
January 19, 2025

የነዳጅ ግብይት ሥርዓትን ለመዘርጋትና ለመቆጣጠር ያስችላል የተባለ አዲስ አዋጅ ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል፡፡ በኢትዮጵያ በነዳጅ ሥርጭት ግብይትና በአጠቃላይ በዘርፉ ያሉትን ማነቆዎች ሊያቃልል ይችላል የተባለው ይህ አዋጅ፣ አሁንም ክፍተት እንዳለበት እየተገለጸ ነው፡፡ በፀደቀው አዋጅና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በኢትዮጵያ የነዳጅ ግብይት ላይ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች መካከል አንዱ ከሆኑት ሰርካለም ገብረ ክርስቶስ (ዶ/ር) ጋር ዳዊት ታዬ ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ሪፖርተር፡- የነዳጅ ግብይትና ቁጥጥርን የተመለከተ አዋጅ ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል፡፡ የአዋጁን ድንጋጌዎችና አስፈላጊነት እንዴት ያያሉ?
ዶ/ር ሰርካለም፡- ምንም ዓይነት ነገር የሕግ ማዕቀፍ ከሌለው ለሙስና፣ ለግብይት ሥርዓት ብልሽትና ለመሳሰሉት ችግሮች ተጋላጭ ይሆናል፡፡ በየትኛውም ዘርፍ ያለ ቢዝነስ የራሱ የሆነ ሕጋዊ አሠራር ያስፈልገዋል፡፡ ከነዳጅ አቅርቦትና ሥርጭት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ሕገወጥ ተግባራት በሙሉ በሕግ ካልተያዙ ከፍተኛ ችግር ያስከትላሉ፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ የነዳጅ ግብይት ሥርዓቱን ለመቆጣጠር የሚያስችል እንዲህ ያለ አዋጅ አስፈላጊነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ እንዲያውም ይህ አዋጅ ዘግይቷል ባይ ነኝ፡፡ በነገራችን ላይ ከዚህ ቀደም ከ10 እና 15 ዓመታት በፊት ከነዳጅ ግብይት ጋር የተያያዙ አሠራሮችን የተመለከቱ በርካታ ጥናቶች ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ደርሰውት የነበረ ቢሆንም፣ ምንም የተወሰደ ዕርምጃ አልነበረም፡፡ ብዙ ጥናቶች ሼልፍ ላይ ተቀምጠው ቀርተዋል፡፡ እነዚህ ጥናቶች ታይተው ወደ ተግባር ተቀይረው ቢሆን፣ ከሰሞኑ የወጣው አዋጅ እስከ ዛሬ ባልቆየ ነበር፡፡ አዲሱ አዋጅ በጣም አስፈላጊ ነው የሚባልበት ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በአቅርቦት በኩል እጥረት አለ፡፡ እጥረቱ የሚፈጠርበት አንዱ ምክንያት ደግሞ ለነዳጅ መግዣ የሚወጣው ገንዘብ በእጅጉ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ይያያዛል፡፡ የነዳጅ ግዥ የውጭ ምንዛሪ ወጪንም ከፍ ስለሚያደርግ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ በቂ የሆነ ነዳጅ የማይገባበት አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን ለነዳጅ ግዥ እንደምታውል ይታመናል፡፡ አንዳንዴ እንዲያውም ዓመታዊ የነዳጅ ግዥ በዓመት ከወጪ ንግድ ከሚገኘው ገቢ እስከ 65 በመቶ ይደርሳል ነው የሚባለው፡፡ ይህ ሠራዊቱ የሚጠቀምበትን ሳይጨምር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የነዳጅ ግዥ በጣም ከፍተኛ ሊባል የሚችል የውጭ ምንዛሪ የሚወጣበት በመሆኑ በጣም ወሳኝ ሸቀጥ (Critical Commodity) ነው፡፡ አንዳንዴ እንዲያውም የፖለቲካ ሸቀጥ ‹‹Political Commodity›› ተብሎም ይጠቀሳል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ነዳጅን ለመግዛት የሚወጣው ወጪ በራሱ ራስ ምታት ነው፡፡ ምክንያቱም የነዳጅ የመግዣ ዋጋ በጣም ብዙ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የአቅርቦት ችግር የሚስተዋል ከሆነ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ችግር ይዞ ይመጣል፡፡ የአቅርቦት እጥረቱን ምክንያት በማድረግ ሙስናውም ይጨምራል፣ ግብይቱም ይበላሻል፣ ኮትንትሮባንዱም ይባባሳል፣ እንዲሁም ነዳጅን ከሌላ ግብዓት ጋር ቀላቅሎ የመሸጥ ሕገወጥ ድርጊት የሚታየው በእጥረቱ ምክንያት ነው፡፡ በመሆኑም በዘርፉ ውስጥ የሚታዩ ሕገወጥ ተግባራትን በሙሉ ለመቆጣጠር የሕግ ማዕቀፍ ቀርፆ መተግበር የግድ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሰሞኑን የወጣው አዋጅ ቢዘገይም መውጣቱ በተወሰነ ደረጃ በግብይት ሥርዓቱ ላይ የሚካሄደውን ቁጥጥር ሊያግዝ ይችላል፡፡ ነገር ግን የችግሩ መንስዔ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ የሕመሙ ምልክት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ደግሞ እኛ ትኩረት የምናደርገው ከሥር ከመሠረት ካለ ችግሩ ላይ ሳይሆን ምልክቱ ላይ ነው፡፡ ይህ እንደ አንድ ችግር ሊታይ ይችላል፡፡ በአሁኑ አዋጅ አዲስ አካሄድ ነው ሊባል የሚችለውና ትንሽ ለየት የሚያደርገው በረቂቅ አዋጁ ላይ በባለድርሻ አካላት ከሌላው ጊዜ የተሻለ ተሳትፎ አይቼበታለሁ፡፡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ በቀረበበት ወቅት የተሻለ ውይይቶች የተደረገ በመሆናቸው የተወሰነ ለውጥ ይመጣል ብዬ ባስብም ጉዳዩ ብዙ ሥራ ይቀረዋል፡፡ ራሱ አዋጁም ቢሆን አሁንም ብዙ ክፍተቶች አሉበት፡፡
ሪፖርተር፡- እንደ ክፍተት ያዩት ምንድነው?
ዶ/ር ሰርካለም፡- ብዙ ጊዜ እኛ አገር እንዲህ ዓይነት ነገር ስትጀምር የባለድርሻ አካላትን በአግባቡ ያለ ማማከር ክፍተት አለ፡፡ ይህም አዋጅ ከዚያ የፀዳ አይደለም፡፡ ምክንያቱም እጅግ በጣም ብዙ ችግር አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- አለ የሚሉኝን ክፍተቶች ምሳሌ ቢጠቅሱልኝ?
ዶ/ር ሰርካለም፡- አንዱ የቃላት ትርጓሜን ‹‹Definition of Terms›› የተመለከተ ነው፡፡ በኢንዱስትሪው የተለመዱ ቃላት ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ነዳጅ አዳዮች (Delears) ይባሉ፡፡ ይህ በዚያው ቢቀጥል የተሻለ ነበር፡፡ ከማደያ ወስደው የሚቸረችሩት ቸርቻሪ (Resalers) ይባሉ ነበር፡፡ ይህንን በአዋጁ አላየሁም፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ አዋጁ በጥቅል ሲታይ ከበፊቱ የተሻለ ቢሆንም፣ ከባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ባሻገር ባለሙያዎች አዋጁን በማርቀቅና ሙያዊ ምልከታቸውን እንዲያሰሙ አለመደረጉም እንደ ክፍተት የሚታይ ነው፡፡ በረቂቅ አዋጁ የውይይት መድረክ ላይ የነበሩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በአዋጁ ላይ ሲሰጡ የነበረው አስተያየት ከራሳቸው ፍላጎት ጋር የተያያዘ ስለሚሆን፣ የባለሙያዎች ምክረ ሐሳብ ተገቢ ቦታ ሊሰጠው ይገባ ነበር፡፡ በውይይቱ ላይ እንደታዘብኩትም ብዙዎቹ ባለድርሻ አካላት በአዋጁ ላይ አስተያየት ሲሰጡ ከራሳቸው ጥቅም አንፃር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሚዛናዊ ላይሆን ይችላል፡፡ የባለሙያዎች አስተያየት ምልከታ ግን ከዕውቀት፣ ከልምድና ከመሳሰሉ ነገሮች ጋር የተገናኘ ስለሚሆን ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች ሊሰጡ ይችሉ ነበር፡፡ አዋጁን ሊያዳብሩት ይችሉ ነበር፡፡ አዋጁ የባለሙያዎች አስተያየት በተገቢው መንገድ የተሰጠበት ባለመሆኑ እንደ አንድ ክፍተት ሊታይ ይችላል፡፡ ሌላው በዚህ አዋጅ ውስጥ እንዲካተት የተደረገው ዴፖን በተመለከተ የተቀመጠ ነገር አለ፡፡ አንድ የነዳጅ ኩባንያን ለማቋቋም 500 ሺሕ ሊትር የሚይዝ ዴፖ ያስፈልጋል ይላል፡፡ ይህ ብዙም ነው፣ ብዙም አይደለም፡፡ ከምን ተነስቶ ነው 500 ሺሕ ሊትር ማድረግ የተፈለገው የሚለው ግልጽ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም የነበረው ሕግ ላይም እኮ አንድ የነዳጅ ኩባንያ 500 ሺሕ ሊትር ነዳጅ ሊይዝ የሚችል ዴፖ ሊኖረው ይገባል ይላል፡፡
ዶ/ር ሰርካለም፡– አዎ፣ የዛሬ አሥር ዓመትም የወጣው ሕግ ላይ 500 ሺሕ ሊትር ነው የሚለው፡፡ የዚያን ጊዜም ሐሳብ የሰጠንበት ቢሆንም ማስተካከያ ሳይደረግበት ነው ሕጉ የወጣው፡፡
ሪፖርተር፡- ከአሥር ዓመት በፊት ሕጉ ሲወጣ አንድ ነዳጅ ኩባንያ ለማቋቋምና ፈቃድ ለማግኘት 500 ሺሕ ሊትር የመያዝ አቅም ያለው ዴፖ ሊኖረው ይገባል የተባለው በወቅቱ ከነበረው የነዳጅ ፍላጎት ጋር ለማጣጣም ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ከአሥር ዓመታት በኋላ ሕጉ ሲሻሻልም በዚያው መጠን መቀጠል የለበትም ከሚል መነሻ ነው የተጠቀሰው መጠን ላይ የማይስማሙት?
ዶ/ር ሰርካለም፡- አዎ፣ አንደኛ የነዳጅ ፍላጎት እየጨመረ ስለሚሄድ ነው፡፡ ዴፖን በተመለከተ አዋጁ ሁለተኛ የጎበዝ መንገድ የለውም፡፡
ሪፖርተር፡- የጎበዝ መንገድ የለውም ሲሉ?
ዶ/ር ሰርካለም፡- የጎበዝ መንገድ የለውም ያልኩበት ምክንያት፣ አሁን ካሉት የነዳጅ ኩባንያዎች ኦይል ሊቢያ ወይም ቶታል እስከ አምስትና አሥር ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ የማከማቸት አቅም አላቸው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች 500 ሺሕ ሊትር ይዘው ቁጭ ሊሉ ነው ማለት ነው፡፡ የማይጠቀሙበት አቅም ይኖራቸዋል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ነዳጅ ስትይዝ ብዙ ካፒታል ይይዝብሃል፡፡ የነዳጅ ትነትና የመሳሰሉ ነገሮችም ስላሉ ቢዝነሱ ከባድ አደጋ አለው፡፡ በክምችት መጠን የኢንሹራንስ ዓረቦን (ፕሪሚየም) ይጨምርብሃል፡፡ እንዲህ ያሉ አንድንድ ነገሮችን ስታይ ብዙ ነዳጅ መያዝ አይመከርም፡፡ 500 ሺሕ ሊትር ነዳጅ ዴፖ መያዝ ላይ ግትር ከማለት አዋጁ መንገድ መስጠት ነበረበት ብዬ የማምነው፣ ሌሎች አማራጮችን እንዲኖሩ ዕድሎችን መስጠት ነበረበት፡፡ ይህ ማለት በቂ ዴፖ የሌለው ኩባንያ የትልልቅ ኩባንያዎችን ዴፖ በኪራይ እንዲጠቀም ማድረግ ነው፡፡ እንዲህ ያለ አሠራር አለ፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት ሱሉልታ ከሚገኝ የነዳጅ ኩባንያ ጋር በመዋዋል ዴፖውን ለቤንዚንና ለኢታሎን ማደባለቂያነት ይጠቀማሉ፡፡ ይህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ በመሆኑም እንዲህ ያሉ ነገሮችን ክፍት በማድረግ አገልግሎት አሰጣጣችን ላይ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ አሠራሮች ታሳቢ ተደርገው በአዋጁ ቢካተቱ የተሻለ ነበር፡፡ ዴፖ ራሱን የቻለ ቢዝነስ ነው፡፡ 59 የነዳጅ ኩባንያዎች 500 ሺሕ ሊትር የመያዝ አቅም ያለው ዴፖ ይኑራቸው ከሚባል፣ የዴፖ ሥራ ብቻ መሥራት የሚቻልበት ሌላ አሠራር ማየትም ይቻላል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ክፍተቶች አሉት ብዬ አስባለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ ፈጣን በሚባል ሁኔታ የነዳጅ ኩባንያዎች ቁጥር 59 ደርሷል፡፡ ከእነዚህ ኩባንያዎች ውስጥ 80 በመቶውን የገበያ ድርሻ የያዙት ግን አራትና አምስት ኩባንያዎች ናቸው፡፡ በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት ሲደረግ እንደተሰማው መብዛታቸው ጥቅም እየሰጠ አለመሆኑን ነው፡፡ እንዲሁም አንዳንዶች ወደ እዚህ ሥራ የገቡበት ምክንያት በነዳጅ ግብይት ሠርተው ለማትረፍ ሳይሆን፣ ከባንክ ብድር ለማግኘት በማሰብ ፈቃዱን እንደሚወስዱ ይነገራል፡፡ እርስዎ ይህንን ሐሳብ እንዴት ያዩታል? በዚህን ያህል ደረጃ መብዛታቸውስ ጥቅም አለው?
ዶ/ር ሰርካለም፡- የነዳጅ ማደያ ቢዝነስ ተለይቶ ሊጋነን የሚችል ቢዝነስ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ እንደ ሌሎች ቢዝነሶች እኩል ነው መታየት ያለበት፡፡ በኢኮኖሚክስም ይታወቃል፡፡ ብዙ ጊዜ ብዙውን የገበያ ድርሻ የሚወስዱት ሰዎች ጥቂት ናቸው፡፡ 80/20 የሚባል ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ በዓለም ላይ 80 በመቶ የሚሆነው ሀብት ሃያ በመቶ በማይሞሉ ሰዎች ነው የተያዘው፡፡ በእኛም አገር የነዳጅ ግብይት ውስጥ ትልቁን የገበያ ድርሻ የያዙት ኖክ፣ ኦይል ሊቢያና ቶታል ናቸው፡፡ ይህ እንግዲህ ከመቆየትና ከመሳሰሉት ምክንያቶች የመጣ ነው፡፡ በእኔ በኩል የኩባንያዎቹ መብዛት ችግር አለው ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም በጣም በቀላሉ ሊደረስባቸው የማይችሉ ቦታዎች አሉ፣ እነዚህ አዳዲሶቹ በተሻለ ይህንን ክፍተት ለመድፈን ይቀድማሉ፡፡ ኩባንያዎች እየተፈጠሩ ያሉት ለባንክ ብድር ማግኛ ነው የተባለውን ግን አላምንምበትም፡፡ ባንኮች ሥራቸው አትራፊ ነው እስካሉ ድረስ ከሰጧቸው ምንም ችግር የለውም፣ ይሁን ይስጧቸው፡፡ ይህ የባንክ ጉዳይ ነው፣ የእኛ ጉዳይ አይደለም፡፡ ከሕዝብ የተሰበሰበ ገንዘብን ዝም ብሎ አልባሌ ቦታ ተበትኖ እንዲጠፋ ባናበረታታም ባንኮቹ አዋጭ ነው ብለው ብድሩን እስከሰጡ ድረስ እሱ የእኛ ራስ ምታት ሊሆን አይገባም፡፡
ሪፖርተር፡- ተበድረውም ሥራውን በአግባቡ እየሠሩ አይደለም ነው እየተባለ ያለው፡፡ ነዳጅ በዱቤ ወስደው ክፍያ ያልፈጸሙ ሁሉ አሉ መባሉስ?
ዶ/ር ሰርካለም፡- ችግሩ እሱ ላይ ነው፣ ይህ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል፡፡ ይህ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሥራ ነው፡፡ እንዲያውም በእዚህ አዋጅ እርስ በርስ የሚጋጨው ነገር የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና የአዲሱ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ሥራ ግልጽ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ግን 130 ሚሊዮን ሕዝብ ላላት አገር 59 ኩባንያዎች ብዙ አይደለም፡፡ እዚህ ጎረቤት አገር 200 እና 300 የነዳጅ ኩባንያዎች አሉ፡፡ ይህ አነጋጋሪ ጉዳይ ሊሆን አይገባም፡፡ ዋናው አነጋጋሪ ጉዳዩ መሆን ያለበት ኩባንያዎቹ የነዳጅ አቅርቦት ሥራውን በአግባቡ እየተወጡ ነው ወይ የሚለው ነው፡፡ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እንዴት ነው ሊታገዙ የሚገባው መሆን አለበት፡፡ ዋናው ነገር ሁሉም ብቁ ኩባንያዎች ሆነው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማሰብና መሥራት ነው፡፡ ሦስትና አራት ኩባንያዎች ወደ አንድ የሚመጡበትን ነገር ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ማበረታቻዎችን በመፍጠር ማስኬድ ይቻላል፡፡ ተዋህደው የሚመጡትን ኩባንያዎች እንዲህ ያለ ማበረታቻ እንሰጣለን ሊባልም ይችላል፡፡ ለምሳሌ ለዚህን ያህል ቀን የሚወስዱትን ነዳጅ በክሬዲት እንሰጣለን የሚሉና ሌሎች ማበረታቻዎችን እየሰጡ ጠንካራ ኩባንያዎች እንዲፈጥሩ የማድረግ አሠራር መዘርጋትም፣ እንደ አንድ መፍትሔ መታሰብ ይኖርበታል፡፡ በረዥም ጊዜ የነዳጅ ፍላጎት እየጨመረ ነው የሚሄደው፡፡ ፍላጎት እንዲጨምር አይፈለግም አይባልም፡፡ ፍላጎት እንዲጨምር ስላልፈለግክ አይደለም የሚጨምረው፣ ይህ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ አገር ሲያድግና የሕዝብ ቁጥጥር ሲጨምር ፍላጎትም ይጨምራል፡፡ ፍላጎቱ እያደገም ቢሆን ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ግን ይቻላል፣ አስፈላጊም ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ ባለፉት ሦስት ዓመታት በዚህን ያህል ደረጃ የነዳጅ ኩባንያዎች መብዛት ግን ከምን የመጣ ነው ይላሉ?
ዶ/ር ሰርካለም፡- የኩባንያዎቹ መብዛት ዋና ምክንያቱ በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አካባቢ የላላ የቁጥጥር ሥርዓት ስለነበር ነው፡፡ ድርጅቱ የትኛውም ነዳጅ ኩባንያ ሲመጣ በ30 ቀናት ነዳጅ በዱቤ ይሰጥ ነበር፡፡ በእነዚያ 30 ቀናት እንደፈለጉ ነዳጅ አውጥተው ይሸጡና አራጣ ሊያበድሩት ይችላሉ፡፡ ወደ ሌላ ኢንቨስትመንት የሚያዘዋውሩትም አሉ፡፡ ከአገር የሚጠፉም አለ፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ችግር የነበረው ከአቅራቢው በኩል ነው፡፡ አሁንም ሁሉ ነገር የሚሽከረከረው ከአቅራቢው በኩል ነው፡፡ እንዲያውም የዚያን ጊዜ እጥረት ሲፈጠር እልል ነበር የሚባለው፡፡ ምክንያቱም የነዳጅ እጥረቱ ስላለ ከጂቡቲ ወይም ከሱዳን የሚመጣ ነዳጅ ስለሚዘገይ መንግሥት የነዳጅ እጥረቱ ችግር እንዳይኖር በሚል ከኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት መጠባበቂያ፣ የነዳጅ ኩባንያዎች ወስደው እንዲያሠራጩ ያደርጋል፡፡ ሁሉም ኩባንያዎች ከመጠባበቂያው ነዳጅ ይወስዱና ገንዘቡን ለመሰብሰብ ችግር ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ብዙዎቻችን ከልጅነት ጀምሮ የነዳጅ እጥረት ተፈጠረ፣ ነዳጅ ጠፋ የሚል መረጃ እየሰማን ነው ያደግነው፡፡ አሁንም ወቅት እየጠበቀ ይኸው ‹‹ነዳጅ ጠፋ›› የሚለው ነገር አላቆመም፡፡ የተለመደ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ከሰሞኑም ይህንኑ እየሰማንና እያየን ነው፡፡ ለሰሞኑ እጥረትም ሆነ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የሚፈጠረው የነዳጅ እጥረት ሲያጋጥም መንግሥት የተለያዩ ምክንያቶችን ይሰጣል፡፡ በማደያዎች ላይ ይሳበባል፣ የነዳጅ ኩባንያዎችና አጓጓዦችም የችግሩ መንስዔ ስለመሆናቸው ይጠቀሳል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ችግሩ ተደጋግሞ የሚፈጠረው ቆንጣጭ ሕግ ስለሌለ እንጂ ነዳጅ ጠፍቶ አይደለም ይባላል፡፡ እንዲህ ያሉ ለዘመናት ሲባሉ ለነበሩ ሰበቦችና አጠቃላይ የነዳጅ እጥረትና ተያያዥ ችግሮችን አዲሱ የነዳጅ ግብይት አዋጅ መፍትሔ ይሰጣል? ብዙ ሕጎች በወረቀት ላይ እጅግ በጣም ጥሩ የመሆናቸውን ያህል በተግባር ግን የማይገለጹ ናቸው ስለሚባል አዋጁ በተሻለ ደረጃ ተዘጋጅቷል የሚባለውን ያህል በአግባቡ ተፈጻሚ ለመሆኑ ምን ያህል እርግጠኛ መሆን ይቻላል?
ዶ/ር ሰርካለም፡- ዋናው ችግር ይህ ነው፡፡ ከዚህም በፊትም ሕግ ነበር፡፡ አሁንም ሕጉ ተሻሽሎ ወጥቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ሕጉን ልናሻሽለው እንችላለን፡፡ ችግሩ ሕግ አለመኖሩ አይደለም፡፡ የሕግ ማስከበርና የፍትሕ አለመኖር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ደጋግሜ እንደምለው የሕግ ማስከበር የለም፡፡ በነገራችን ላይ በኮንትሮባንድ የሚወጣውን ነዳጅን በተመለከተ የተካሄዱ ጥናቶች ቁልጭ አድርገው አስቀምጠዋል፡፡ ችግሩ የትና ማን ዘንድ እንዳለ በደንብ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ከለውጡ በፊት እነዚህ ችግሮች ተለይተው በዝርዝር የቀረበው ጥናት ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ይላክ ሲባል ነው የቆመው፡፡ ስለዚህ በዘርፉ ያለው አንዱና ዋነኛው የሕግ ማስከበር ችግር ነው፡፡ ትልቁ ችግር የነዳጅ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችም በዚህ ጉዳይ ውስጥ አሉ፡፡ ከዚያም ደረጃ በደረጃ ትራንስፖርተሮችም እንደ ችግር ፈጣሪ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ስለዚህ አሁን የሕግ መኖርና አለመኖር ሳይሆን ሕጉ ቀድሞም ያለ ነው፡፡ ትልቁ ችግር ያለው የመንግሥት ቁርጠኝነትና ሕግ ማስከበር ላይ በጣም ክፍተት መኖሩ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በመንግሥት ደረጃ እየተነገረ ያለው በነዳጅ ግብይት ሥርዓት ውስጥ ያለውን ችግር ተቆጣጥሮ ዕርምጃ ለመውሰድ ሥራ ላይ የነበረው ሕግ ጠበቅ ያለ አልነበረም የሚል ነው፡፡ በአዲሱ አዋጅ ግን ሕገወጥ ተግባር በወንጀል የሚያስጠይቅ ስለሚሆን የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት አለ፡፡ በሌላ በኩል ቅጣቱ ኩባንያዎችን እስከ ማገድና ተሽከርካሪዎችንም ከሥራ ውጪ የማድረግ ድረስ ከሆነ፣ እንዲህ ያለው ዕርምጃ በሥራ ላይ ሌላ ተፅዕኖ አይፈጥርም? ለምሳሌ ተሽከርካሪዎችን ሲታገዱ አቅርቦት ላይ ችግር በመፍጠር የነዳጅ እጥረት አያስከትልም?
ዶ/ር ሰርካለም፡- ነገሩን ከአንድ አቅጣጫ ብቻ ማየት የለብንም፡፡ ወንጀልን የሚያበራክቱ ነገሮችን ከሥር መሠረት ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ‹‹ካሊቢሬሽን›› ላይ ያለ ችግር እስከ ዛሬ ትልቅ ራስ ምታት ለምን እንደሚሆን አይገባኝም፡፡ ከዚያ በፊት ኪሎ ሜትር ይጨመር ‹‹ጂፒኤስ›› ይግባ ይባላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ‹‹ጂፒኤስ›› ይግባ ሲባል ለእኔ ያን ያህል ጠቃሚ አይደለም፡፡ ከ‹‹ጂፒኤሱ›› ይልቅ ኪሎ ሜትር ነው የበለጠ መፍትሔ የሚሰጠው፡፡ ኪሎ ሜትር የትም አገር የሚሠራበት ነው፡፡ በኪሎ ሜትርም ቢሆን ጥፋት አይሠራም ማለት አይደለም፡፡ ግን በስፋት ችግሩን ይቀንሳል፡፡ የካሊብሬሽን ጉዳይም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ፓምፑ ላይ ማጭርበሪያ ሊሠራለት ይችላል፡፡ አንድ ሊትር እንዲሸጥ ተደርጎ የደረጃ መዳቢ ወይም ለሥራው ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ይገጥምለታል፡፡ ከዚያ በኋላ ማደያው ከደረጃ መዳቢ ሠራተኞች ጋር በመሻረክ አሠራሩን ሊያዛባው ይችላል፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች ሲያጋጥሙ ቴክኒካዊ ነገር ላይ ጭምር አጠንክረህ በመሥራት ጭምር ነው ችግሩን ልትቀንስ የምትችለው፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ያሉና ሌሎች ነገሮች አንድ ላይ ሆነው ነው ይህን ነገር ማስታገስ የሚቻለው፡፡ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት አይቻልም፡፡ ከነዳጅ ጋር በተያያዘ ያሉ ማጭበርበሮችን መቀነስ ይቻላል እንጂ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አይቻልም፡፡ ስለዚህ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ኖራቸው ከሠሩ ችግሩን በጣም መቀነስ ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- የነዳጅ ሥርጭትንና ፍትሐዊነትን በተመለከተ የክልል የንግድ ቢሮዎች ቀዳሚ ጥያቄ አድርገው ሲያቀርቡት የነበረው ሊደርሳቸው የሚገባው ነዳጅ በአግባቡ እየደረሳቸው አለመሆኑን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ የነዳጅ ማደያዎች ሥራ ላይ የማይሆኑበት ጊዜ የሚበዛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እንዲሁም በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የነዳጅ ፍጆታ ይታወቃል? የሥርጭቱ አትራፊነትስ እንዴት የሚታይ ነው?
ዶ/ር ሰርካለም፡- አንዱ ችግር ይህ ነው፡፡ ከነዳጅ ፍላጎት ጋር በተያያዘ የሚኖሩ ትንበያዎች ላይ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የራሱን ነው የሚሠራው፡፡ ዓምና አንድ ሚሊዮን ሊትር ከተሸጠ በቀጣዩ ዓመት የነዳጅ ፍላጎቱ በ15 እና 17 በመቶ ያድጋል ስለሚል በዚያ ሥሌት ነው የሚሠራው፡፡ መሆን ያለበት የግብይትና የአቅርቦት ሥርዓቱ ከላይ እስከ ታች በዕቅድ ተጀምሮ መሥራት ነው፡፡ ለምሳሌ የነዳጅ ኩባንያዎች በተለይ በዓመት ይህንን ያህል የነዳጅ ፍላጎት ይኖረናል የሚለውን መረጃ እንዲሰበሰቡ ማድረግ አንዱ ነው፡፡ ነዳጅ ኩባንያዎቹ መረጃዎቹን ሲሰበስቡ ማንን ያማክራሉ? በየክልሉ ያሉ ነዳጅ ማደያዎችን ነው፡፡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ዓመታዊ የነዳጅ ሒደት መሰብሰብ ያስፈልጋል፡፡ እኛ ድሮ ስንሠራ ያለፈውን ዓመት ሒደት እንወስድና አዲስ ማደያዎች ይኖራሉ ብለን እናስባለን፡፡ አዳዲስ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ካሉም የእነሱን ፍላጎት ታሳቢ እናደርጋለን፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ለዕቅድ ትልቁ ምንጫችን ነበር፡፡ ነዳጅን ብቻ ሳይሆን የአስፋልት ፍላጎት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በቀጣዩ ዓመት ይህንን ያህል መንገዶችን ለመገንባት ጨረታ ያወጣል የሚለውን ሁሉ መረጃ በማሰባሰብ ግምት እንይዛለን፡፡ ልክ እንደዚህ ሁሉ አሁንም የነዳጅ ኩባንያዎቹን ያካተተ የመረጃ አሰባሰብ ቢተገበር፣ ሁሌም የነዳጅ ፍላጎታችንን ለማወቅም ሆነ ለመተንበይ በጣም ቀላል ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትም ከተለመደው አሠራር መውጣት አለበት፡፡ ይህንን ዲዛይን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ውስጥ የነዳጅ ኩባንያዎች፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፣ የክልል ንግድ ቢሮዎችና ሌሎችንም አካቶ ዓመታዊ የነዳጅ ሒደቱን መረጃ በመሰብሰብ መሥራት ይቻላል፡፡ ነገር ግን አሁንም ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ስላለ በየክልሉ ምን ያህል ነዳጅ ፍጆታ አላቸው የሚለውን ለማወቅ ነው የሚያስቸግረው፡፡
ሪፖርተር፡- ተደጋጋሚ የነዳጅ እጥረት የሚፈጠረው ከጥቅል አቅርቦት እጥረት ጋር ነው ብለውኛል፡፡ ሰሞኑን ከተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ጋር ተያይዞ ባለሥልጣኑ እንደገለጸው ደግሞ፣ እጥረቱ ሰው ሠራሽ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በየማደያዎቹ ቺፕስ እንገጥማለን፣ ጂፒኤሶችንም በመግጠም የነዳጅ ግብይቱን በአንድ ማዕከል ውስጥ እንቆጣጠራለንም ብሏል፡፡ ይህ ምን ያህል ለውጥ ያመጣል? የሌሎች አገሮች የነዳጅ ግብይት እንዴት ነው የሚካሄደው?
ዶ/ር ሰርካለም፡- በሌሎች አገሮች ይህ ጉዳይ ብዙ አሳሳቢ አይደለም፡፡ ጥያቄው ከብዙ ነገሮች ጋር ይያያዛል፡፡ ባላደጉና የነዳጅ አቅርቦት ችግር በሆነባቸው አገሮች ውስጥ ተመሳሳይ ችግር አለ፡፡ ያደጉ አገሮች ውስጥ ይህ ችግር አይደለም፡፡ ለነዳጅ አቅርቦት በጣም ቀላል አሠራር አላቸው፡፡ ከዚያ የበለጠ ትኩረት የሚሰጠው ለደኅንነት ነው፡፡ ቅድም እንዳልኩህ በእኛ አገር ትልቅ ችግር ሲከሰት ነው የምንሰበስበው፡፡ ችግሩ ሲመጣ ሳይሆን ማሰብ ያለብን ሳይደርስ ነው፣ አደጋውን በጣም ለመቀነስ፡፡
ሪፖርተር፡- አዲሱ የነዳጅ ግብይት አዋጅ አዳዲስ ድንጋጌዎች ተካተውበታል፡፡ ለምሳሌ ከፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተያዘ አዳዲስ አሠራሮች አሉ፡፡ ወደ ዘርፉ ለመግባት የተለያዩ የብቃት ማረጋገጫዎች እንደሚያስፈልጉም ተደንግጓል፡፡ አዋጁ ውስጥ ያሉ ድንጋጌዎችን እንዴት ያያሉ? ሕገወጥ ግብይት የሚለው ጉዳይ ሲያከራከርም ይሰማል፡፡
ዶ/ር ሰርካለም፡- አዋጁ ውስጥ ካየናቸው ድንጋጌዎች ውስጥ እንደ ክፍተት ሊታዩ ከሚችሉት አንዱ፣ ለምሳሌ አሁን የኮንስትራክሽንን ሥራ ፈቃድ በነዳጅ ባለሥልጣን ሊሰጥ አይገባም፡፡ የኮንስትራክሽን ፈቃድ የሚሰጠው ከኮንስትራክሽን ሥራ ጋር ግንኙነት ባለው አካል ነው፡፡ ባለሥልጣኑ ሊሰጥ የሚገባው የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ነው፡፡ የብቃት ማረጋገጫ ነው፡፡ ለምሳሌ እነሱ የደረጃ ምደባ ያወጡና በዚያ መሠረት ለመሠራቱ የሰርቲፊኬሽን ፈቃድ ማየት ነው እንጂ፣ የኮንስትራክሽን ፈቃድ ውስጥ መግባት የለባቸውም ባይ ነኝ፡፡ ሁለተኛ የነዳጅ ማደያ መገንባት ይህንን ያህል ስፔስ ሳይንስ አይደለም፡፡ እንደ ማንኛውም የግንባታ ፈቃድ የሚታይ ነው፡፡ ሁሉንም ነገሮች ከባድ ማድረግ አይጠበቅብንም፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች በመመርያና በመሳሰሉት ሊገለጹ ይችላል፡፡ አዋጁ ብዙ ጊዜ ዋና ዋና ነገሮችን ያስቀምጣል እንጂ ዝርዝር ጉዳዮችን ላይገልጽ ይችላል፡፡ ሕገወጥ የነዳጅ ግብይት ግን ግልጽ ነው፡፡ ሕጋዊና ሕገወጥ ነገሮች ይታወቃሉ፡፡ ሕገወጥ የነዳጅ ግብይት አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ይህም ፈቃድ የሌለው ሰው ነዳጅ በብዛት ከማደያ ሲቀዳ ፈቃድ የሌለው ሰው በበርሜል ነዳጅ ቀድቶ ከሄደ ሕገወጥ ነው፡፡ ሁለተኛው ከኢትዮጵያ ድንበር ውጪ ወደ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ በኮንትሮባንድ ነዳጅ ማስወጣት ሕገወጥ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ ተደጉሞ የሚቀርብ ምርት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ምርት በየትኛውም መንገድ ኬላ አሳልፈህ ማጓጓዝ ሕገወጥ ነው፡፡ ሌላው ሕገወጥ የነዳጅ ግብይት የሚባለው ነዳጅን ቀላቅሎ መሸጥ ነው፡፡ በነዳጅ ግብይት ውስጥ በሕገወጥነት የሚጠቀሰው ‹‹ፓምፓር›› ማድረግ ነው፡፡ አንድ ሊትር እንዲሰጥ የተደረገ መሣሪያን 0.98 ሊትር ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ 0.98 ሊትር እንዲሰጥ ተደርጎ እንዲሠራ በማድረግ 00.2 ሊትር በእያንዳንዱ ሊትር ይሰረቃል ማለት ነው፡፡ ይህም ሕገወጥ የነዳጅ ግብይት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች ናቸው ሕገወጥ የነዳጅ ግብይት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የብዙ አሽከርካሪዎች እሮሮ አሁን የጠቀሱልኝ ነገር ነው፡፡ ብዙ ማደያዎች የነዳጅ መቅጃ መሣሪያዎች እንዲህ ላለው ያልተገባ ተግባር የተዘጋጁ ናቸው ይባላል፡፡ አሽከርካሪዎች አንድ ሊትር ተብሎ የሚቀዳላቸውን ነዳጅ በትክክል አንድ ሊትር መሆኑን የሚለዩበት መንገድ ስለሌለ እርስዎ እንዳሉት ይቀሸባሉ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሕገወጥ ድርጊት እየተስፋፋም ነው ይባላልና መፍትሔው ምንድነው?
ዶ/ር ሠርካለም፡- ማጭበርበሩን መቀነስ ይቻላል፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ ችግር አንዱና በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው ሙስና ነው፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ከደረጃ መዳቢ መሥሪያ ቤት መጥተው ፓምፕ የሚያደርጉ፣ የነዳጅ ማደያ ሠራተኞችና በአብዛኛው ባለቤቶች ናቸው፡፡ እንዲህ ያለው ሕገወጥ ተግባር የሚፈጸመው ሰው በሌለበት በሌሊት ነው፡፡ ስለዚህ ነገሩ በጣም ከባድ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ማደያ ላይ ደግሞ ካሜራ መግጠም አትችልም፡፡
ሪፖርተር፡- በአዲሱ አዋጅ ረቂቅ ውይይት ላይ ሊሆን ይገባል ተብለው ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ የአገሪቱ የነዳጅ ግዥ እየተፈጸመ ያለው በመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት ቢሆንም፣ ነገር ግን የነዳጅ ግዥው ሒደት በግል ኩባንያዎች በኩል መፈጸም ይኖርበታል የሚል አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ ይህ ግን ይቻላል? እንደተባለው ጥቅም ይኖረዋል? በተለይ በአሁኑ ወቅት ነዳጅ በገበያ ዋጋ ይገበያል ከተባለ የግል ኩባንያዎች ቢሳተፉበት ችግር ላይኖረው ይችላል የሚለውስ ሐሳብ ምን ያህል ውኃ ያነሳል?
ዶ/ር ሰርካለም፡- አሁን ባለው ሁኔታ ይህ በፍፁም የሚታሰብ ነገር አይደለም፡፡ እኔም የግል ኩባንያዎች የነዳጅ ግዥው ውስጥ ይግቡ ሲባል እሰማለሁ፡፡ የነዳጅ ኩባንያዎች ራሳቸው ነዳጅ እንዲያመጡ ይፈቀድላቸው የሚሉም አሉ፣ ይህ አይሆንም፡፡ የትኛው ኩባንያ ነው በዶላር ነዳጅ ገዝቶ ማስገባት የሚችለው? ዶላሩን ከየት ያገኛል? ሁለተኛ በዶላር ገዝቶ አምጥቶ በብር ሰብስቦ እንደገና በዶላር ቀይሮ እንዴትስ አድርጎ ያወጣል? ለግዥ የሚጠየቀው የውጭ ምንዛሪ በጣም ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ነገር አሁን የሚታሰብ አይደለም፡፡ የነዳጅ የአቅርቦት ሰንሰለትን በተመለከተ ኢትዮጵያና ግብፅ ከበፊት ጀምሮ ግብይቱን የተቆጣጠሩት መንግሥታቻው ግብይቱን ስለሚቆጣጠረው ነው፡፡ ይህ ባይሆን የገበያ ትርምስ ይፈጠራል፡፡ የግል ኩባንያዎች በዚህ ሥራ ይግቡ ቢባል አንድ ወር ማቅረብ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም የግል ኩባንያዎች ዋና ግባቸው ትርፍ ስለሚሆን ሲያዋጣቸው ያመጣሉ፣ ሳያዋጣቸው ደግሞ ንክች አያደርጉም አያመጡም፡፡ ዋጋውን ከፍ ለማድረግ አርቴፊሻል ነገር ይፈጥራሉ፡፡ መንግሥት ግን ነዳጅ ለሕዝብ የሚቀርብ ወሳኝ ምርት በመሆኑ ኃላፊነቱን ይወስዳል፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ነዳጅ የሕዝብ ጉዳይ ነው የሚባለው፣ ምክንያቱም መንግሥት ስለሚቆጣጠረው፡፡ ነገር ግን መንግሥት ከተቆጣጠረው ወደ ግል ዘርፉ ከሄደ በጣም ለማጭበርበር ስለሚጋለጥ ነው፡፡ ይህ እኮ ለግል ዘርፉ ሥራውን ሰጥተኸው ነዳጅ ባያመጣ እንዴት ነው የምንንቀሳቀሰው? ስለዚህ ነዳጅን የግሉ ዘርፍ እንዲያስመጣ ሐሳብ ቢነሳም አሁን ባለው ሁኔታ መተግበር የማይታሰብ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የነዳጅ ዋጋ ሄዶ በሊትር መናር ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ትርጉም አለው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ የነዳጅ ዋጋ እያሻቀበ ከመቶ ብር በላይ ደርሷል፡፡ በአጠቃላይ ከነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችለውን ጫና እንዴት ማርገብ ይቻላል ብለው ያምናሉ? በሒደት መንግሥት ከነዳጅ ድጎማ እጁን ሊያወጣ ቢችልስ?
ዶ/ር ሰርካለም፡- መንግሥት ከነዳጅ ድጎማ እጁን ያወጣል ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ፣ ይህንን ዕርምጃ እንደማልስማማበት በተለያዩ መንገዶች ገልጫለሁ፡፡ አሁንም መንግሥት ከነዳጅ ድጎማው ይውጣ በሚለው ሐሳብ አልስማማም፡፡ መንግሥት ከነዳጅ ድጎማ እጁን ማውጣቱ ብዙ ተፅዕኖዎች አሉት፡፡ በኢኮኖሚክስ ‹‹Spillover Effect›› ይባላል፡፡ ይህ ማለት ነዳጅ ላይ አንዲት ሳንቲም ጨመርክ ማለት ሁሉም ነገር ላይ ይዛመታል፡፡ የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ከሌሎች ዕቃዎች ጋር አይገናኝም የሚሉት ነገር ይገርመኛል፡፡ ነዳጅ ሲጨምር ትራንስፖርት ይጨምራል፡፡ ትራንስፖርት ጨመረ ማለት እያንዳንዱ የምንጠቀምበት ዕቃ ላይ የዋጋ ለውጥ ያመጣል ማለት ነው፡፡ ዕቃዎች የሚመጡት ከውጭ እንደመሆኑ የእነዚህ ዕቃዎች የማጓጓዣ ዋጋ ይጨምራል፡፡ ይህ ጭማሪ ኅብረተሰቡ ላይ ነው የሚያርፈው፡፡ የሕዝብ ትራንስፖርትንም ከወሰድክ በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት የትርፍ ለውጥ ስለሚደረግ በተለይ የወር ደመወዝተኛ ላልተጠበቀ ወጪ ይዳረጋል፡፡ ይህ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ በረዥም ጊዜ መንግሥት እንደገና የድጎማን ጉዳይ ተመልሶ ሊያየው ይገባል እንጂ፣ ተወው ማለት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡ የዋጋ ንረቱንም ያባብሳል፡፡ በእርግጥ ከዚህ በኋላም የዓለም የነዳጅ ዋጋ ይቀንሳል ተብሎ ባይታሰብም፣ ክፍተቱን የሚሟላበት የፈንድ ዘዴ አዘጋጅቶ ድጎማው ሊቀጥል ይገባል፡፡ ነዳጅ ሲጨምርና ሲቀንስ ከፈንዱ ላይ በመውሰድ መደጎም ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ከሁሉም ነገር በላይ ቅድሚያ ሰጥቶ የኢኮኖሚ ጫናውን ለመቀነስ የነዳጅ ድጎማውን መቀጠል ይኖርበታል፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ አዲሱ የነዳጅ ግብይት አዋጅ ልመልስዎ ነው፡፡ በአዋጁ በነዳጅ ግብይት ሒደት ውስጥ በቀጥታ የተለያዩ ኃላፊነት አለባቸው ተብለው የሚጠቀሱ እንደ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን፣ የክልል ንግድ ቢሮዎችና የመሳሰሉት አሉ፡፡ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ሚናም የተደበላለቀ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ለምሳሌ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በዚህ አዋጅ የተሰጠው ኃላፊነት ምንድነው? የትራንስፖት ሥራ ደርቤ እንድሠራ በጀት ሊመደብልኝ ይገባል እስከማለት መድረሱ ምን ያሳያል?
ዶ/ር ሰርካለም፡- ከደንቦችና ከኃላፊነት አኳያ ግራ መጋባቶች አሉ፡፡ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የሚባለውን ተቋም ማቋቋም ያስፈለገው ለምንድነው? የሚል ጥያቄ አለኝ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በ24 ሰዓታት አሥር ኩባንያዎችን እናቋቁማለን፡፡ አንዴ የነዳጅና ባዮፊል ባለሥልጣን ይባላል፣ በሌላ መጠሪያም ዘርፉ እዚህና እዚያ ይደረጋል፡፡ በእኔ ዕይታ አሁን የተቋቋመው ባለሥልጣን አስፈላጊነት ብዙ አይታየኝም፡፡ ለዘርፉ ትኩረት አለመሰጠቱን ያሳያል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋነኛ ሥራው አቅርቦትና ሥርጭት ነው፡፡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ደግሞ የንግድ ሥራውን ማሳለጥ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ በብዛት ከነዳጅ ጋር የተገናኙ ሥራዎች ተነጥቀው የተወሰዱት ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ነው፡፡ ይህ ግራ መጋባት አለው፡፡ እንደገና ደግሞ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ኃላፊነት ፈቃድ መስጠትና የመሳሰሉትን ነው፡፡ እዚህ ላይ የተወሳሰበ ነገር አለ፡፡ በደንብ የፀዳ ነገር አይደለም፡፡ የችግሩ ሥረ መሠረት ትኩረት አድርገን ስላልሠራን ነው፡፡ የቱ ጋ ነው ችግሩ? ለዚህ ምን ዓይነት መፍትሔ ያስፈልጋል ብለን ባለማየታችን ነው፡፡