January 19, 2025

ርዕሰ አንቀጽ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማደግ ያለበት በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ ከሚሰበሰብ ታክስ ብቻ ሳይሆን ከግብርና፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከማዕድን፣ ከአገልግሎትና ከሌሎች ሀብት አመንጪ ዘርፎች ጭምር ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ ያለ ተደራራቢ ታክሶች፣ የመንግሥታዊ አገልግሎቶች ክፍያና ታሪፍ ጭማሪዎች፣ የትራፊክ ቅጣትና ሌሎች ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ የታክስና የቀረጥ ገቢዎች በዜጎች ኑሮ ከፍተኛ ጫና እየፈጠሩ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ጭማሪዎች በቀጥታ የሚተላለፉት ሸማቾች ላይ ስለሆነ ፅኑ ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡ በፀጥታ ችግር ምክንያት በበርካታ አካባቢዎች የተረጋጋ የግብርና ሥራ እየተካሄደ አይደለም፡፡ ብዙዎቹ ፋብሪካዎች ከአቅማቸው ከግማሽ በታች ሲያመርቱ በዚያው መጠን ሥራ ያቆሙም የሉም፡፡ መንግሥት ገቢ መሰብሰብ ላይ ሲያተኩር የሚሰበሰበው ገቢ በከፍተኛ የሥራ ፈጠራ፣ በምርትና በምርታማነት ላይ ካልተመሠረተ ሁሉም ነገር ቀጥ የሚልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ስለሚችል መንግሥት ገቢውን ብቻ ሳይሆን የሕዝቡን ኑሮ ያካተተ ስትራቴጂ ይንደፍ፡፡ 

ከዚህ በፊት የነበሩና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠሩ ችግሮችን ለማስወገድ ቅደም ተከተል ያስፈልጋል፡፡ በረጅም፣ በመካከለኛና በአጭር ጊዜ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን መለየት ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትኩረት ከሚፈልጉ ጉዳዮች መካከል ሰላም፣ የምግብ ዋስትና፣ መጠለያ፣ የሥራ ፈጠራና የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡ መንግሥት ሌሎች ጊዜ የሚሰጡ ፕሮጀክቶቹን ገታ አድርጎ መሠረታዊና አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ቢያተኩር ከመካከለኛ ኑሮ ወደ ድህነት፣ ከድህነት ወደ ባሰው ፍፁም ድህነት እያሽቆለቆሉ ያሉ ወገኖችን መታደግ ይችላል፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ደግሞ በተለይ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቴክኖሎጂና በሌሎች ዘርፎች በርካታ ወጣት የሰው ኃይል ሊያሰማራ የሚያስችል አዋጭ ፖሊሲ መንደፍ ነው፡፡ የልማት ዕቅዱ በተጨባጭ የዜጎችን ሕይወት የሚለውጥ መሆን አለበት፡፡ የሕዝቡ ኑሮ ከዕለት ወደ ዕለት እየከበደ ሲሄድ አዋጭ አማራጮችን በባለሙያዎች ታግዞ ማየት ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ሰላም አግኝታ በአዋጭ ፖሊሲ የተደገፈ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ካልተፈጠረ በስተቀር፣ አሁን ባለው ሁኔታ ወደኋላ እንጂ ወደፊት አንዲት ጋት መራመድ አይቻልም፡፡ በመላ አገሪቱ ሰዎችና ምርቶች በሚፈለገው ልክ ካልተዘዋወሩ የምርቶች አቅርቦት ይገታል፡፡ አቅርቦት ሲያንስ ደግሞ ፍላጎት በጣም ይጨምራል፡፡ በዚህ ላይ የግብይት ሥርዓቱ በወጉ ስለማይመራ ዜጎች ምክንያታዊ ላልሆነ የዋጋ ንረት እየተዳረጉ ድህነቱ እየተባባሰ ነው፡፡ መንግሥት በፕሮጀክቶቹ ሳቢያ ገበያው ውስጥ የሚረጨው ገንዘብ ሲበዛ ችግሩ ይጨምራል፡፡ በበርካታ ሥፍራዎች ሰላም ጠፍቶ የሰዎችና የምርቶች ዝውውር ሲገታ፣ ዜጎች የኑሮ ውድነቱን ሊቋቋሙት አይችሉም፡፡ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች መጠን ሲቀንስ የዋጋ ንረቱ ማቆሚያ አይኖረውም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከባዱን የኑሮ ጫና መቋቋም የተሳናቸው ዜጎች ለከፍተኛ ችግር ከመጋለጣቸውም በተጨማሪ፣ የሰላም ዕጦት ታክሎበት ሕይወታቸው በምሬት እየተሞላ ነው፡፡ ከምንም ነገር በፊት ለሰላም መስፈንና ለኑሮ ውድነቱ መርገብ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

እንደሚታወቀው ኢኮኖሚው ሲዳከም ለግጭት ምክንያት የሚሆኑ ችግሮች ይበራከታሉ፡፡ ድህነት ሲባባስና የማደግ ዕድሎች ሲጨናገፉ ሰዎች ወደ ግጭት ያመራሉ፡፡ በማኅበረሰቦች ውስጥ በእኩልነት ፉክክር ለማደግ የሚያስችሉ አማራጮች ሲጠፉ፣ ሥራ አጥነት ሲስፋፋ፣ በቂ ምግብና መጠለያ ሳይኖር ሲቀርና ተስፋ አስቆራጭ ክስተቶች ሲበዙ ግጭት ውስጥ መግባት የተለመደ ሥራ ይሆናል፡፡ ከግጭት በመለስ ከኪስ አውላቂነት ጀምሮ እስከ ተደራጀ ዘረፋና ግድያ ድረስ የሚያስገቡ ወንጀሎች ይለመዳሉ፡፡ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ሥፍራዎች የተካሄዱ ግጭቶችና ጦርነቶች ኢንቨስትመንቶችንና የንግድ ሥራዎችን አውከዋል፡፡ በዚህም ምክንያት እንኳንስ ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር፣ ሥራ ላይ የነበሩ በርካታ ዜጎች ለሥራ አጥነት ተዳርገዋል፡፡ ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በየመጠለያው ዕርዳታ ጠባቂ ከመሆን አልፈው፣ የከፋ ድህነት ውስጥ ሆነው ተስፋ እንዲቆርጡ ተገደዋል፡፡

አገር ሰላም የምታገኘው ሕዝብና መንግሥትን ሆድና ጀርባ የሚያደርጓቸው እንከኖች ሲወገዱ ነው፡፡ እንከኖቹ ደግሞ ሕዝብና መንግሥት ውስጥ የመሸጉ በመሆናቸው ለግልጽነት፣ ለተጠያቂነትና ለኃላፊነት መርህ መገዛት ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብ የመንግሥት ቀጣሪ እንደ መሆኑ መጠን ለልማቱና ለሰላሙ መንግሥትን ማገዝና መቆጣጠር ይኖርበታል፡፡ መንግሥትም የቀጠረውን ሕዝብ በፍፁም ጨዋነትና ኃላፊነት ስሜት ማገልገል ይጠበቅበታል፡፡ ሕግ አውጭው ፓርላማ፣ አስፈጻሚው መንግሥትና ሕግ ተርጓሚው አካልም በሚዛናዊ ቁጥጥር አንዱ ከሌላው ጋር የሚናበቡበትን አሠራር በሕጉ መሠረት ማከናወን አለባቸው፡፡ በተለይ መንግሥት ልማቱን ለማቀላጠፍ፣ ሕግ ለማስከበርና ሌሎች ኃላፊነቶቹን ለመወጣት ከሕዝብ ጋር አብሮ መሥራት አለበት፡፡ የአገር ጉዳይ በድጋፍና በተቃውሞ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ የሚቀነበብ ሳይሆን፣ ሰፋ ያለ ዕይታ ያለው ጉዳይ መሆኑ ይታመን፡፡ አገር የምትረጋጋው በልማትና በፀጥታ ጉዳዮች ጭምር መግባባት ሲቻል ነው፡፡

በመላ አገሪቱ በሕዝብ ለሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ስለማይሰጥ አንፃራዊው ሰላም ደፍርሶ በቦታው ግጭት ይተካል፡፡ ለምሳሌ በከተሞች ውኃ ከሳምንት በላይ ይጠፋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል በየቀኑ ይቆራረጣል፣ ለቀናትም ይጠፋል፡፡ የትራንስፖርት ችግር አሁንም ድረስ መፍትሔ ያጣ ፈተና ነው፡፡ የበርካታ መንግሥታዊ ተቋማት ቢሮክራሲ ያስመርራል፡፡ ሙሰኞች በጣም ከመብዛታቸው የተነሳ በየቁኑ አቤቱታዎች ይሰማሉ፡፡ ቅሬታ ሰሚ ግን አልተገኘም፡፡ የሕዝቡን ሕጋዊ መብቶች ማን ያክብር? እነዚህ ከላይ የተነሱት መጠነኛ ችግሮች ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ በመሆናቸው አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ ዜጎች ከአቅማቸው በላይ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ወገባቸውን እያጎበጣቸው በላዩ ላይ የተለያዩ ክፍያዎች ሲታከሉበት የኑሮ ክብደቱ ያስፈራል፡፡ በጣም መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ማለትም ምግብ፣ መጠለያና አልባሳት ለብዙዎች ከአቅም በላይ እየሆኑ ነው፡፡ ምርትና ምርታማነት ላይ ትኩረት ሳይደረግ የመንግሥት ገቢ ላይ ብቻ ማተኮር ተገቢ አይደለም፡፡ የመንግሥት ገቢን ከመሰብሰብ ባሻገር የሕዝብ ኑሮ ትኩረት ይቸረው!