የጥምቀት ክብረ በዓል በምንጃር ሸንኮራ ኢራንቡቲ

ኪንና ባህል የመገለጡ ቀን እና ትውፊቱ

ሔኖክ ያሬድ

ቀን: January 19, 2025

ከአንድ ሺሕ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ስድስት ዓመታት በፊት በዛሬዋ ቀን ማለትም ጥር 11 ቀን 31 ዓ.ም. (5531 ዓመተ ዓለም) ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ የተጠመቀበት ነው፡፡

እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓመቱ በመጥምቁ (አጥማቂው) ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበትን ቀኑን በማስታወስም በምሥራቅም ሆነ በምዕራብ ያሉ ክርስቲያኖች እንደዘመን ቀመራቸውና ትውፊቶቻቸው የጥምቀት በዓልን ያከብሩታል፡፡ በዓሉ ‹‹ኤጲፋንያ›› (አስተርእዮ/መገለጥ/መታየት) በመባልም ይታወቃል፡፡

የመገለጡ ቀን እና ትውፊቱ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የጥምቀት ክብረ በዓል በባቱ ዝዋይ ሐይቅ

የጥምቀት በዓልን ልደት በተከበረ በ12ኛው ቀን በምሥራቅም በምዕራብም ያሉ የኦርቶዶክስና ካቶሊክ ክርስቲያኖች ያከብሩታል፡፡ የተወሰኑ ኦርቶዶክሳዊ አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ጥር 11 ቀን (በጁሊያን ቀመር ጃንዋሪ 6) ሲያከብሩ ግሪጎሪያን ካላንደርን የሚከተሉት ‹‹ጃንዋሪ 6›› ብለው ያከበሩት ከ13 ቀናት በፊት ነበር፡፡

በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጸው፣ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ በዮሐንስ እጅ ተጠምቋል፡፡ ይህንን በማሰብም በአዲስ አበባም ሆነ በመላው አገሪቱ በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኙ በየአብያተ ክርስቲያኑ ያሉ ታቦቶች ትናንትና ቅዳሜ በከተራው ዕለት  ጥር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቅዱስ መንበራቸው ተነስተው በዓሉ ወደሚከበርበት ባህረ ጥምቀት ዘልቀዋል፡፡

የመገለጡ ቀን እና ትውፊቱ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ከተራ ‹‹ከተረ›› ከሚለው ቃል የተገኘ ሲሆን የሚወርድ ውኃ መገደብ ማለት ነው፡፡ ውኃው የጥምቀት ዕለት ምዕመናን የሚጠመቁበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በገጠራማ አካባቢዎችም ይሁን በከተማ ጥምቀት የሚከበረው ውኃ በሚገኝበት አካባቢ ነው፡፡

የነገረ መለኮት ምሁሩ አባ ኃይለ ማርያም መለሰ (ዶ/ር)፣ በአንድ መጣጥፋቸው እንዳብራሩት፣ ‹‹ከተራ ስንል በዋዜማው ምዕመናን ተሰብስበው በአንድነት የሚሆኑበት ነው። ከተራ ማለት መሰብሰብ ክብ ሠርቶ በአንድ ላይ ምስጋና ማቅረብን የሚያመለክት ቃል ነው፡፡››  አያይዘውም ‹‹በአራቱም ማዕዘን ምዕመናን በአንድ ላይ ሆነው በዓሉን ያከብራሉ፡፡ ይህም በዓል መገለጥ (ኤጲፋኒያ) ይባላል። ይህም ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ መገለጥ ሆኗል። የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ አንድነትና ሦስትነት ተገልጿል። ክርስቲያኖችም ይህንን በዓል የምናከብረው ለበረከትና ለረድኤት ነው፤›› ሲሉ አክለዋል።

በዓለ ጥምቀት ከአክሱም እስከ ላሊበላ፣ ከጎንደር እስከ አዲስ አበባ፣ ከማይጨው እስከ ዝዋይ፣ ከሐዋሳ እስከ ጅማ፣ ከአሶሳ እስከ ጋምቤላ በሁሉም ሥፍራዎች ይከበራል።

የመገለጡ ቀን እና ትውፊቱ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ጥምቀትን በሥዕል በተክለማርያም ዘውዴ

በኢትዮጵያና ኦርቶዶክሳዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በምትገኝባቸው አገሮች  የሚከበረው  የጥምቀት በዓል፣ ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው፣ በየባሕረ ጥምቀቱ የሚከበሩ በመሆናቸው፣ አገሬውን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መስህብነትን በመጎናጸፉ፣ ቱሪስቶችን እንደሳበ ነው፡፡

በከፍተኛ ደረጃ ከሚከበርባቸው ቦታዎች አንዱ በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የሚገኘው የኢራንቡቲ መንደር ነው፡፡ በዓሉ መከበር የጀመረው ከስድስት ምዕት ዓመታት በፊት በ14ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ ይወሳል፡፡ ከተራው የሚከናወነው በሸንኮራ ወንዝ ላይ ሲሆን፣ 44 ታቦታት ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ይወርዳሉ፡፡

‹‹ኢራንቡቲ ዳግማዊ ዮርዳኖስ›› የሚለው ተጓዡ ጋዜጠኛ ሔኖክ ሥዩም ስለ ቦታው በመጽሐፉ እንዲህ ከትቧል፡፡  ‹‹ለጥምቀት በዓል ኢራንቡቲ ስደርስ የሆነውን አልረሳውም። ባልጪ አማኑኤልን አጅቤ ወረድኩ። ባልጪ አማኑኤል አፄ ዘርዐ ያዕቆብ የተከሉት ሸንኮራ የሚገኝ ታሪካዊ ደብር ነው። ከዚያ ከመጥምቀ መለኮት ሸንኮራ ዮሐንስ ጋር ሲገናኙ የነበረው ትዕይንት እስከ አሁን ህልም ይመስለኛል።

‹‹የምንጃር ሸንኮራ ሰውና የቃል ኪዳኑን ታቦት ዝምድና አየሁ። ከአርባ አራት ታቦታት ጋር ጥምቀት ዋልኩ። ያንን ለአገሬ ሰው ለአዲስ አበባ ቅርብ ቦታ ይሄ አለ ብዬ አወጅኩ። በእርግጥም ተሳክቶልኛል። ብዙ ለውጦች ለማየት ቻልኩ። ጥምቀትን በአንዴ ብዙ ቦታ መኾን ብችል ይሄኔ ወደ ምንጃር እየመጣሁ ነበር።

የሐይቁ ላይ አከባበር

የጥምቀት በዓል ከሚከበርባቸው ቦታዎች መካከል ባቱ ከተማ ዳርቻ ባለው በዝዋይ ሐይቅ ውስጥ የሚገኙት ገዳማት አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ ቅዱስ ሚካኤል፣ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም፣ አርባዕቱ እንስሳትና ፀዴቻ አቡነ አብርሃም ይጠቀሳሉ፡፡ ከአምስቱ ገዳማት አቡነ ተክለ ሃይማኖትና ደብረ ጽዮን ከደሴታቸው በመውጣት ሦስት ኪሎ ሜትር የሚሆነውን የሐይቁን ክፍል አቋርጠው ምድር ላይ በማክበር ብቸኛ ያደርጋቸዋል፡፡ የተቀሩት ሦስቱ ደግሞ ከሐይቁ ዳር በጣም የራቁ በመሆናቸው ከቤተ መቅደሳቸው በመውጣት በግቢያቸው የሐይቁ ጠርዝ ላይ ድንኳን በመጣል እዚያው ያከብሩታል፡፡

በዕለተ ቀኑ ከሃይማኖታዊው ሥነ ሥርዓት በኋላ ካህኑ በሃሌታ፣ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ ታቦተ ሕጉን አጅበው፣ እንደያመጣጣቸው ወደየአጥቢያቸው የሚመለሱት ከተወሰኑት በቀር ዛሬ እሑድ ጥር 11 ቀን ይሆናል።

 በዕለቱም ካህናቱ ከሚያስተጋቡት ዝማሬዎች አንዱ ‹‹ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ›› ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀ የሚለው ነው፡፡

ምዕመናኑ ታቦታቱን ሲያጅቡ ከሚያሰሟቸው በዝማሬቸው መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

‹‹እዩት ወሮ ሲመለስ

 መድኃኔ ዓለም በፈረስ

 የሚካኤል አንበሳ

 ሎሌው ሲያገሳ።

 ማር ይፈሳል ጠጅ

 በእመቤቴ ደጅ፤

 በሕይወት ግባ በዕልልታ

       የዚህ ሁሉ አለኝታ

       በሕይወት ግቢ እምዬ

       እንድበላ ፈትዬ፡፡››

ወጣቶችም ታቦቶቹን የሚያሞጋግሱት በየዓመቱ የጥምቀት በዓል ሲመጣ ነው፡፡ በተለይ በጥምቀት ማግሥት የሚከበረው የቃና ዘገሊላና የቅዱስ ሚካኤል በዓላት ላይ ተዘውትሮ ይደመጣል፡፡

‹‹እጣን እጣን ይላል መሬቱ፣

ሚካኤል ያረፈበቱ፡፡

ማር ይፈሳል ጠጅ፣

ባርባራቱ ደጅ፤

የቅዱስ ሚካኤል አፋፉ ደብር፣

መሳለሚያው ዋርካ ጥዱ ምን ያምር፡፡

አለው አለው ሞገስ፣

ታቦት ሲነግሥ፡፡››

    ዘመነ አስተርእዮ

የቤተክርስቲያን መምህራን እንደሚያብራሩት፣ ከዛሬ ጥር 11 ቀን ጀምሮ እስከ ጾመ ነነዌ ዋዜማ ያለው ጊዜ ነው (ዘንድሮ እስከ የካቲት 2 ድረስ ይሆናል) ዘመነ አስተርእዮ (ኤጲፋንያ) ይባላል። በዚህ ጊዜ ውስጥ አምላክ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡ፣ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ የአንድነትና የሦስትነት ምሥጢር መታወቁ፣ በቃና ዘገሊላ በተደረገው ሠርግ ላይ የመጀመሪያው ተዓምር በመፈጸሙ፣ አምላካዊ ኃይሉ መገለጡ፣ እየታሰበ ምስጋና ይቀርብበታል።

የኢየሩሳሌምና የቅዱሳት ቦታዎች ታሪክ ኢየሩሳሌምን ለመሳለም ለሚሔድ መንገደኛ መሪ እንዲሆን በሚል ርዕስ አቶ ጳውሎስ መን አመኖ በጻፉት መጽሐፍ እንደገለጹት፣ ‹‹ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ተወልዶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ 30 ዓመት ሲሆነው በዮርዳኖስ ወንዝ ሰማያዊው በመሬታዊው በዮሐንስ እጅ በትኅትና ተጠመቀ፡፡ መሢሕነቱንና አምላክነቱን አስመሰከረ፡፡ ምስክሩም ከሰው አልነበረም ወይም በመልአክ አፍ አልተነገረም፡፡ ነገር ግን ከዘለዓለም ጀምሮ የባሕርይ አንድነት የነበረው አባቱ ይህ ነው ልጄ የምወደው ደስታዬን የማይበት ብሎ መሰከረለት፡፡››

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በዓሉን በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መዝገብ ውስጥ እንዲገባ፣ ለመንግሥታቱ ድርጅት የባህል ተቋም ዩኔስኮ በላከው ሰነድ ላይ እንደተብራራው፣ በዓሉ ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ አከባበሩ በተጓዳኝም ባህላዊ ገጽታው ይታያል፡፡ ወጣቶች የሚተጫጩበት የትዳር አጋራቸውን የሚመርጡበት አጋጣሚዎችን ከመፍጠሩም ባለፈ በከተማም ሆነ በገጠር ሰውን የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡

የጥምቀት በዓል የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ ሕይወትና አንድነት በከፍተኛ ደረጃ የሚያጠናክር እንደሆነ ይስተዋላል፡፡ ለጥምቀት በዓል የቤተሰብ አባላት ከያሉበት ይሰባሰባሉ፡፡ ዘመድ ከዘመዱ ይጠያየቃል፡፡ ስለዚህ ባህልን ከመጠበቅና ከማስቀጠል አንጻርም የጥምቀት በዓል የጎላ ድርሻ  አለው፡፡ በዓለ ጥምቀት ደማቅ ማኅበራዊና ባህላዊ ገጽታዎች (ዕሴቶች) አሉት፡፡ እነዚህ ዕሴቶች በልዩ ልዩ ሁኔታ የሚገለጹ ለሰላምና ለዕርቅ፣ ለአገር የመልካም ገጽታ ግንባታ፣ ለአንድነትና ለመከባበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

ታሪካዊ ዳራ

ጠቅላይ ቤተ ክህነት ባሳተመው አንድ መጣጥፍ ላይ እንደተገለጸው፣ ጥምቀት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓተ አምልኮ መሠረት ታሪካዊ መሠረቱን ሳይለቅ አሁን እንዳለው መከበር የጀመረው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን ነገሥታቱ አብርሃና አጽብሃ የክርስትና ሃይማኖትን ተቀብለው ብሔራዊ ሃይማኖት ሲያደርጉ የጥምቀት በብሔራዊ ደረጃ እንዲከበር አድርገዋል፡፡ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ በብሉይ ኪዳን ሥርዓት መሠረት ሲከበር የኖረ  የመጸለት (ዳስ) በዓል የሚባል ስለነበር ጥምቀት በእሱ ምትክ የጉዞና የአደባባይ በዓል ሆኖ እንዲከበርም አድርገዋል፡፡

እነዚህ ቅዱሳን ነገሥት ለሃይማኖቱ ማደግ ብቻ ሳይሆን ለበዓሉም መስፋፋት ተግተው ሠርተዋል፡፡ በዓሉ በየዘመኑ እያደገ መጥቶ በአፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅዱስ ያሬድ በዘመኑ ይፈጸም የነበረውን የበዓሉን አከባበር ሥርዓት በማየት ለበዓሉ አከባበር የሚስማማ የዜማ ሥርዓት አዘጋጅቷል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለበዓሉ ያዘጋጀው የዜማ ድርሰትም ከበዓሉ ዋዜማ (ከተራ) ጀምሮ የሚፈጸም በመሆኑ ለበዓሉ ተጨማሪ ድምቀትንና ሥርዓትን ሰጥቶታል፡፡

ቅዱስ ላሊበላም በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአንድ ወጥ አለት ፈልፍሎ ባነፃቸው ውቅር አብያተ ክርስቲያን ሥራ ውስጥ በዓሉን ሁሉም ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በአንድነት የሚያከብሩበትን ቦታ በዮርዳኖስ ወንዝ ስም ምሳሌነት አካቶ ሠርቶታል፡፡ እስካሁንም ድረስ በላሊበላ ከተማ የሚገኘው ይህ ቦታ ‹‹ዮርዳኖስ›› በመባል ይታወቃል፡፡

ከዚያ በኋላ የተነሱ ነገሥታት እንደ አፄ ይኩኖ አምላክ (13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) አፄ ዘርዓ ያዕቆብና አፄ ናኦድ (በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) ካህናቱና ሕዝቡ ታቦታቱን አጅበው በአንድነት የሚያከብሩትን ይህንን ጥንታዊና መንፈሳዊ በዓል በየዘመናቸው ደምቆ እንዲከበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ይወሳል፡፡ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም በጎንደር የነገሡት አፄ ፋሲል ለመዋኛ ገንዳ ያሠሩት የጥምቀት በዓል ማክበሪያ የተደረገ ሲሆን፣ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም ከነገሡት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጀምሮ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በዓሉ  እየተከበረበት ይገኛል፡፡ ከከተማዋ ስፋት አንፃር በየአካባቢው ባሉ ከ100 በላይ ባህረ ጥምቀት ምዕመኑ በዓሉን እያከበረ ይገኛል፡፡

ዓለም አቀፉ የባህል ተቋም ዩኔስኮ፣ በወርኃ ጥር የኢትዮጵያ አደባባዮች ደምቀው እንዲታዩ የሚያደርገውን የጥምቀት ክብረ በዓልን በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት ከአምስት ዓመት በፊት ታኅሣሥ 1 ቀን 2012 ዓ.ም.  የመዘገበው በቦጎታ ኮሎምቢያ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች የበይነ መንግሥታት ኮሚቴ ስብሰባ ላይ መሆኑ ይታወሳል፡፡