

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ
ዜና በምርጫ ወቅት ማጭበርበር አምስት ዓመታት እንደሚያስቀጣ የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ
ቀን: January 19, 2025
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011ን ለመተካት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተረቀቀው አዲስ አዋጅ፣ በተጭበረበረ መረጃ ለመወዳደርና ለመመረጥ የሚሞክሩ ግለሰቦችን በአምስት ዓመት እስራት የሚያስቀጣ ድንጋጌ በረቂቁ ተካቶ ቀረበ፡፡
በረቂቅ አዋጁ በሥራ ላይ ባለው ሕግ ሲሠራባቸው የቆዩ በርካታ ጉዳዮች ተሻሽለው መቅረባቸውን ጥር 9 ቀን 2017 ዓ.ም. ቦርዱ ይፋ አድርጓል፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከመናኛ ብዙኃንና ከሺቪክ ማኅበራት አመራሮች ጋር ለሁለት ዙር በተደረገ የምክክር መድረክ ለውይይት የቀረበው ረቂቁ አዋጅ፣ ከትርጓሜ ጀምሮ እስከ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች አዳዲስ ነጥቦችን ማካተቱ ታውቋል፡፡
በሥራ ላይ ባለው አዋጅ አራት የምርጫ ዓይነቶች ተብለው ከሚጠቀሱት ከጠቅላላ ምርጫ፣ ከአካባቢያዊ ምርጫ፣ ከማሟያ ምርጫና ከድጋሚ ምርጫዎች በተጨማሪ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫ በአምስተኝነት በአዲሱ አዋጅ እንዲካተት መደረጉን ቦርዱ አስታውቋል፡፡
የምርጫ ዘመቻን በሚመለከት ከዚህ ቀደም ‹‹ምርጫ ከመካሄዱ ከአራት ቀናት ቀደም ብሎ የምርጫ ዘመቻ እንቅስቃሴ መቆም አለበት›› የሚለው ድንጋጌ ተሻሽሎ፣ ‹‹ከምርጫ ቀን 48 ሰዓት ቀደም ብሎ›› እንዲሆን መደረጉም ታውቋል፡፡
ዕጩዎችንና መራጮችን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ማሻሻያዎችን ይዞ የቀረበው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ ክፍተቶችን የሚፈታ ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡ ለአብነት ከዚህ ቀደም ‹‹ምርጫ ሊካሄድ 90 ቀናት ሲቀሩት የዕጩዎች ምዝገባ መጠናቀቅ አለበት›› የሚለው ድንጋጌ አሳሪ በመሆኑ፣ ‹‹ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሚያደርገው ውይይት የጊዜ ገደቡ ይወሰናል›› በሚል ሕግ መተካቱ ተመልክቷል፡፡
የመራጮችን ዕድሜና የአንድ አካባቢ ነዋሪነት ሁኔታም አዲሱ አዋጅ አሻሽሎታል ተብሏል፡፡ አንድ መራጭ ለመምረጥ ብቁ የሚያደርገው 18 ዓመት የዕድሜ ገደብ ለመምረጥ በተመዘገበበት ዕለት ሳይሆን፣ ምርጫው በሚካሄድበት ቀን ታሳቢ እንደሚደረግ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ በዚህም ምርጫው በሚካሄድበት ዕለት 18 ዓመት የሚሞላ ማንኛውም ሰው የመምረጥ መብቱ ይጠበቅለታል ተብሏል፡፡ ሆኖም የአንድ ሰው የመምረጥ መብት የሚረጋገጠው ለመምረጥ ሲመዘገብ፣ በዚያ አካባቢ ለስድስት ወራት መኖሩን የሚያረጋግጥ መረጃ ሲቀርብ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ ቀደም ለመምረጥ የሚያበቃ የአዕምሮ ጤና ሁኔታን በተመለከተ ‹‹በሚመለከተው አካል›› ተብሎ ሲሠራበት የቆየው ድንጋጌ ቀርቶ፣ ‹‹በፍርድ ቤት ሲወሰን›› በሚል ተሻሽሎ መቅረቡን ቦርዱ ገልጿል፡፡
የዕጩዎች ምዝገባን በሚመለከት ዕጩ ሆኖ የሚቀርብ ሰው ሲመዘገብ 21 ዓመት የሞላውና የተመዘገበበት አካባቢ ነዋሪ መሆኑን የሚጠቁም መረጃ ማቅረብ አለበት የሚል ድንጋጌ በአዲሱ አዋጅ ተካቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ሲሠራበት በቆየው ሕግ ዕጩዎችን የማስመዝገቢያ ጊዜ ምርጫው ሦስት ወራት (90 ቀናት) ሲቀረው መጠናቀቅ እንዳለበት የሚደነግገው አንቀጽ፣ አሳሪ ነው በሚል፣ መለወጡን ቦርዱ አመልክቷል፡፡ በዚህም ለውጥ የዕጩዎች ምዝገባ ቀነ ገደብ ቦርዱ በምርጫው ከሚሳተፉ አካላት ጋር በሚያደርገው ውይይትና መግባባት ይወሰናል የሚል ማሻሻያ ቀርቧል ተብሏል፡፡
በተሻሻለው አዲስ አዋጅ ውስጥ ተሻሽለው የቀረቡ ሌሎች ጉዳዮች መካከል መለያ ምልክት፣ የተፈናቃዮች የመምረጥ መብት፣ የዕጩዎች ቅያሪና የውጤት ይፋ ማድረጊያ ነጥቦችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች መኖራቸው ተመልክቷል፡፡
ተፈናቃዮች መምረጥ የሚችሉት ከተፈናቀሉበት ቦታ የሚገኝ መረጃን ተመርኩዞ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ዕጩዎች የመወዳደሪያ መለያ ምልክታቸውን ምርጫው ከሚካሄድበት ቀን አንድ ወር እስኪቀረው ባለው ጊዜ ማስመዝገብ እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡ ለምርጫው በሚቀርቡ የኅትመት ውጤቶች ላይ ዕጩዎች ምልክቶቻቸውን መቀየር ወይ መለወጥ የሚችሉት፣ የምርጫው ቀን አምስት ቀናት እስኪቀሩት ብቻ ነው ተብሏል፡፡ በምልክት ይገባኛል ጉዳይ ውዝግብ ከተፈጠረ የግልግል ሒደቱ አልፎ ከምርጫው ዕለት 15 ቀናት ቀደም ብሎ የምልክቱ ባለቤት የሆነው ወገን ምልክቱን ሊያቀርብ እንደሚገባም በረቂቅ ሕጉ ተካቷል፡፡
አንድ ለምርጫ የቀረበ ዕጩ እጅ ከፍንጅ በሚያስጠይቅና በሚያሳስር፣ እንዲሁም በፍርድ ቤት ውሳኔ ብቻ ካልሆነ በስተቀር ዕጩነቱ እንደማይስተጓጎል ነው በአዲሱ አዋጅ የቀረበው፡፡ ዕጩ መቀየር ወይም በሌላ መተካት የሚቻለው ደግሞ ከምርጫው መካሄጃ ከአንድ ወር ቀደም ብሎ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ውጤት ይፋ ማድረግን በተመለከተ ደግሞ በምርጫ ጣቢያዎች ከአምስት ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውጤት ይፋ ይሆናል ተብሏል፡፡ በቦርዱ ደረጃ ደግሞ ከዚህ ቀደም በ15 ቀናት ውስጥ ተብሎ የተደነገገው ወደ 20 ቀናት ከፍ ማለቱ ታውቋል፡፡ ውጤትን በተመለከተ አጨቃጫቂ ሁኔታ ከተፈጠረ ሁኔታው ተጣርቶ በ30 ቀናት ውስጥ ውጤቱ ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡
እነዚህን መሰልና ሌሎችንም በርካታ ማሻሻያዎችን አካቶ የቀረበው አዲሱ የምርጫ ቦርድ ረቂቅ አዋጅ፣ በተለይ ማጭበርበርን በተመለከተ ጠንከር ያለ የቅጣት ድንጋጌ ይዞ መቅረቡ ተመልክቷል፡፡
የአዲሱን ሕግ ዝርዝር የማሻሻያ ነጥቦች ለውይይት ያቀረቡት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕግ ክፍል ኃላፊ አቶ ኢድሪስ ሰልማን፣ በማጭበርበር ምርጫ ውድደር ውስጥ መግባትን በሚመለከት አስተማሪ የሆነ ጠንካራ ቅጣት መጣል አስፈላጊ መሆኑ እንደታመነበት ተናግረዋል፡፡
‹‹የግል ዕጩዎች በምርጫ ፉክክሩ ያቀረቡት መረጃ የተጭበረበረ ከሆነ መረጃ አቅራቢው በአምስት ዓመት እስራት እንዲቀጣ ተሻሽሎ ቀርቧል፤›› በማለት የቅጣቱን ውሳኔ ማደግ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የምርጫ ተወዳዳሪዎች በዕጩነት ሲቀርቡ ሊያቀርቡ የሚገባው የድጋፍ ፊርማ መጠንና በአንድ የምርጫ ጣቢያ ሊሳተፉ የሚችሉ መራጮችን ብዛት በተመለከተ መጠነኛ ማሻሻያዎች መደረጉንም፣ የሕግ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም የክልል ምክር ቤቶች የመቀመጫ ቁጥር መጠን ላይ ማሻሻያ የማድረግ ጥያቄ ሲኖር፣ ክልሉ ምርጫ ከመካሄዱ ከአንድ ዓመት ቀደም ብሎ ለቦርዱ ማሳወቅ ይገባዋል የሚል ማሻሻያም ረቂቅ አዋጁ ይዞ መቅረቡን አስረድተዋል፡፡
ዓርብ ጥር 9 ቀን 2017 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ከመገናኛ ብዙኃንና ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በተካሄደ መድረክ ለውይይት የቀረበው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ፣ ጥልቅ ጥናትን አልፎ ተዘጋጅቶ መቅረቡን የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ የአሠራር ክፍተቶችን ለመሙላት፣ ቅር የተሰኙ ፓርቲዎች ያሰሙ የነበረውን ቅሬታ ለመፍታት፣ የልማት አጋሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሲሰጡ የቆዩትን ግብዓትና የማሻሻያ ሐሳብ ለማካተት በሚያስችል መንገድ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ አዋጁን ለማሻሻል ጥናት ሲደረግና ግብዓት የመሰብሰብ ሥራ ሲከናወን መቆየቱን የጠቀሱት ሰብሳቢዋ፣ ተከታታይ ውይይት በማድረግ በሒደት ዳብሮ እንደሚፀድቅ አስረድተዋል፡፡
ሰብሳቢዋ ይህን ቢሉም በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን ቅሬታ እንዳላቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ከስብሰባው ቀደም ብሎ ረቂቅ አዋጁ ለፓርቲዎች አለመላኩን፣ በራሳቸው ተወያይተውበት፣ የሕግ ባለሙያዎችን አማክረውና የሚስተካከል የሚሉትን ሐሳብ አደራጅተው ለመምጣት ዕድል አለመሰጠቱ መሠረታዊ ችግር መሆኑን የአንዳንድ ፓርቲዎች ተወካዮች ገልጸዋል፡፡ በስብሰባው ዕለትም ቢሆን በሰነድ (በወረቀት) ረቂቁ አለመቅረቡ ተጨማሪ ችግር ነው ብለዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ግልጽና አሳታፊ በሆነ መንገድ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁን ሒደት እንዲመራ ያሳሰቡት የፓርቲዎቹ ተወካዮች፣ አዋጁን ለማሻሻል የመካለብ ሁኔታ መኖሩን ነው በሥጋትነት የገለጹት፡፡