20 ጥር 2025
ቲክቶክ ከ170 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ተጠቃሚዎቹ ድጋሚ አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ አስታወቀ።
ኩባንያው ድጋሚ ሥራ የጀመረው ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ ሥልጣን ሲይዙ ለቲክቶክ የእፎይታ ጊዜ እንደሚሰጡ ካስታወቁ በኋላ ነው።
ቅዳሜ አመሻሹን የቻይናው መተግበሪያ አሜሪካ ውስጥ አገልግሎት መስጠት አቁሞ ነበር። ይህን ያደረገው በይፋ ከመታገዱ ከሰዓታት አስቀድሞ ነው።
ከዚህ ቀደም ቲክቶክ መዘጋት አለበት የሚለውን ሐሳብ ይደግፉ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ እሑድ በሰጡት አስተያየት መተግበሪያው እንዲዘጋ የወጣው ሕግ የሚተገበርበት ቀን መራዘም አለበት ብለዋል። ይህን ተከትሎ ቲክቶክ “ድጋሚ አገልግሎት ለመስጠት” ሥራ መጀመሩን አስታውቆ ነበር።
መተግበሪያው መሥራት ሲጀምር ተጠቃሚዎች ሲከፍቱት የሚመወጣው መልዕክት ላይ ትራምፕን በስም ጠቅሶ ያመሰግናል።
ኩባንያው ባወጣው መግለጫ መጪውን ፕሬዝደንት አመስግኖ “ቲክቶክ አሜሪካ ውስጥ መሥራቱን እንዲቀጥል ዘላቂ የሆነ መፍትሔ” ለመፈለግ ከትራምፕ ጋር እንደሚሠራ ገልጿል።
የቲክቶክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሹ ቺው የትራምፕ በዓል ሲመት ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
- ጥምቀት በመላው ዓለም እንዴት ይከበራል?19 ጥር 2025
- ለቁልፍ ኃላፊነቶች በትራምፕ እምነት የተጣለባቸው አስሩ ባለሥልጣናት እነማን ናቸው?20 ጥር 2025
- ስለ ዶናልድ ትራምፕ በስፋት የማይታወቁ ስምንት እውነታዎች20 ጥር 2025
ዶናልድ ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያቸው እሑድ በለጠፉት መልዕክት “ሰኞ ዕለት ቲክቶክ እንዲታገድ የወጣው ሕግ ተግባራዊ የሚሆንበት ቀን እንዲራዘም ትዕዛዝ እሰጣለሁ። በዚህ ጊዜ ብሔራዊ ደኅንነታችንን ለመጠበቅ ስምምነት ላይ መድረስ እንችላለን” ብለዋል።
የቲክቶክ እናት ኩባንያ ባይትዳንስ መተግበሪያው ለአሜሪካ ኩባንያ መሸጥ አለበት የሚለውን ሐሳብ አጥብቆ ተቃውሞት ነበር። ባለፈው አርብ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኙን ውድቅ አድርጎ ሕጉ እንዲፀድቅ መወሰኑ ይታወሳል።
ትራምፕ ይህን ሽረው ሕጉ የሚተገበርበት ወቅትን የማራዘም ሥልጣን አላቸው ወይ የሚለው ግልፅ አይደለም። ነገር ግን መጪው ፕሬዝደንት ትዕዛዝ ከሰጡ መንግሥታቸው ቲክቶክን አያግደውም ተብሎ ይጠበቃል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ቲክቶክ መታገድ አለበት የሚል ጠንካራ አቋም ሲያንፀባርቁ የነበሩት ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት በርካታ ሚሊዮን ሰዎች የእሳቸውን ቪድዮ በቲክቶክ መመልከታቸውን ተከትሎ አቋማቸው “መለሳለስ” አሳይቷል።
የተሰናባቹ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር ሕጉን ተፈፃሚ ከሚያደርገው ይልቅ መጪው የትራምፕ አገዛዝ እንዲወጣው እንደሚያደርጉ አሳውቆ ነበር።
አጫጭር ቪድዮዎች የሚጋሩበት ቲክቶክ በተለይ በወጣት አሜሪካዊያን ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ሲሆን አሜሪካዊያን ፖለቲከኞች ወጣቶችን ለመሳብ ሲጠቀሙበትም ይስተዋላል።
ቲክቶክ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲታገድ መደረጉ የንግግር ነፃነትን ላይ የተደገነ አደጋ ነው ሲል ቢከራከርም አልተሳካለትም።
የአሜሪካ ኮንግረስ ሪፐብሊካን እና ዲሞክራት አባላት ቲክቶክ የቻይና መንግሥት ንብረት በመሆኑ ለቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ መረጃ አሳልፎ ይሰጣል በሚል ነው ሕጉ ተግባራዊ እንዲሆን ያፀደቁት።