ከ 3 ሰአት በፊት
ከወራት በፊት ቻይና ውስጥ መንገድ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ በሚያሽከረክረው መኪና ጥቃት ፈጽሞ ቢያንስ 35 ሰዎችን በመግደል ጥፋተኛ የተባለው ግለሰብ በሞት ተቀጣ።
ባለፈው ኅዳር የተፈጸመው ይህ የተሽከርካሪ ጥቃት በቻይና ውስጥ በአሥርታት ያልታየ አሰቃቂ ድርጊት ነው ተብሏል።
ፋን ዌክዩ የተባለው ግለሰብ 62 ዓመቱ ሲሆን፣ በዙሀይ ከተማ ከሚገኝ ስታድየም ውጪ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እያደረጉ የነበሩ ሰዎች ላይ መኪና በመንዳት ገጭቶ በርካቶችን ሲገድል ሌሎችን አቁስሏል።
ከዚህ ጥቃት ከቀናት በኋላ ሌላ ጥቃት በመፈፀም ስምንት ሰዎችን የገደለው የ21 ዓመቱ ዡ ጂጃንም በሞት ተቀጥቷል።
ሁለተኛው ጥቃት የተፈፀመው በውዢ ከተማ ዩኒቨርስቲ አቅራቢያ ያሉ ሰዎችን በስለት በመውጋት ነበር።
ፋን ዌክዩ የተባለው ግለሰብ ከሚስቱ ጋር ከፈጸመው ፍቺ በኋላ በነበረው የሃብት ክፍፍል “ደስተኛ ስላልነበረ” ጥቃቱን እንደፈፀመ ተገልጿል።
ጥቃቱን በፈፀመበት ቦታ ራሱ ላይ ጉዳት አድርሶ በፖሊስ ከተያዘ በኋላ የሕዝብን ደኅንነት አደጋ ላይ በመጣል ተከሷል።
ፍርድ ቤቱ ጥቃቱን “እጅግ የከፋ” ሲል ነበር የገለጸው። ግለሰቡ ሞት ከተፈረደበት ከአንድ ወር በኋላ ነው ቅጣቱ የተፈፀመው።
- እስራኤል 90 ሴቶች እና ታዳጊ እስረኞችን ስትፈታ ሐማስ ሶስት ታጋቾችን ለቀቀ20 ጥር 2025
- ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ቀናቸው በርካታ ትዕዛዞችን ለማስተላለፍ ቃል ገቡ20 ጥር 2025
- በማንቸስተር ዩናይትድ ታሪክ ደካማው ቡድን ሳይሆን አይቀርም- ሩበን አሞሪምከ 9 ሰአት በፊት
ሌላኛው ጥቃት ፈጻሚ ደግሞ ዡ ጂጃን የተባለ ግለሰብ ሲሆን “አነስተኛ ውጤት ስላለው እና ዲፕሎማ ማግኘት ስላልቻለ” ጥቃቱን እንደፈፀመ ተገልጿል።
ፖሊስ እንዳለው ግለሰቡ ድርጊቱን መፈፀሙን አምኗል።
ፍርድ ቤት የሞት ቅጣት ሲያስተላልፍ ድርቱን “በጣም መጥፎ” ሲል ገልጾታል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ቻይና የሞት ቅጣት በመፈፀም ከዓለም ቀዳሚዋ አገር ናት።
በቻይና ውስጥ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሞት ቅጣት ይፈፀምባቸዋል።
አገሪቱ ስለ ሞት ቅጣት ዝርዝር መረጃ ስለማታወጣ ትክክለኛ ቁጥሩን ለማወቅ ያስቸግራል።
ቻይና ውስጥ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ላይ የሚደርስ ጥቃት እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ የጥቃት አድራሾቹ ይህንን ወንጀል የሚፈጽሙት “ማኅበረሰብን ለመበቀል” በሚል እንደሆነ ተገልጿል።
በአገሪቱ ውስጥ የግል ቂምን በማያውቋቸው ሰዎች ላይ የሚወጡ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ የተገለጸ ሲሆን፣ እአአ በ2004 መሰል 19 ጥቃቶች ደርሰዋል።
ሁለቱ በሞት የተቀጡ ሰዎች ጥቃት ከፈፀሙ በኋላ በቻንግዴ ከተማ አንድ ግለሰብ ወላጆች እና ልጆች በተሰበሰቡበት መኪና በመንዳት 30 ሰዎችን አቁስሏል።
ሁዋንግ ዌን የተባለው ግለሰብ በኢንቨስትመንት የደረሰበትን ኪሳራ እና የቤተሰብ ፀብ ተከትሎ ጥቃቱን መፈፀሙ ተገልጿል።
ጥቃት ፈጻሚው ባለፈው ወር የሞት ቅጣት የተላለፈበት ሲሆን፣ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ሌላ ወንጀል ካልሠራ ወደ ዕድሜ ልክ እስራት ሊለወጥለት ይችላል።
በተከታታይ የተፈፀሙ ጥቃቶች ቻይናውያን እንዴት ቁጣቸውን ያስተናግዳሉ የሚለው ላይ ጥያቄ አስነስቷል።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የቻይና ማዕከል የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ጆርጅ ማግነስ “ሰዎች በምጣኔ ሃብት መቀዛቀዝ የተማረሩ ይመስላል። በቀጣይም እየተባባሰ የሚሄድ ይሆናል” ብለዋል።