ከ 4 ሰአት በፊት
ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ፣ ጥር 12/ 2017 ዓ.ም ዕለት ወደ ዋይት ሃውስ ይመለሳሉ።
47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ባሉት ሰዓታት ውስጥ “ብዙ ነገር እንደሚቀይሩ” የገቡትን ቃል እንደሚተገብሩ ይጠበቃል።
እንደህገ ወጥ ስደት፣ የአየር ንብረት ህግጋት፣ ሚስጥራዊ ሰነዶች እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቶች ወደ ዋይት ሃውስ ሲገቡ የተለያዩ የሥራ አስፈጻሚ ትዕዛዞችን ፈርመው ወደ ሥራ ማስገባታቸው የተለመደ ነው። እንደዚህ አይነት ትዕዛዞች በቀጣይ ፕሬዚዳንቶች ወይም በፍርድ ቤቶች ውሳኔ ሊሻሩ ይችላሉ።
ትራምፕ ያቀዱት ነገር ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ሊሆን ይችላል።
ውሳኔያቸው የህግ ተቃውሞ እንደሚደርስበትም ይጠበቃል
በዚህ ጉዳይ ላይ ማወቅ ያለብዎት ነገሮች የሚከተሉት ናቸው።
ስደት እና ድንበር
ማባረር
ትራምፕ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ “በአሜሪካ ታሪክ ትልቁን የማባረር ፕሮግራም ለመጀመር ቃል ገብተዋል።
ፎክስ ኒውስ እንደዘገበው ከሆነ ብሔራዊ የድንበር የአደጋ ጊዜ ያውጃሉ ተብሎ ይጠበቃል። የአገሪቱ ጦርም ደቡባዊውን ድንበር እንዲጠብቁ ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የፌዴራል የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት በአብያተ ክርስቲያናት እና ትምህርት ቤቶች ላይ ፍተሻ እንዳያካሂዱ ያደረገውን የረዥም ጊዜ ፖሊሲ እንደሚያስቆሙም ትራምፕ ተናግረዋል።
የጅምላ ማባረር ዕቅዱ የሎጂስቲክስ ችግሮች፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እና በርካታ የህግ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሙት ይጠበቃል።
በሜክሲኮ ይቆዩ
ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ወደ 70 ሺህ የሚጠጉ የጥገኝነት ውሳኔያቸውን የሚጠባበቁ ጥገኝነት ጠባቂዎች በሜክሲኮ እንዲቆዩ ያደረገውን “በሜክሲኮ ይቆዩ” የሚለውን ፖሊሲያቸውን እንደገና ለመተግበር በፍጥነት ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ።
በመወለድ የሚገኝን ዜግነት ይቆማል
በአሜሪካ ምድር የተወለደ ማንኛውም ሰው አሜሪካዊ ዜጋ ነው የሚለው እና ለ150 ዓመት የዘለቀውን ህገ-መንግስታዊ መብት “አስቂኝ ነው” ሲሉ የገለጹት ትራምፕ፤ ህጉን በመጀመሪያው ቀን እንደሚሽሩት ቃል ገብተዋል።
በመወለድ የሚገኝ ዜግነት በአሜሪካ ህገ መንግስት በግልጽ የተረጋገጠ በመሆኑ ይህንን ለማስፈጸም ትዕዛዝ በማውጣት ብቻ መቀየር የበለጠ ከባድ ይሆናል።
በጤና ሰበብ ድንበር መዝጋት
እአአ በ1944 ”ታይትል 42 በሚል የወጣ አሠራር የአሜሪካ መንግስት የህብረተሰብ ጤናን ለመጠበቅ ሲል ድንበር ሊዘጋ እንደሚችል ያሳውቃል።
ለመጨረሻ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው የኮቪድ ወረርሽን በተከሰተበት ወቅት ነው። የዩናይትድ ስቴትስ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ አዲሱ አስተዳደር ደቡባዊ አሜሪካን ከሜክሲኮ ጋር የሚያገናኘውን ድንበር ለመዝጋት እንዲረዳው ምክንያት የሚሆን በሽታ እያፈላለገ ነው ።
የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች
ትራምፕ የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎችን ልክ እንደ አልቃይዳ፣ እስላማዊ መንግስት እና ሐማስ “የውጭ አሸባሪ ድርጅቶች” በማለት ይፈርጇቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
አጥሩን መገንባት
ትራምፕ እአአ በ2016 ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዝዳንት ሆነው ሲመረጡ፣ የድንበር አጥር ለመገንባት የሥራ አስፈፃሚ ትዕዛዝ ፈርመዋል። የተወሰኑ የአጥሩ ክፍሎች ቢገነቡም፤ ሙሉ ሙሉ ባለመጠናቀቃቸው ምክንያት ፕሬዝዳንቱ የጀመሩትን ለመጨረስ ሊሞክሩ ይችላሉ።
- ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ቀናቸው በርካታ ትዕዛዞችን ለማስተላለፍ ቃል ገቡ20 ጥር 2025
- ለቁልፍ ኃላፊነቶች በትራምፕ እምነት የተጣለባቸው አስሩ ባለሥልጣናት እነማን ናቸው?20 ጥር 2025
- ስለ ዶናልድ ትራምፕ በስፋት የማይታወቁ ስምንት እውነታዎች20 ጥር 2025
ንግድ እና ኢኮኖሚ
ታሪፎች
ትራምፕ ለአሜሪካ ምርቶች ቅድሚያ ለመስጠት በገቡት ቃል መሠረት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ታሪፍ እንደሚጥሉ ቃል ገብተዋል ።
ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው አንዳንድ ታሪፎችን አስተዋውቀዋል። በቻይና ላይ የተጣሉትን ጨምሮ አንዳንዶቹን ጆ ባይደን አስቀጥለዋቸዋል።
አሁን በሁሉም ምርቶች ላይ 10 በመቶ ታሪፍ ለመጣል ቃል ገብተዋል። 25 በመቶ የካናዳ እና የሜክሲኮ እቃዎች ላይ ሲጥሉ 60 በመቶ ከቻይና በሚመጡ ምርቶች ላይ ለመጣል ቃል ገብተዋል። በመጀመሪያው ቀንም እነዚህን የማስፈጸሚያ ትዕዛዞች በመፈረም እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።
ታሪፉ የፍጆታ ዕቃዎችን የበለጠ ውድ እንደሚያደርገው እና የዋጋ ንረቱን ሊያባብሰው እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ። አንዳንድ አገሮችም አሜሪካ ላይ ታሪፍ ለመጣል እያሰቡ ነው።
የክሪፕቶ ክምችት
ትራምፕ ክሪፕቶፕን በማወደስ ላይ ሲሆኑ መመረጣቸውም የቢትኮይንን ዋጋ በ 30 በመቶ ኣድጎታል።
አንዳንዶች ትራምፕ የፌዴራል “ቢትኮይን ክምችት” ለመፍጠር በፍጥነት እንደሚንቀሳቀሱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ይህም ከአሜሪካ የወርቅ እና የዘይት ክምችት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ስትራቴጂካዊ ክምችት ነው። “ሁሉንም አሜሪካውያን የሚጠቅም ቋሚ ብሄራዊ ሀብት” ሆኖ ያገለግላል ሲሉ ትራምፕ ገልጸዋል።
የአየር ንብረት እና ኃይል
የጆ ባይደን የአየር ንብረት ፖሊሲዎችን መሰረዝ
ተሰናባቹ ፕሬዝደንት አረንጓዴ ልማቶችን ለማሳደግ፣ ብክለትን ለመቆጣጠር እና መሠረተ ልማትን በገንዘብ ለመደገፍ ያወጧቸው ተከታታይ መመሪያዎች፣ ህጎች እና የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራሞች እንደ ትልቅ ስኬታቸው ይመለከታሉ።
ትራምፕ ብዙዎቹን መቀልበስ እንደሚፈልጉ ግልጽ አድርገዋል። በባህር ዳርቻ እና በፌዴራል መሬት ላይ የቁፋሮ ገደቦችን ለማስወገድ አስፈፃሚ ትዕዛዞችን ይጠቀማል ተብሎ ይጠበቃል።
አዳዲስ የንፋስ ኃይል ፕሮጀክቶችን ለማገድ እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አገልግሎት ለመሰረዝም ቃል ገብተዋል።
ድጋሚ ከፓሪስ ስምምነት መውጣት
ትራምፕ ወደ ስልጣን በመጡ በስድስተኛው ወር እአአ በ2017 ከፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት ራሳቸውን አገለሉ። ስምምነቱ የዓለምን ሙቀት መጨመርን ለመገደብ የተነደፈ ጉልህ ዓለም አቀፍ ስምምነት ነበር።
ባይደን እአአ በ 2021 ዋይት ሃውስ በገቡ የመጀመሪያው ቀን ወደ ስምምነቱን በድጋሚ ለመቀላቀል ተንቀሳቅሰዋል። ትራምፕ ደግሞ እንደገና ከስምምነቱ እንደሚወጡ ይጠበቃል።
የካፒቶል ብጥብጥ
የካፒቶል አመጹን ያነሳሱትን ተጠርጣሪዎች ነጸ ማውጣት
ከ 2021 የአሜሪካው ካፒቶል ብጥብጥ በኋላ የተፈረደባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ትራምፕ ወደ ቢሮ ሲመለሱ ይቅርታ እንደሚደረግላቸው በመጠባበቅ ላይ ናቸው።
“ለአብዛኞቹ ይቅርታ ለማድረግ እፈልጋለሁ። ለሁሉም ሰው ማለት ግን አልችልም ምክንያቱም የተወሰኑት ምናልባት ከቁጥጥር ውጭ ሆነዋል”ሲል ለሲኤንኤን ተናግረዋል።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከአንድ ሺህ 500 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል። 600 ያህሉ የፌደራል ባለስልጣናትን በማጥቃት ወይም በመከልከል ተከሰው ነበር።
ሚስጥራዊ ሰነዶች
እሑድ ዕለት ባደረጉት የቅድመ ቃለ መሃላ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ትራምፕ እንደተናገሩት ከሆነ እአአ በ1963 ከተገደሉት ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ግድያ ጋር የተያያዙ ሚስጥራዊ ሰነዶችን ይፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋልል። ግድያው ለቁጥር የሚያዳግቱ የሴራ ፅንሰ ሃሳቦች በር የከፈተ ነው።
በሴናተር ሮበርት ኬኔዲ እና በሲቪል መብቶች መሪ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ላይ እአአ በ 1968 ከተፈጸሙት ግድያዎች ጋር በተያያዘ የተሰበሰቡ ሰነዶችም በተመሳሳይ ይለቀቃሉ ብለዋል።
የውጭ ፖሊሲ
የዩክሬን ጦርነት
ትራምፕ በፕሬዚዳንትነታቸው የመጀመሪያ ቀን ግጭቱን እንደሚያቆሙ በምርጫ ዘመቻው ወቅት ተናግረው ነበር። ከዚያን በኋላ ግን ስድስት ወር ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ተናግሯል። በመጀመሪያዎቹ ቀናት ምን ሊያደርጉ እንደሚችል ግን ግልጽ አይደለም።
ኩባ እና ቬንዙዌላ
ባይደን በቅርቡ ኩባን ከዩናይትድ ስቴትስ የሽብርተኝነት ድጋፍ ሰጪ አገራት ዝርዝር ውስጥ ለማስወገድ ያሳለፉትን ውሳኔ ለመቀልበስ ትራምፕ የሥራ አስፈፃሚ ትዕዛዞችን ሊጠቀሙ ይችላሉ። በቬንዙዌላ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ወደነበረበት መመለስም ይችላሉ። ሁለቱም አገራት በመጀመርያው የአስተዳደር ዘመናቸው በተደጋጋሚ ውርጅብኛቸው ደርሷቸዋል።
ብዝሃነት እና ጾታ
ብዝኃነት፣ ፍትሃዊነት እና አሳታፊነት
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአሜሪካ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና ተቋማት ሴቶችን እና አናሳ ብሔሮችን ለመደገፍ የተነደፉ ፖሊሲዎችን አጽድቀዋል።
“በብዝሃነት፣ ፍትሃዊነት እና አሳታፊነት” ስር የሚመደቡት እነዚህ አሠራሮች ብዙ ወግ አጥባቂዎችን አስቆጥተዋል። ህጋዊ ጥያቄም ተነስቶባቸዋል። ትራምፕ አሠራሩን ለማስቀረት ቃል ገብተዋል። እንደሜታ፣ ዎልማርት እና አማዞን ያሉ ታላላቅ ኩባንያዎችም አሠራሩን ማስወገድ ጀምረዋል።
ትራምፕ የፌደራል መንግሥት የገንዘብ ድጋፍን ብዝኃነት፣ ፍትሃዊነት እና አሳታፊነት ላላቸው ትምህርት ቤቶች ወይም ሌሎች ተቋማትን እንዳይደርስ የሚከለክል የሥራ አስፈፃሚ ትዕዛዝ ሊጠቀምሙ ይችላሉ። “ወሳኝ የዘር ንድፈ ሃሳብ” የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶችን የገንዘብ ድጋፍም ሊከለክሉ ይችላሉ።
ፅንስ ማቋረጥ
ከእርሳቸው በፊት እንደነበሩት አብዛኞቹ የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንቶች ሁሉ ትራምፕም የፅንስ ማቋረጥ ምክር ለሚሰጡ ዓለም አቀፍ ቡድኖች የፌዴራል መንግሥት ዕርዳታን የሚከለክለውን “የሜክሲኮ ሲቲ ፖሊሲን” ወደነበረበት ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ፆታ የቀየሩ (ትራንስጀንደር) ሴት ስፖርተኞች
ትራምፕ በትምህርት ቤቶች እና በጤና አጠባበቅ ውስጥ “የጾታ መቀየር እብደት” በማለት የሚጠሩትን ጉዳይ በተደጋጋሚ ተችተዋል። በተለይም ጾታቸውን ሴት የቀየሩ ትራንስጄንደር ሴቶች፣ በሴቶች ስፖርት ላይ እንዳይወዳደሩ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
ቲክቶክ
ትራምፕ እሑድ ጥዋት፣ ጥር 11/ 2017 ዓ.ም በቻይናው ባለቤትነት የተያዘው ቲክ ቶክ ከሥራ ውጭ እንዳይሆን የሚከለክል ትዕዛዝ እንደሚያስተላልፉ ቃል ገብቷል።
መመሪያቸው የኩባንያውን 50 በመቶ ድርሻ ለመግዛት የሚችል የአሜሪካ አጋር ለማግኘት ጊዜ እንደሚሰጠው ተናግረዋል።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም የቲክ ቶክን እገዳ ደግፈው ነበር።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በተካሄደው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዘመቻ ወቅት ቪዲዮዎቻቸው በመድረኩ ላይ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዕይታዎችን በማግኘታቸውን ሃሳባቸውን መቀየራቸውን ተናግረዋል።