20 ጥር 2025
ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ሰኞ ጥር 12/2017 ቃለ-መሐላ ፈፅመው የኃያሏን አገር የመሪነት ቦታ ለሁለተኛ ጊዜ ይረከባሉ።
ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ ፈጣን እና ጥልቅ ለውጥ ለማምጣት ቃል የገቡት ትራምፕ በአስተዳደራቸው ውስጥ 10 ሹማምንት ይዘው ነው ወደ ሥልጣን የሚመጡት።
የትራምፕ ሹም ለመሆን ትልቁ መስፈርት ተዓማኒነት ይመስላል። ነገር ግን እያንዳንዳቸው የትራምፕ ባለሥልጣናት የራሳቸውን ሐሳብ ይዘው መምጣታቸው አይቀርም።
እነዚህ ቁልፍ የትራምፕ አስተዳደር አስር ሹማምንት አነ ማናቸው? ኃላፊነታቸውስ ምንድነው?
የስደተኞች ጉዳይ
የስደተኞች ጉዳይ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ደጋግመው ሲያነሱት የነበረ ዋነኛ አጀንዳቸው ነው። ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በሕገ-ወጥ መንገድ የገቡ ሰዎችን ከሀገሪቱ ማባረር እና ድንበራቸው ላይ ያለውን ጥበቃ በከፍተኛ ደረጃ ማጠናከር ይፈለጋሉ።
በቅስቀሳቸው ወቅት በአሜሪካ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሕገወጥ ስደተኞችን ከሀገራቸው ለማባረር ቃል ገብተዋል። ይህ እንዴት ተግባራዊ ሊሆን ይችላል የሚለውን ጊዜ የሚፈታው ይሆናል።
ክሪስቲ ኖም – የሀገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር
“እያንዳንዱ ሕገ ወጥ ስደተኛ አሜሪካ ሲገባ የመጀመሪያ ሥራው ሕግ መጣስ ነው።”
አራት ጊዜ የኮንግረስ አባል ሆነው ያገለገሉት ክሪስቲ በአውሮፓውያውኑ 2018 ነው የሰሜን ዳኮታ ግዛት ሀገረ ገዥ ሆነው የተሾሙት። በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛን እንዲሁም ሌሎች ሕግጋትን በመቃወም ይታወቃሉ።
በወረርሽኙ ወቅት የአሜሪካ የነፃነት ቀን ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ሆነው አክብረዋል።
በፕሬዝደንት ጆ ባይደን የአስተዳደር ዘመን አሜሪካ ድንበሯን አጥብቃ አልያዘችም ሲሉ ብዙ ትችት ሲያቀርቡ ቆይተልዋል። የግዛታቸውን የፀጥታ ኃይሎች ወደ ድንበር የላኩ የመጀመሪያዋ ሀገረ ገዥም ናቸው።
አኒህን ግለሰብ ዶናልድ ትራምፕ ለሥልጣን ቢያጯቸውም የክሪስቲ ሹመት በሀገሪቱ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴናት) መፅደቅ ይኖርነታል።
ቶም ሆማን – የድንበር ጥበቃ ኃላፊ
“ከ9/11 ጥቃት በኋላ ይህ በታሪክ አሜሪካ ተጋላጭ የሆነችበት ወቅት ነው። ይህን ማስተካከል ይገባናል።”
ለአስርት ዓመታት በድንበር ጥበቃ ዙሪያ ሠርተዋል። በቀደመው ጊዜ የፖሊስ መኮንን ነበሩ። በአንድ ወቅት ደግሞ የአሜሪካንንን ኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ (አይሲኢ) የተባለውን መሥሪያ ቤት መርተዋል። በድንበር ጉዳይ ለትራምፕ ትክክለኛው ሰው ይመስላሉ።
ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ወቅት ከአዋቂ ስደተኞች ጋር የመጡ ሕፃናትን ከወላጆቻቸው ለይተዋል ተብለው ተወቅሰዋል፤ ቶም የዚህ ፖሊሲ ደጋፊ ናቸው።
ወግ አጥባቂ በሚባሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ እየቀረቡ ሐሳብ አስተያየት በመስጠት ይታወቃሉ። የፌዴራል መንግሥቱ የሚያራምደውን ፖሊሲ በተለመከተ ከረር ያለ አቋም አላቸው።
የውጭ ጉዳይ
በርካታ ወግ አጥባቂዎች በምጣኔ ሀብት እና በወታደራዊ ጉዳይ የዩናይትድ ስቴትስ ትልቋ ተቀናቃኝ ቻይና ናት ብለው ያስባሉ።
ትራምፕ ብዙውን ጊዜ ቻይናን በተለመከተ ሐሳብ ሲሰጡ የንግድ ጉዳይ ላይ ነው የሚያተኩሩት። ነገር ግን ለውጭ ጉዳይ የመረጧቸው ሰዎች በቻይና ጉዳይ ጠንከር ያለ አቋም ያላቸው ናቸው። የትራምፕ የታሪፍ ጭማሪ ያስፈፅማሉ ተብለውም ይጠበቃሉ።
- ከቢቢሲ አማርኛ ዜና እና ታሪኮች በቀጥታ እንዲላክልዎ የዋትስአፕ ቻናላችን አባል ይሁኑ5 ታህሳስ 2024
- ትራምፕ የፓናማ ቦይ፣ ግሪንላንድን እና ካናዳን ለመጠቅለል ለምን ፈለጉ?10 ጥር 2025
- የአነጋጋሪው ዶናልድ ትራምፕ የሕይወት ታሪክ – ከሪል ስቴት እስከ ፖለቲካ5 ጥቅምት 2024
ማርኮ ሩቢዮ – የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
“ይህን ምዕተ ዓመት የምትገዳደረው ቻይና ናት። ይህን ለመቋቋም ደግሞ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ማኅበረሰብ አብሮን ሊቆም ይገባል።”
ከአውሮፓውያኑ 2011 ጀምሮ ፍሎሪዳ የወከሉት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባሉ ኩባዊ አሜሪካዊው ማርኮ ሩቢዮ ናቸው። በአንድ ወቅት የትራምፕ ቀንደኛ ተቺ ነበሩ። በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል።
በ2016 ሩቢዮ የሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው ዕጩ ፕሬዝደንት ለመሆን በተወዳደሩበት ወቅት ሩቢዮ እና ትራምፕ ከበድ ያለ እሰጥ አገባ ውስጥ ነበሩ። ነገር ግን ትራምፕ የዕጩነት ቦታውን ማግኘታቸውን ተከትሎ ሩቢዮ ድጋፋቸውን ሰጥተዋቸዋል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ዋነኛ የትራምፕ ደጋፊ ሆነው ብቅ ብለዋል። በኢራን ጉዳይ ጠንከር ያለ አቋም አላቸው። በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት እንዲሁም በቻይና ጉዳይም ፈርጠም ያለ አስተያየት ሲሰጡ ይሰማል።
የ53 ዓመቱ ፖለቲከኛ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ሆነው ከትራምፕ ጋር ወደ ዋይት ሐውስ ያቀናሉ።
ማይክል ዋልትዝ – የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ
“አምባገነናዊ መንግሥታት ጥንካሬ የሚያገኙት በፍርሀት ስለሚታጠሩ ነው። ጠንከር ያለ አቋም ያስፈራቸዋል።”
በጦር ሠራዊቱ ልዩ ኃይል ውስጥ አገልግለዋል። ብዙ ኒሻን ተሸልመዋል። በአሜሪካ ምክር ቤትም ፍሎሪዳን በመወከል የኮንግረስ አባል በመሆን አገልግለዋል።
በቻይና ጉዳይ ያላቸውን አቋም ጠንከር ያለ ነው። አሜሪካ በፓሲፊክ ውቅያኖስ ለሚነሳ ግጭት በተጠንቀቅ መቆም አለባት የሚል ሐሳብ ሰጥተው ያውቃሉ።
በ2022 ቤይጂንግ ባዘጋጀችው የክረምት ኦሊምፒክ ዩናይትድ ስቴትስ መሳተፍ የለባትም ብለው አቋም ይዘው ነበር።
የባይደንን አስተዳደር አጥብቀው ይተቻሉ። በተለይ ደግሞ የአሜሪካ ወታደሮች ከአፍጋኒስታን የወጡበትን መንገድ ሲነቅፉ ቆይተዋል።
የአሜሪካ ጦር የዘር እና የፆታ እኩልነት ላይ ከሚያተኩር የጦርነት ብቃት ያላቸውን ሰዎች ቢመለምል ይሻል የሚል አስተያየትም ሰጥተው ያውቃሉ።
ወጪ ቅነሳ
ትራምፕ ሁለት የቴክኖሎጂ ፈርጦችን የመንግሥትን ወጪ አንዲቆጣጠሩ እና እንዲቀንሱላቸው ሹመዋል። እነሱም ኢላን መስክ እና ቪቬክ ራማስዋሚ ናቸው።
የመንግሥት ተቋማት በውስን ወጪ ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውኑ የተቋቋመው አዲስ መሥሪያ ቤት ዲፓርትመንት ኦፍ ኤፊሼንሲ (ዶጅ) የተባለ ሲሆን፣ የመንግሥትን ቢሮክራሲ “ለመበጣጠስ የተቋቋመ ነው” ተብሏል።
ኢላን መስክ 2 ትሪሊዮን የመንግሥት ወጪ እቆጥባለሁ ሲል ቃል ገብቷል። ቪቬክ ደግሞ ግብር ሰብሳቢውን መሥሪጣ ቤት (አይኤርኤስ) እና የትምህርት ሚኒስቴርን ለማፍረስ አልሟል።
ኦፊሴላዊ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ያልሆነው ዶጅ ይህንን ዕቅዱን እንዴት ሊያሳካ ይችላል የሚለው በጊዜ ሂደት የሚታይ ይሆናል።
ኢላን መስክ – የመንግሥት ወጭ ቁጠባ
“የዲሞክራሲ ፀር? አይደለም። የቢሮክራሲ ጠር እንጂ።”
ደቡብ አፍሪካ የተወለደው የኤክስ፣ የቴስላ እና የስፔኤክስ ባለቤት ኢላን መስክ የዓለማችን ሀብታሙ ሰው ነው። ትዊተርን ገዝቶ ኤክስ ብሎ ከቀየረው በኋላ በርካታ ሠራተኞችን አባሯል።
የፖለቲካ አቋሙን ይፋ ከማድረግ ይቆጠብ የነበረው መስክ፣ ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ነው ትራምፕን በይፋ በመደገፍ ቅስቀሳ ጭምር ማድረግ የጀመረው።
ቴክኖሎጂን በመጠቀም የመንግሥት ወጪውን በሰፊው መቀነስ ይቻላል ብሎ ያምናል።
ቪቬክ ራማስዋሚ – የመንግሥት ወጭ ቁጠባ
“ኤፍቢአይ ‘ሊለወጥ’ አይችልም። ትክክለኛው መልሰ የሚሆነው መዝጋት ነው። አዎ ፕሬዝደንቱ ሊያደርጉት ይችላሉ። እኔም አደርገዋለሁ።”
ሕንዳዊ አሜሪካዊው ሚሊየነር በባዮቴክኖሎጂ ዘርፍ ነው ሀብት ያፈራው። በ2024 ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ዕጩ ለመሆን ቢወዳደርም አልተሳካለትም። ከዚያ በኋላ ነው የትራምፕን ቡድን የተቀላቀሉት።
የሴራ ትንታኔን በማቀንቀን ይታወቃሉ። የመንግሥት ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ አለበት ብሎ ያምናል። ይህን ለማድረግ ደግሞ አንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መዘጋት አለባቸው ይላሉ።
ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር – የጤና ሚኒስትር
“በፋብሪካ የተቀናበሩ ምግቦች ለክብደት መጨመር ምክንያት ናቸው። ይህን የተሰበረ ሒደት እንጠግናለን። አሜሪካን እንደገና ጤናማ እናደርጋታለን።”
ለረዥም ጊዜ ጠበቃ እና የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ ሆነው አገልግለዋል።
ምንም እንኳ የሕክምና ልምድ ባይኖራቸውም የጤና ሚኒስትር ሆነው እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል። በምግብ እና መድኃኒት ጉዳይ ፈላጭ ቆርጭ ይሆናሉ ማለት ነው።
አንዳንድ ሐሳቦቻቸው በሙያተኞች ውድቅ እየተደረጉ ነው። በሌሎች ጉዳዮች ግን ከሕዝቡ ይሁንታ ያገኙ ይመስላል። በተለይ ደግሞ በፋብሪካ ተመርተው በሚወጡ ምግቦች ላይ በሚያራምዱት ፖሊሲ።
በ2024 ፕሬዝደንታዊ ምርጫ መጀመሪያ ላይ ዲሞክራቶችን ወክለው፣ ቀጥሎ ደግሞ በግላቸው ተወዳድረው አልተሳካላቸውም።
ከምርጫው ራሳቸውን ካገለሉ በኋላ ለትራምፕ ድጋፋቸውን የሰጡት ኬኔዲ ሹመታቸው በሴኔቱ መፅደቅ አለበት።
ቱልሲ ጋባርድ – ብሔራዊ ደኅንነት
“ትራምፕ ከአንድ የጦር አዛዥ የሚጠበቀውን ጥንካሬ አሳይተዋል። ሰላምን ይሻሉ። ጦርነት እንደ መጨረሻ አማራጭ ነው የሚጠቀሙት።”
በአሜሪካ ጦር ሠራዊት ውስጥ ያገለገሉት ጋባርድ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመተቸት ይታወቃሉ።
በ2017 ዲሞክራት ፓርቲን ወክለው የኮንግረስ አባል ሳሉ ከቀድሞው የሶሪያ ፕሬዝደንት ባሽር አል-አሳድ ጋር ተገናኝተዋል። የአሜሪካ ደኅንነት መሥሪያ ቤቶች የአሳድ መንግሥት ኬሚካል የጦር መሣሪያ ይጠቀማል ማለቱ እንዳጠራጠራቸው ተናግረው ነበር።
ሩሲያ ዩክሬንን ስትወር ኔቶን ወቅሰዋል። አሜሪካ ዩክሬንን እያስታጠቀችም ነው ብለዋል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው ከዲሞክራት ፓርቲ ተነጥለው ትራምፕን መደገፍ የጀመሩት። ነገር ግን አሜሪካ በሌሎች ሀገራት ጦርነት ጣልቃ መግባት የለባትም የሚለውን አቋማቸውን አልቀየሩም።
ሆዋርድ ሉትኒክ – የንግድ ሚኒስትር
“በታሪፍ ጉዳይ እኛም ገንዘብ እናገኛለን። በተጨማሪ ደግሞ ሌሎች ሀገራት ከእኛ ጋር መደራደር ይጀምራሉ።”
ቢሊየነሩ የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳን በገንዘብ በመደገፍ ይታወቃሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ ሥራዎችን የመፈጠር ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
የትራምፕን የምጣኔ ሀብት ዕቅድ ይደግፋሉ። የታሪፍ ጭማሪን ጉዳይ የማስፈፀም ኃላፊነት የንግድ ሚኒስቴር ነው። ክሪፕቶከረንሲን መቆጣጠር እና ከገቢ የሚቆረጥ ግብርን የማንሳት ጉዳይም የሳቸው ሥራ ይሆናል።
ስኮት ቤሴንት – የግምጃ ቤት ኃላፊ
“የታሪፍ ጭማሪን ልንፈራው አይገባም። የበርካታ አሜሪካውያንን ሕይወት ሊቀይር ይችላል።”
በፋይናንሱ ዘርፉ ረጅም ጊዜ በማገልገል ልምድ ያካበቱት ስኮት ለቦታው ትክክለኛ ሰው ናቸው የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ።
የበጀት ቅነሳ እና አሜሪካ የነዳጅ ምርቷን መጨመር አለባት የሚሉ ሐሳቦችን ያንፀባርቃሉ።