” እየሄዳችሁበት ያለው መንገድ ሁሉንም የሚያጠፋ ፤ የተገኘችውንም ሰላም የሚያደፈርስ በመሆኑ ህዝባችሁ የሚሰጣችሁ ምክር እና ተግሳፅ ተቀብላችሁ በስክነት እና በማስተዋል የህዝባችሁን ጥያቄ እንድትመልሱ አደራ እንላለን ” – ቅዱስነታቸው
ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ለትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት ጌታቸው ረዳ እና ለህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ምክር እና ተግሳፅ አስተላለፉ።
ቅዱስነታቸው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ጥር 6/2017 ዓ/ም በፃፉት ደብዳቤ ነው።
ቅዱስነታቸው በዚሁ ደብዳቤ ፤ ሁለቱን አመራሮች በአካል አግኝተው ለማነጋገር እንዳልተሳካላቸው ገልፀው ሁኔታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ መሄዳቸው አሳስቧቸው ለመሪዎቹ ሃሳባቸው በፅሁፍ ለመገለፅ መገደዳቸው አስፍረዋል።
አመራሮቹ በትግራይ ያለው ጊዜ የማይሰጥ ተደራራቢ ችግር ከመፍታት ይልቅ ከመደማመጥ እና መከባበር በወጣ አኳኋን እርስ በርስ በመዘላለፍ መጠመዳቸው እንዳሳዘናቸው ጠቅሰዋል።
መሪዎቹ ጥበብን እና የሰለጠነ አሰራርን እንዲታጠቁ መክረዋል።
ቅዱስ ፓትርያርኩ ፤ ” ካህናት አበው ፣ የቤተክርስትያን ሊቃውንት ፣ ምእመናን ፣ የአገር ሽማግሌዎች የዕድሜ ባለፀጎች በሃዘን እያነቡ አካሄዳችሁን እንድታስተካክሉ ሲለምኗችሁ እና ሲመክሯችሁ ሰክናችሁ ማሰብ እና ማዳመጥ የተሰናችሁ ምክንያት ምን ይሆን ? ” ሲሉ ጠይቀዋል።
” ‘ የእኔ አካሄድ ብቻ ነው ልክ ‘ በሚል እልህ እና አስተሳሰብ የፈረሰ እንጂ የተገነባ ህዝብ እና አገር የለም ” ሲሉ በአፅንኦት ያስገነዘቡት ቅዱስነታቸው ፤ ” የናንተ መለያየት አልበቃ ብሎ በአንድነት እና በመከባበር የኖረውን ህዝብ ለማራራቅ እየሄዳችሁበት ያለው ርቀት ህዝብን ለማገልገል መቆማችሁን ጥያቄ ውስጥ የሚከት የጥፋት እና የመጠፋፋት መንገድ በመሆኑ ቆም ብላችሁ አስቡ ” ሲሉ አሳስበዋል።
ይህ ሳይሆነ ከቀረ መሪዎቹ እየተከተሉት ያለው የጥፋት መንገድ የተገኘውን ሰላም የሚያደፈርስ አገርን እና ህዝብን ለከባድ ቀውስ የሚያጋልጥ እንደሆነ አስረግጠው ገልጸዋል።
የተፈጠረው የሃሳብ አለመጣጣም ለመፍታት ከአመራሮቹ አቅም በላይ እንዳልሆነ ያስታወሱት ቅዱስ ፓትርያርኩ ፥ መሪዎቹ ችግሮቻቸው በጥበብ እና በሰለጠነ አሰራር በመፍታት ጅምር ሰላሙን በማፅናት ህዝባቸውንና አገራቸውን በልማት ለመካስ ከልብ እንዲተጉ የአባትነት ምክራቸውን ደግመው ደጋግመው አስተላልፈዋል።
ጥር 6/2017 ዓ.ም ተፅፎ ዛሬ ጥር 11/2017 ዓ.ም በበዓለ ጥምቀቱ ይፋ የሆነው የቅዱስነታቸው የምክር እና የተግሳፅ ደብዳቤ ወደ ትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት ፅህፈት ቤት መድረሱን የቲክቫህ ኢትዮጵያ መቐለ አባል በስልክ ደውሎ አረጋግጧል።
እስካሁን ለደብዳቤው የተሰጠ ምላሽ የለም።