እንዳለው ቢነገርም፣ የግብፅ ለሶማሊያ አለሁልሽ ብሎ ማንዣበብ መልስ የሚሻው ፀብ አጫሪነትና ግብዝነት መሆኑን በርካቶች ሲነጋገሩበት ነበር፡፡
ከወራት በፊት መቀመጫውን በአሜሪካ ዋሽንግተን ያደረገውና የዓለም አቀፍ ፖለቲካና የደኅንነት ጉዳዮች ጹሑፎችን ይዞ የሚወጣው አትላንቲክ ካውንስል የተሰኘ ድረ ገጽ ባሰፈረው ጹሑፍ፣ ግብፅ ከዓባይ ውኃ ጋር በተገናኘ ጥቅሜን ትጎዳለች የምትላትን ኢትዮጵያ ለማወክ የማትቆፍረው ጉድጓድ እንደሌለ ያብራራል፡፡ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ሰበብ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግብፅ እጇን ካስገባችባቸው ዋነኛ ከሚባሉት መካከል ከሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፍጠር፣ የጦር መሣሪያዎችን የጫኑ የግብፅ የጦር አውሮፕላኖችን ወደ ሶማሊያ ማስገባት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ማዕከላዊ መንግሥቱን የሚገዳደሩ ኃይሎችን በህቡዕ መደገፍና በሶማሊያ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ወታደሮቿን የማስጠጋት እንቅስቃሴዎችን ዘርዝሯል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሶማሊያ ከግብፅ ጋር በፈጠረችው ወታደራዊ ትብብር የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያን ለቆ እንዲወጣና በምትኩ የግብፅ ጦር የሰላም ማስከበር ቦታውን እንዲሸፍን ለማድረግ፣ የካይሮ ባለሥልጣናት ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርጉ ሰነባብተዋል፡፡
ለአንድ ዓመት ያህል በበረታ የዲፕሎማሲጫና ውስጥ የነበሩት ኢትዮጵያና ሶማሊያ ከበርካታ የቃላት ምልልስና መካረር በኋላ በቱርኪዬ ፕሬዚዳንት ረጂፕ ጠይብ ኤርዶሃን አሸማጋይነት በአንካራ ስምምነት አድርገዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው ሉዓላዊነቴን የጣሰ ነው ያለችውን የመግባቢያ ስምምነት ካልቀደደች በስተቀር ድርድር አይኖርም ስትል የቆየችው ሶማሊያ፣ በአንካራው ስምምነት መሠረት ሁለቱ አገሮች ቀድሞ ወደ ነበሩበት ጤነኛ በሚባል ዲፕሎማሲያዊ መንፈስ በጋራ ለመሥራት ስምምነት መፍጠራቸው ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ በነበራት የመግባቢያ ስምምነት ልታገኝ የምትችለውን የባህር በር፣ በሶማሊያ የተሰማራውን የኅብረቱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ (ATMIS)ን በሚተካው የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ድጋፍና ማረጋጋት ተልዕኮ (African Union Support and Stabilization Mission for Somalia – AUSSOM) የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ መካተት ጉዳይ ይህ ነው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡
በዚህ ዓይነቱ የዲፕሎማሲያዊ ውጣ ውረድና የፖለቲካ ጫና፣ እንዲሁም ግብፅና ሶማሊያ በፈጠሩት ጥምረት ሳቢያ እ.ኤ.አ. በጥር 2024 ከራስ ገዟ ሶማሌላንድ ጋር ስለተፈረመው የባህር በር ስምምነት፣ ከኢትዮጵያም ሆነ ከሶማሌላንድ ባልሥልጣናት በኩል የተሰማ ግልጽ ነገር የለም፡፡ አንዳንድ የዘርፉ ምሁራንና ተንታኞች ከሶማሌላንድ ጋር የተፈረመው ስምምነት ያለቀለትና የሞተ ጉዳይ ነው ቢሉም፣ በሌላ በኩል ከጉዳዩ ባለቤቶች የሚሰማው ደግሞ ተቃራኒውን ነው፡፡
መቀመጫቸውን በእንግሊዝ ለንደን ያደረጉት የሶማሌላንድ ዋዳኒ ፓርቲ አስተባባሪና የምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ሻርማኬ ዓሊ እንደሚሉት፣ አዲሱ የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንትና የዋዳኒ ፓርቲ መሪ አብዲራህማን መሐመድ አብዱላሂ (ኢሮ) አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያደረገችውን ስምምነት ሰዎች እንደሚሉት የሞተና ያለቀለት ሳይሆን በይደር የተያዘ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ወደ ሥልጣን ከመጡ አጭር ጊዜ በመሆኑ በቀጣይ ሊታይ እንደሚችል ታሰቦ የተቀመጠ ጉዳይ ነውም ይላሉ፡፡ አክለውም ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ከየትኛውም ወዳጅ በላይ የቀረበ መሆኑ፣ በቀጣይ ሰፋ ባሉ ትብበሮች የመሥራት ፍላጎት በአዲሱ ፕሬዚዳንት ዕቅድ ውስጥ ስለመኖሩ ያብራራሉ፡፡
የአንካራውን ስምምነት ተከትሎ የሶማሊያና የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሞቃዲሾና በአዲስ አበባ ተገናኝተው የመከሩ ሲሆን፣ በመሪዎች ደረጃ ጥር 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ከፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ ጋር በአዲስ አበባ ተገናኝተው የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ውጤታማ ውይይቶች ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ በተለያዩ ጫናዎች ውስጥ ለነበረችው ኢትዮጵያ የሶማሌላንድ ስምምነት የሞተ ጉዳይ ነው ከተባለ፣ በአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ልታገኘው የምትችለው ጉዳይ ምን ሊሆን ይችላል? ሶማሊያ ለኢትዮጵያ የባህር በር እንድትሰጥ ምን አስገዳጅ ነገርስ ይኖራል? በአንካራው ስምምነት ማንስ አሸነፈ? ሲል ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፖለቲካ አጥኝና ተንታኝ መሐመድ አብዲ አህመድ፣ ስምምነቱ ለዓመታት ያህል ከቀጣናው ፖለቲካ ተገልላ የነበረችውን ኢትዮጵያ ወደ ጨዋታው የመለሰ ነው ይላሉ፡፡
ግብፅን፣ ኤርትራንና ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በቻለችው መጠን ከጎኗ በማሠለፍ ሶማሊያ ስታደርጋቸው የነበሩ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ኢትዮጵያን ከቀጣናዊ ጉዳዮች አግልለዋት የነበረ ቢሆንም፣ የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያን ወደ ጨዋታው ሜዳ እንድትመለስ ማድረጉን ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያን ከሶማሊያ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንድትጀምር ማድረግ አሸናፊ ያደረጋት እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የፈረመችው ስምምነት ተግባራዊ እንዳይሆን ሶማሊያ ኢትዮጵያን ስታስጨንቅበት (Hard Time for Ethiopia) የነበረውን ሒደት እንዲቆም በማድረግ፣ ሶማሊያን አሸናፊ ያደረገ ስምምነት ነውም ይላሉ፡፡
የፖለቲካ አጥኝውና ተንታኙ አክለውም ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት ላይ ቆማ ቢሆን ኖሮ፣ የሶማሌላንድ አዲሱ ፕሬዚዳንት በቀደመው ስምምነት ላይ ደስተኛ ባለመሆናቸውና ስምምነቱ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነቱ አጠያያቂ የነበረ በመሆኑ ከጅምሩ ለኢትዮጵያ አትራፊ ሊሆን እንደማይችል አክለው ይገልጻሉ፡፡
ይሁን እንጂ በውስጥ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ያለውን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ ከኤርትራና ከግብፅ ጋር የፈጠረውን ስምምነት እንዲያቆም ኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ ጨዋታዋን በሚገባ መጫወት እንዳለባት ይናገራሉ፡፡ በተመሳሳይ አሜሪካን ጨምሮ በርካታ አገሮች ቀጣናውን በሚገባ ጠንቅቆ የሚያውቀውንና አሸባሪ ድርጅቶችን በመዋጋት በቂ የሰላም ማስከበር ልምድ ያካበተውን የኢትዮጵያን ጦር፣ ከአዲሱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውጪ እንዲሆን አይፈልጉም የሚለውን ዕሳቤ አጠንክረው ያስረዳሉ፡፡
ከሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ጋር ውዝግብ ውስጥ የገቡት ፑንትላንድና ጁባላንድ ግዛቶች ለኢትዮጵያ ባላቸው የተሻለ ዕይታ ሐሰን ሼክ ቁመናቸውን ካላስተካከሉ፣ በራሳቸው ላይ ነገር መጠምጥም እንደሚሆንባቸው ይናገራሉ፡፡ የፖለቲካ አጥኝውና ተንታኙ ይህን ይበሉ አንጂ ኢትዮጵያ የምትፈልገው ወታደራዊና ለንግድ የሚሆን የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ከሶማሌላንድ ጋር ተፈርሞ በነበረው ስምምነት ልክ ከሶማሊያ ይገኛል ወይ የሚለውን በጥርጣሬ የሚያዩት ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሶማሊያ በኩል የባህር በር የማግኘቷ ጉዳይ በሶማሊያ ፓርላማ የሚወሰን ከመሆኑም በላይ፣ ጥምረት የፈጠረችባቸው ግብፅና ኤርትራ ይህንን የማይፈቅዱ በመሆናቸው ኢትዮጵያ የተወሳሰበውን የግብፅ ፖለቲካ መጫወት ያስፈልጋታል ይላሉ፡፡
የዓለም አቀፍ ግንኙነትና የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም ኢንተርአክሽን ፎር ቼንጅ ኢን አፍሪካ የተሰኝ የምርምር ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወርቁ ያዕቆብ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ባደረገችው ስምምነት ትልቅ የዲፕሎማሲ ጫና ደርሶባታል የሚለውን የፖለቲካ አጥኝውንና ተንታኙን መሐመድ ዕሳቤ ይጋራሉ፡፡
የአንካራ ስምምነትን ተከተሎ ሶማሊያ ለኢትዮጵያ የገባችውን ቃል ባትፈጽም ኢትዮጵያ ምን ማድረግ ትችላለች ለሚለው ጥያቄ፣ ይህ ካልተፈጸመ ኢትዮጵያ የጁባላንድ፣ የፑንትላንድና ሌሎችም ግዛቶች ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ግጭት ውሰጥ እንዲገቡ በማድረግ፣ ችግር ወስጥ ያለውን የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት የበለጠ አደጋ ውስጥ ትጥለዋለች በሚል ፍርኃት ሶማሊያ የገባችውን ቃል ትፈጽመዋለች ይላሉ። በተመሳሳይ ሶሚሊያ በስምምነቱ የገባችውን ቃል አጥፋ ልትመለስ ብትሞክር፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በዘላቂነት የሶማሊያን ጥቅም ሊጎዳ የሚችል እንቅሰቃሴ ሊያደርግ የሚችልበት ዕድል አለው ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
ይሁን እንጂ ከኤርትራና ከግብፅ ጋር ያለው ስምምነት ሊቆም ይገባል የሚሉት ወርቁ (ዶ/ር)፣ በምሥራቅ አፍሪካ ያሉ አገሮች ስምምነት ፈጥረው በመሀላቸው ያለው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ግንኙነት እንዲዳብር ስትሠራ ታይታ የማትታወቀው ግብፅ አሁን መቃቃር ውስጥ ሲገቡ መምጣቷ፣ ለኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው አደጋ በመሆኑ ሁሉም ሊመክሩበትና ሊስማሙበት የሚገባ ነው ብለዋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ አንድነት ፈጥረው በኅብረት ለመሥራት በተስማሙበት ወቅት ድምጿን አጥፍታ የነበረችው ግብፅ አሁን ፀብ ውስጥ ሲገቡ መምጣቷ የባላንጣነቷ መገለጫ ነው ብለውታል፡፡ በቅርብ ርቀት ሆና በዘላቂነት ጦር አሥፍራ ኢትዮጵያን የማዳከም ትልሟ እንዲከሽፍ የኢትዮጵያ መንግሥት ሶማሊያ ላይ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ጫና ማሳረፍ አለበት ይላሉ፡፡
ይሁን እንጂ የግብፅን በሶማሊያ ውስጥ ተዋናይ ሆኖ መምጣት የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት፣ የአውሮፓ ኅብረትና ሌሎችም ድርጅቶችና አገሮች ዝምታ መርጠዋል ያሉት ወርቁ (ዶ/ር) ዓለም ዝም አለ ተብሎ ስለማይተኛ፣ መንግሥት በአገር ወስጥና በቀጣናው ያለበትን የቤት ሥራ ማከናወን እንደሚኖርበት አክለው ገልጸዋል፡፡ ግብፅ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ውስጥ የምትገኝ አገር ብትሆንም፣ በቀጣናው ጉዳይ እንድትገባ ሊፈቀድላት አይጋባም የሚሉት ምሁሩ፣ ከዚህ በኋላ ሶማሊያም ሆነች ሌሎች ጎረቤት አገሮች ከማንም በተሻለ በኢትዮጵያ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በችግር ውስጥ ያለውን የአፍሪካ ቀንድ ወደ ሌላ የከፋ ሁኔታ ይከተዋል በሚል ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ቀልብ ስቦ ለነበረው የሶማሊያና የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ቀውስ የአንካራው ስምምነት ሰላም አትራፊ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ቢሆንም፣ ከአገራዊ ጥቅም አንፃር ሲታይ ሁለቱ አገሮች ስምምነቱን ከፈጸሙ ሁለቱንም የበለጠ አትራፊ ሊያደርግ የሚችል እንደሚሆን የሚገምቱ አሉ፡፡
እ.ኤ.አ. ሰኞ ጥር 20 ቀን 2025 በዓለ ሲመታቸው የሚከናወነው አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ለራስ ገዟ ሶማሌላንድ ዕውቅና የመስጠት ፍላጎት እንዳላቸው መረጃዎች ሲወጡ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ዕውቅና የመስጠቱን ጉዳይ የሚቀጥሉበት ከሆነ ብዙ አገሮች አሜሪካን ተከትለው ተመሳሳይ ውሳኔ የመወሰን ባህል የተለመደ በመሆኑ፣ የሶማሌላንድ ዕውቅና ማግኘት አይቀሬ ይሆናል እየተባለ ነው፡፡
ግራም ነፈሰ ቀኝ የአንካራው ስምምነት የዲፕሎማሲ ሽንፈትን ወይም ትርፍ ሶማሊያ በቀጣይ ጥቂት ወራት ውስጥ ለኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በምትሰጠው መልስ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ በምታደርገው የዲፕሎማሲ ጫና ይወሰናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡