20 ጥር 2025
ዶናልድ ትራምፕ ዴሞክራቷ ካማላ ሃሪስን ማሸነፋቸውን ተከትሎ በሚመጣው ጥር ወር ዳግመኛ ወደ ፕሬዝዳንትነት ይመለሳሉ።
በአሜሪካ ታሪክ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ በተከታዩ ምርጫ ውድድር ተሸንፈው ዋይት ሐውስን ከለቀቁ በኋላ፣ በቀጣይ ውድድር በማሸነፍ ወደ ሥልጣን የተመለሱ ሁለተኛው ፖለቲከኛ ናቸው።
እአአ ከ2017 እስከ 2021 ፕሬዝዳንት የነበሩት ትራምፕ አነጋጋሪ የአደባባይ ሕይወት አላቸው። ወታደራዊ ትምህርት ቤት መማራቸውን ጨምሮ ሌሎችም ስለ ትራምፕ የማይታወቁ እውነታዎችም አሉ።
ከእነዚህ መካከል ስምንቱን እንመልከት።
1. በኒው ዮርክ ወታደራዊ ትምህርት ቤት ተምረዋል
ትራምፕ በ13 ዓመታቸው ወላጆቻቸው ኒው ዮርክ ወደ ሚገኘው ወታደራዊ ትምህርት ቤት ልከዋቸው ነበር።
ትምህርት ቤቱ አመፀኛ ወጣቶችን “የሚያስተካከል” እንደሆነ ይገለጻል።
‘ዘ አርት ኦፍ ዘ ዲል’ በሚል ትራምፕ እአአ በ1987 ባሳተሙት መጽሐፍ “ወጣት ሳለሁ አመፀኛ ነበርኩ። ችግር መፍጠር እና ሰዎች መገዳደር ያስደስተኝ ነበር” ብለዋል።
በወታደራዊ ትምህርት ቤቱ ለአምስት ዓመታት ሲቆዩ ቅርጫት ኳስ፣ እግር ኳስ እና ቤዝቦል ይጫወቱ ነበር።
የመሪ ባህሪ ያላቸው እንደነበሩ አንዳንድ አብረዋቸው የተማሩ ሰዎች ያስታውሳሉ። ሌሎች ደግሞ ለአሜሪካ ጋዜጦች እንደተናገሩት ትራምፕ ጨቋኝ ነበሩ።
ከዚያም ብሮንክስ በሚገኘው ፎርድሃም ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት ጀመሩ። ከሁለት ዓመት በኋላ ፔንሲልቬንያ ወደሚገኘው ዋርቶን ስኩል ኦፍ ቢዝነስ ተዘዋወሩ።
በኢኮሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው።
እንዴት ወደ ትምህርት ቤቱ እንደገቡ እና ውጤታቸው ምን ይመስል እንደነበር ግን በግልጽ አይታወቅም።
2. የአባታቸው ድርጅት ወራሽ ነበሩ
ከኮሌጅ ከወጡ በኋላ በአባታቸው የሪል ስቴት ድርጅት መሥራት ጀመሩ።
የ25 ወጣት ሳሉ በአውሮፓውያኑ 1971 የድርጅቱ አስተዳዳሪ ሆኑ። ‘ትራምፕ ኦርጋናይዜሽን’ ብለው ተቋሙን ሰየሙት።
ቅንጡ ቤቶችን በመገንባት ከፍተኛ ገቢ ያገኙ ነበር። በቴሌቭዥን ሲቀርቡ ዝናቸው ናኘ። ኋላ ላይም ወደ ፖለቲካው ገቡ።
ድርጅታቸው የንግድ እና የመኖሪያ ሕንጻዎች እንዲሁም ቢሮዎች፣ ቁማር መጫወቻ፣ ኮንዶሚንየም፣ ጎልፍ መጫወታ፣ ሆቴል እና ሪል ስቴት መገንባት ቀጠለ።
የኒው ዮርክ ታይምስ የምርመራ ዘገባ እንደሚለው፣ ትራምፕ ወደ 400 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ከአባታቸው ወስደዋል።
- ከቢቢሲ አማርኛ ዜና እና ታሪኮች በቀጥታ እንዲላክልዎ የዋትስአፕ ቻናላችን አባል ይሁኑ5 ታህሳስ 2024
- የትራምፕ ማሸነፍን በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውን እንዴት ይመለከቱታል? ለኢትዮጵያስ ምን ይዞ ይመጣል?7 ህዳር 2024
- ንግድ፣ እርዳታ፣ ፀጥታ፡ የትራምፕ ወደ ፕሬዝዳንትነት መመለስ ለአፍሪካ ምን ማለት ነው?7 ህዳር 2024
3. ትራምፕ ዴሞክራት ነበሩ
ዶናልድ ትራምፕ ከዓመታት በፊት የሚያራምዱት ፖለቲካ ከአሁኑ የተለየ ነበር።
ከአራት ዓመት በፊት እና አሁን ለፕሬዝዳንትነት በምርጫ የተወዳደሩት የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ሆነው ቢሆንም ቀደም ሲል የተቀናቃኙ ዲሞክራቲክ ፓርቲ አባል ነበሩ።
አብዛኛውን ሕይወታቸውን ያሳለፉት በሪፐብሊካን ፓርቲ ቢሆንም ከ2001 እስከ 2009 በኒው ዮርክ የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባል እንደነበሩ የምርጫ ቦርድ መረጃ ይጠቁማል።
በ2000 የሪፎርም ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ለመሆንም ጥረት አድርገው ነበር። ሆኖም ፓርቲው ቀውስ ውስጥ ሲገባ ዕቅዳቸውን ሰረዙ።
4. ጽንስ ማቋረጥ ላይ ያላቸውን አቋም በተደጋጋሚ ቀይረዋል
እአአ በ1999 ከኤንቢሲ ‘ሚት ዘ ፕረስ’ ከተባለው ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ “የሴቶችን ምርጫ እደግፋለሁ” ብለው ነበር ትራምፕ።
ሪፐብሊካኑ ትራምፕ ስለ ጽንስ ማቋረጥ ያላቸውን አቋም በተደጋጋሚ ለውጠዋል። ጉዳዩ አሜሪካውያንን የሚከፋፍል ነው። በየካቲት 2011 ጽንስ ማቋረጥን እንደማይደግፉ አስታወቁ። ይህንን የገለጹት በኮንሰርቫቲቭ ፖለቲካል አክሽን ኮንፍረንስ ላይ ነበር።
ከ2017 እስከ 2021 ሥልጣን ላይ ሳሉ ከ20 ሳምንታት በኋላ ጽንስ ማቋረጥ በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲታገድ ለማድረግ ሞክረዋል።
ወግ አጥባቂ ዳኞችን በጠቅላይ ፍርድ ቤት በመሾም ጽንስ ማቋረጥን ሕገ ወጥ ለማድረግ ቃል በገቡት መሠረት አስፈጽመዋል።
በ2024 የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ፣ ጽንስ ማቋረጥን መፍቀድም ሆነ መከልከል የግዛቶች ውሳኔ እንደሆነ ገልጸዋል።
5. የትራምፕ ስድስት ቢዝነሶች ከስረዋል
ከዶናልድ ትራምፕ ንግዶች መካከል ስድስቱ ዕዳቸውን መክፈል ተስኗቸው ከስረዋል።
እነዚም በአትላንቲክ ሲቲዋ ኒው ጀርሲ ይገኝ የነበረው ትራምፕ ታጅ ማሀል ካዚኖ (በ1991)፣ በአትላንቲክ ሲቲ ይገኝ የነበረው ትራምፕ ካስል ካዚኖ (በ1992)፣ በአትላንቲክ ሲቲ ይገኝ የነበረው ትራምፕ ፕላዛ ኤንድ ካዚኖ (በ1992)፣ በኒው ዮርክ ይገኝ የነበረው ፕላዛ ሆቴል (በ1992) ይጠቃሳሉ።
በተጨማሪም በአትላንቲክ ሲቲ እና ኢንዲያና ይገኝ የነበረው ትራምፕ ሆቴልስ ኤንድ ካዚኖ ሪዞርትስ (በ2004)፣ እንዲሁም ትራምፕ ኢንተርቴመንት ሪዞርትስ (በ2009) ኪሳራ አጋጥመጨው የተዘጉ የትራምፕ ተቋማት ናቸው።
በ1992 ከአበዳሪ ባንኮች ጋር ባደረጉት ስምምነት ዕዳቸውን ለማስተካለል ሞክረዋል።
መርከባቸውን፣ ጄታቸውን፣ አውሮፕላን ማረፊያቸውን፣ በግራንድ ሃይት ያላቸውን ድርሻ እና ትራምፕ ሸትልን ለመሸጥም ተገደዋል።
በድጋሚ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ ሲገቡም ከአበዳሪ ባንኮች ጋር ስምምነት በማድረግ ተወጥተውታል።
የቁማር ማጫዎቻዎች እና ሆቴሎች እንዲሁም የኒው ጀርሲ ጄኔራልስ የእግር ኳስ ቡድን እና ትራምፕ ዩኒቨርስቲ ስኬታማ ካልሆኑ ቢዝነሶቻቸው መካከል የሚገኙ ናቸው።
6. ‘ዘ አፕረንተስ’ ላይ ከታዩ በኋላ ዝነኛ ሆነዋል
‘ዘ አፕረንተስ’ ቢልየነሮች ከሚቀርቡባቸው የቴሌቪዥን ትርዒቶች (ሾው) መካከል አንዱ ነበር። ትራምፕም የዚህ ዝግጅት አቅራኒ ሆነው ከታዩ በኋላ ዝነኛ ሆነዋል።
ወደ ፖለቲካው ከመግባታቸው በፊት በቴሌቪዥን መሰናዶዎች እና መዝናኛዎች ቀርበዋል።
የቁንጅና ውድድሮችን መዳኘት ነበር መጀመሪያ ላይ ታዋቂ ያደረጋቸው። ከዚያም ከ2004 እስከ 2015 በቴሌቪዥን የተላለፈው ‘ዘ አፕረንተስ’ ላይ መታየታቸው ይጠቀሳል።
በተጨማሪም ‘ዘ ፍሬሽ ፕሪንስ ኦፍ ቤል ኤር’ እና ‘ሆም አሎን 2’ ላይ ራሳቸውን ሆነው ተውነዋል።
7. ትራምፕ በስቶርሚ ዳንኤልስ ተከሰዋል
በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያው ጥፋተኛ የተባሉ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ናቸው።
ጥፋተኛ የተባሉት በ34 ክሶች ሲሆን፣ ይህም ከ2016ቱ ምርጫ በፊት ከወሲብ ፊልም ተዋናይቷ ስቶርሚ ዳንኤልስ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ክፍያ በመፈፀም ለመሸፈን ሐሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀትን ያካትታል።
ትሩዝ ሶሻል በተባለው የራሳቸው ንብረት በሆነው ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ንጹህ መሆናቸውን ገልጸው “ፖለቲካዊ ጥቃት” ነው ሲሉ ክሱን አጣጥለዋል።
በተጨማሪም ካላቸው ገንዘብ በላይ እንዳላቸው በማስመሰል የተከሰሱ ሲሆን፣ ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል።
ኢ ጂን ኮሮል የተባለችውን አምደኛ በመተንኮስ እና ስም በማጥፋትም ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል።
ከከሰረው የትራምፕ ዩኒቨርስቲ ጋር በተያያዘ ለተማሪዎች ካሳ እንዲከፍሉ በ2018 ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።
ሌሎች ሦስት የወንጀል ክሶችም አሉባቸው። ይህም የአሜሪካ ምርጫ ውጤትን ለመቀልበት በ2020 ሙከራ አድገዋል የሚለውን ክስ ያካትታል።
8. የጀርም ፍርሃት አለባቸው
እአአ በ1997 ባሳተሙት ‘ዘ አርት ኦፍ ዘ ካምባክ’ መጽሐፍ ላይ እንዳሉት “የአሜሪካ እርግማን የሆነው የሰዎችን እጅ መጨበጥ ነው” ሲሉ መጨባበጥን ነቅፈዋል።
ደጋግመው ስለ እጅ ንጽህና ያወራሉ።
“ንጹህ እጅ እወዳለሁ። እጄን በደንብ ስታጠብ ጥሩ ስሜት ይሰማኛል። በቻልኩት መጠን ያን አደርጋለሁ” ብለዋል።
ለህመም የሚያጋልጥ ነገር ሲገጥማቸው እንደሚጨነቁ አብረዋቸው የሠሩ ሰዎች ይናገራሉ።
በ1993 ከሀዋርድ ስተርን ጋር ቆይታ ባደረጉበት የራድዮ መሰናዶ ላይ “የጀርም ፍርሃት አለብኝ” ማለታቸው ይታወሳል።