20 ጥር 2025, 08:01 EAT
የጋዛው የመጀመሪያ ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት እሁድ፣ ጥር 11/ 2017 ዓ.ም ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ እስራኤል 90 ሴቶች እና ታዳጊ ወንዶች እስረኞችን ስትፈታ ሐማስ ሶስት ታጋቾችን ለቀቀ።
ለበርካታ ፍልስጤማውያን እልቂት ምክንያት የሆነው የ15 ወራቱ ጦርነት እልባት እንዲያገኝ የተደረሰውን የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ መሆን ተከትሎ ከሰዓታት በኋላ የተለቀቁት ሶስቱ የሐማስ ታጋቾች በቀይ መስቀል በኩል የእስራኤል ጦር እንዲረከባቸው ተደርጓል።
በምትኩም በእስራኤል እስር ቤት ከታሰሩት ፍልስጤማውያን መካከል 69 ሴቶች እና 21 ታዳጊ ወንዶች በድምሩ 90 መለቀቀቻውን ሐማስ አስታውቋል።
ከዌስት ባንክ እና ከኢየሩሳሌም የተወሰዱት እነዚህ ፍልስጤማውያን በአብዛኛው በቅርቡ የታሰሩ፣ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ወይም ያልተፈረደባቸው መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
በመጀመሪያው የተኩስ አቁም ስምምነት ምዕራፍ እስራኤል ወደ 1,900 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ትፈታለች ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ሐማስ 33 ታጋቾችን እንደሚለቅ ይጠበቃል።
እሁድ እለት ከእስራኤል እስር ቤት የተፈቱትን ፍልስጤማውያንን ለመቀበል በርካቶች በዌስት ባንክ ተሰባስበው ታይተዋል።
ቅዳሜ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ጀምሮ በርካቶች እስረኞቹን ለመቀበል በጉጉት ሲጠባበቁ ነበር። እስረኞችን የያዙት አውቶብሶች ቤይቱኒያ በተሰኘችው ከተማ ሲያልፍ ህዝቡ በደስታ፣ በጩኸት፣ በመፈክር እና እልልታቸውን አሰምተዋል።
በአውቶብስ ውስጥ የነበሩት ከእስር የተፈቱት አብዛኛዎቹ ሴቶች ፍልስጤማውያን ለተሰበሰበው ህዝብ ፈገግታቸውን እያሳዩ በጣቶቻቸው የድል ምልክቶችን ሲያሳዩ እንደነበር አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
- እስራኤል እና ሐማስ ስምምነት ላይ ከመድረሳቸው በፊት የነበሩ ቁልፍ ክስተቶች19 ጥር 2025
- ቲክቶክ ትራምፕ ከገቡት ቃል በኋላ ድጋሚ አሜሪካ ውስጥ መሥራት ጀመረ20 ጥር 2025
- ለቁልፍ ኃላፊነቶች በትራምፕ እምነት የተጣለባቸው አስሩ ባለሥልጣናት እነማን ናቸው?20 ጥር 2025
ከተፈቱት መካከል ታዋቂዋ የፍልስጤም ፖለቲከኛ ካህሊዳ ጃራር አንዷ እንደሆነች አሶሺየትድ ፕሬስ እና ኒውዮርክ ታይምስን ጨምሮ በርካታ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ጃራር ‘ፖፑላር ፍሮንት ፎር ዘ ሊበሬሽን ኦፍ ፓለስታይን’ የተሰኘው ለፍልስጤም ነጻነት የሚታገለው ድርጅት ዋነኛ መሪ ናት። ይህ ድርጅት በእስራኤል፣ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ህብረት በአሸባሪ ድርጅትነት ተፈርጇል። ለአስር ዓመታት ያህል እስራኤል ስታስራትና ስትፈታት የቆየችው ጃራር አመጽን በማነሳሳት በሚል ክስ ከዚህ ቀደም ተፈርዶባት ነበር።
በርካታ እስረኞች በጉጉት እየጠበቋቸው ከነበሩ ቤተሰቦቻቸው ጋር ሲገናኙ ሲተቃቀፉ እና ሲላቀሱ የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።
ኳታር፣ አሜሪካ እና ግብጽ ያደራደሩት ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት ሦስት ምዕራፍ አለው።
በመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ሴቶች፣ ህጻናት እና አዛውንቶችን ጨምሮ 33 ታጋቾች ይለቀቃሉ።
እስራኤል በምላሹ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ትለቃለች።
የእስራኤል ጦር ከምሥራቃዊ የጋዛ ክፍል እንደሚወጣ እና የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ወደቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚፈቀድላቸው ተገልጿል።
በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዲገቡም ይፈቀዳል።
በሁለተኛው የስምምነቱ ዙር ተጨማሪ ታጋቾች የሚለቀቁ ሲሆን፣ የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ እና “ዘላቂ መረጋጋትን ማምጣት” ያለመ ሲሆን ይህም የሚተገበረው የመጀመሪያው ዙር 16 ቀን ሲሞላው ነው።
ሦስተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍ ጋዛን መልሶ መገንባት ሲሆን፣ ይህም ዓመታት ይወስዳል።
በዚህ ምዕራፍ የታጋቾች አስክሬንም ይመለሳል።
እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ46,870 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።
ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።