January 19, 2025

ናታን ዳዊት

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ በይፋ ሥራ ጀምሯል፡፡ አገራዊ ኢኮኖሚውን ከመደገፍና ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች የሚውል ካፒታል ለማሰባሰብ እንደ አንድ አማራጭ የሚወሰድና ለኢትዮጵያ እንደ አዲስ ምዕራፍ የሚታይ ዕርምጃ አድርገን ልንወስደው እንችላለን፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ረዥም ዕድሜ ያለው አገር ካፒታል ገበያ ብርቅ ሆኖባት እስከዛሬ መቆየቱ አግባብ እንዳልነበር ካሰብንም ገበያው ዘግይቶም ቢሆን መጀመሩ እንደ አገር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ በሌላ አንጻር ዛሬ እንደ አዲስ ብለን የጀመርነው የካፒታል ገበያ ከዛሬ 60 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ይሠራበት የነበረ መሆኑን ስናስብ ደግሞ በመካከል የጠፋው ጊዜ ማስቆጨቱ አይቀርም፡፡ ቀድመን እንደመጀመራችን በዚያው ባለመቀጠላችን እናገኝበት የነበረው ጥቅም ምን ያህል እንደሆነም መገመት አያዳግትም፡፡ 

የካፒታል ገበያ በንጉሡ ጊዜ እንደ አጀማመሩ ቢቀጥል ዛሬ ሊደረስበት የነበረው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በእጅጉ የተለየ ይሆን ነበር የሚለው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህም በኋላ በዚህ ገበያ በአግባቡ ለመጠቀም በርትቶ መሥራት ግድ ይላል፡፡ የካፒታል ገበያ መፈጠር ይዟቸው የሚመጡ በርከት ያሉ ዕድሎች ይኖራሉ፡፡ በዋናነት ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች የሚሆኑ ካፒታል መፍጠር ዋናው ነገር ነው፡፡ ዜጎችም ባላቸው አቅም በገበያው ኢንቨስት እያደረጉ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ዕድል ይሰጣል፡፡ ገንዘብ በባንክ ተቀምጦ እዚህ ግባ በማይባል ወለድ ከሚገኝ ጥቅም የተሻለ ጥቅም ሊያስገኙ ወደሚችሉ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ውስጥ በቀላሉ ተሳታፊ መሆን የሚቻልበትን ዕድል ይሰጠዋል፡፡ ይህም ዜጎች ሕጋዊነቱ በተጠበቀ ዘመናዊ ኢንቨስትመንት ውስጥ በመሳተፍ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ የሚያገኙበት በመሆኑ የዚህ ገበያ መፈጠር ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ 

ስለዚህ የገበያው መፈጠር እንደ አገር ሊያስገኝ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን፣ እንዲሁም በግለሰብና በቡድን ደረጃ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መሆኑን ሁሉም ማኅበረሰብ ሊገባው በሚችለው ልክ መረጃው እንዲኖረው ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የካፒታል ገበያ ጠቀሜታዎች የተለያዩ መገለጫዎች ያሉት ሲሆን በአግባቡ እንዲተገበር ከተደረገ የተደራጀ መረጃ መስጠት ለገበያው መሳለጥ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ በካፒታል ዕጦት ሼልፍ ላይ የቀሩ አዋጭ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ቀን ወጥቶላቸው በተግባር ሊታዩ የሚችሉበት ዕድል የሚፈጥር በመሆኑም በፋይናንስ ዕጦት ተሸፋፍነው የቀሩ ኢንቨስትመንቶች በዚህ ገበያ ቦታ ሊያገኙ ይችላሉ የሚለውንም ጥያቄ ለመመለስ ዘርዘር ያለ መረጃ መስጠት ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ባለፉት ዓመታት ይህንን ገበያ ለመፍጠር ኃላፊነት የወሰዱ ባለሙያዎችና የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እየሰጡ የነበረው መረጃ በድፍኑ ጠቃሚ ነው ከሚል የዘለለ ነው ሊባል ስለማይችል ጥያቄ በሚመልስ መልኩ ኅብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እያገኘ ነው ተብሎ አይታመንም፡፡ ገበያው የሁሉንም ኅብረተሰብ ተሳትፎ የሚጠይቅ ከመሆኑ አንጻር እንዲሁም አዲስ የቢዝነስና የአገልግሎት ዘርፍ በመሆኑ በገበያው ውስጥ የሚኖረውን አጠቃላይ አሠራሩን በተገቢው መንገድ ለማቀበልም ቢሆን ያልተቋረጠ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ 

የካፒታል ገበያ ለብዙኃኑ ምንድነው? ብዙኃኑን የሚጠቅመውስ እንዴት ነው? የሚሉ ጥያቄዎችና ከዚሁ ጋር የተያያዙ መረጃዎች ብዙኃኑ በሚገባው መንገድ ማስረዳትም አንዱ የሥራው አካል መሆን አለበት፡፡ 

ሰዎች ባላቸው አቅም ኢንቨስት የሚያደርጉበትን ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ያለችንን ኢንቨስት አደርጋለሁ የሚል ግለሰብም ሆነ ቡድኖች እንዴት ተሳታፊ እንደሚሆኑ ከወዲሁ በበቂ ሁኔታ መረጃ መስጠት ካልተቻለ ብዥታዎች ስለሚፈጠሩ በመገንዘብ ቀድሞ በቂ መረጃዎችን መስጠት በኋላ ሊፈጠሩ የሚችሉ ያልተገቡ መጓተቶችን ሊያስቀር ይችላል፡፡ ገበያው የሚያቅዳቸው ግብይቶችም በአግባቡ እንደ አካሄዱም ቢሆን በቂ መረጃ ለማኅበረሰቡ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ 

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ሀብታቸውን አፍሰው ባለአክሲዮኖች ሊሆኑ የቻሉት አደረጃጀቶች ብዙ ደክመው ነው፡፡ ባንክና ኢንሹራንስ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ አብራርተውና ባለአክሲዮን በቂ ግንዛቤ አስጨብጠው ጭምር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ 

ስለዚህ የካፒታል ገበያው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ገበያውም እንዲደራ ከተፈለገ የመረጃ አሰጣጡም ጥንቃቄ የተሞላበት በኃላፊነት መሠረት ያደረገ መሆኑን ይገባዋል፡፡ ይህንን ማድረግ ዜጎች ስለጥቅምና ጉዳዩ በሚገባ በመረዳት የገበያው ተሳታፊ ያደርግባቸዋል፡፡ 

እስካሁን የምንሰማቸው መረጃዎች ጠቅለል ያሉ የካፒታል ገበያን ምንነት ለሚያውቁት አካላት ሊረዱት የሚችሉት ነው፡፡ ከዚህ በአንጻሩ ግን ይህ ገበያ ምን ማለት እንደሆነ ያልተረዱና ብዥታ ያለባቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ከሥራው ጎን ለጎን በቂ መረጃ ይሰጥ የምንለው፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ የሥራ ሒደት ተሳትፊ የሚሆኑ ተዋንያኖች ኩባንያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ኃላፊነትና ተጠያቂነትም ምን እንደሆነ ማን ምን ይሠራል የሚለውም ጉዳይ በአግባቡ መረጃ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ 

በአጠቃላይ የካፒታል ገበያ አሠራርን የተመለከቱ በተለይም በግብይቱ ውስጥ ባላቸው አቅም ተሳታፊ ሊሆኑ የሚችሉ ዜጎች ትርጉም ያለው አሰተዋጽኦ እንዲኖራቸው ከተፈለገ ያልተቋረጠና የተብራራ መረጃ ወሳኝ ነው፡፡