የእርጅና ሥነ ውበትና ታሪካዊ ዕሴት…(The Aesthrtics of Ageing and Historical Value) ( በጌታሁን ሃራሞ )
ጂዮርጅ ጊልበርት ስኮት እ.ኤ.አ. ከ1811-1878 በምድረ እንግሊዝ የኖረ ዕውቅ የ”Gothic Revival” አርክቴክት ነበር፡፡ በሕይወት ዘመኑ ይበልጥ የሚታወቀው እንግሊዝ ውስጥ የሚገኙ እድሜ ጠገብ ካቴድራሎችን በማደሱ ነበር፡፡ ሆኖም ስኮት በዕድሳቱ ወቅት ይከተለው የነበረው የ”Restoration” መርህ በወቅቱ ከነበሩ የኪነ ሕንፃ ሐያሲያን፣ የታሪክ ምሁራንና ፈላስፎች ውግዘትን ያስከትልበት ነበር፤ ከዕድሳት ጋር በተገናኛ ሰውዬው እንደልቡ የሚባል ዓይነት አርክቴክት ነበር፤ ስኮት ሲያሰኘው የዕድሜ ጠገቡን የካቴድራሉን ዕድሜ ጠገብ ኮርኒስ ፕላስተርንግ ሙሉ በሙሉ በማስነሳት በእንጨት እስከመተካት ይደርስ ነበር፤ አንዳንዴም በሕንፃው አርክቴክቼራል አካላት ላይ እስከ 4 ሜትር ቁመት በራሱ ሥልጣን ይጨምር ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ የቅርቡ የሆኑ ወደዳጆቹና ተማሪዎቹም ሳይቀሩ…ይኄማ ከ”Restoration”ንም የዘለለ የ“Remodelling” ሥራ ነው… በማለት ድፍረት የተሞላበትን የስኮትን የዕድሳት አካሄድ ይቃወሙ ነበር፡፡
ይሁንና ጂዮርጅ ጊልበርት ስኮት ከሌሎች አርክቴክቶችና ምሁራን ለሚሰነዘርበት የሂስ ናዳ ግድ የሌለው ሰው ነበር፤ አልፎ ተርፎም “I am not a medieval architect” በማለት በጥንታዊ ሕንፃዎች ላይ የራሱን ወቅታዊ አሻራዎች ለማሳረፍ ይደፍር ነበር፤ ሆኖም ይህ ሽሽቱ በተለይም በዕድሜ ማብቂያው አካባቢ የሚያዋጣው ሆኖ አልተገኘም፡፡ እንደ ዊሊያም ሞሪስ ያሉና ለዕድሜ ጠገብ ቅርሶች ክብር ያላቸው አርክቴክቶች ይህ ሰው በጊዜ የእንደልቡ-ዕደሳቶቹን እንግሊዝ አለኝ በምትላቸው ቅርሶች ላይ መተግበሩን ካለቆመ ጉዳቱ ለማረም አዳጋች ወደሆነ ደረጃ ሊሸጋገር እንደሚችል ለእንግሊዝ ማህበረሰብ አሳወቁ፡፡ አደጋው ያሳሰባቸው አርክቴክቶች፣ የአርክቴክቸር ሐያሲያንና የታሪክ ምሁራን፣ በስኮት የዕድሳት ወንጀሎች ዙሪያ ቀን ቀጥረው ተወያዩ፤ የውይይታቸውም መቋጫ ጥንታዊ ኪነ ሕንፃዊ ቅርሶች በ”Restoration” ሰበብ ጊዜና ዘመን ያሳረፈባቸው አሻራቸው እንዳይደመሰስ የሚከላከል ማህበር እ.ኤ. አ. በ1877 ዓ.ም. መሰረቱ፡፡ የማህበሩም ስያሜ “The Society for the Protection of Ancient Buildings…SPAB” እንዲሆን ተወሰነ፡፡ የማህበሩ ተቀዳሚ ዓላማም ታሪካዊ ሕንፃዎች ላይ የሚተገበረው አውዳሚ ዕድሳትን (Destructive Restoration) ለሕዝብ ይፋ በማድረግ መቃወምና ማስቆም ነበር። በማህበሩ የምሥረታ ስብሰባ ላይ ከተገኙት ጎምቱና ዕውቅ የኪነ ሕንፃ ሐያሲያን መካከል ጆን ረስኪን ተጠቃሽ ነው፡፡ ከእሱ በተጨማሪ እንግሊዛዊው የታሪክና የህግ ምሁር ጄምስ ብራይስ፤ እንግሊዛዊው ሳይንትስት ጆን ለበክ፤ ስኮትላንዳዊው ፈላስፋና የታሪክ ምሁር ቶማስ ካርላየል እና ሌሎችም ተገኝተው ነበር፡፡ “SPAB” በአሁኑ ወቅት ከእንግሊዝ በተጨማሪ በአይርላንድ፤ በስኮትላንድና በዌልስ ቅርንጫፍ ቢሮዎች አሉት፤ በፈረንሳይና ጀርመን ሀገርም ያሳረፈው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም።
ከላይ ጠቀስ እንዳደረኩትና ስያሜው እንደሚጠቁመው የ”SPAB” ተቀዳሚ ተግባሩ ጥንታዊ ህንፃዎች በስመ “Restoration” በጊዜ ጅረት ውስጥ የተጎናፃፉት አሻራ እንዳይደመሰስ ጥበቃ ማድረግ ነው፡፡ ይህን ዓላማ ሰንቀው እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አርክቴክቶችና የታሪክ ምሁራን በእንግሊዘኛው አጠራር “preservationist” ተብለው ይጠራሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከላይ ጆን ረስኪን እ. ኤ.አ. በ1849 ዓ.ም. በ”The Seven Lamps of Architecture” መፅሐፉ ያስቀመጠውን በግርድፉ በመተርጎም እንደሚከተለው ላስቀምጥ
“ሕዝቡም ይሁን የሕዝብን ቅርስ የሚጠብቁ፣ ተሃድሶ(Restoration)” ለሚለው ቃል ያላቸው ግንዛቤ ትክክለኛ አይደለም፡፡ “ተሃድሶ” ማለት አንድ ሕንፃ ሊያስተናግዳቸው ከሚችላቸው አደጋዎች ሁሉ የከፋው ነው፡፡ የመደምሰስ አዳጋ የተጋረጠበት ሕንፃም በስመ- ተሃድሶ ከመፍረሱ በፊት የሚከበበው በውሸት ገለፃዎች ነው፡ በጊዜ ሂደት ውብና ታላቅ የሆነውን የኪነ ሕንፃ ቅርስ መጀመሪያ ወደ ነበረበት ሁኔታ ለመመለስ መሞከር የሞተን ሰው ከሞት ለማስነሳት እንደማሰብ ይቆጠራል፡፡”
ጆን ረስኪን እ.ኤ.አ. በ1874 ዓ.ም. የ”RIBA”ን የወርቅ ሽልማት ላለመቀበል የወሰነው አንዳንድ የወቅቱ አርክቴክቶች በስመ-ተሃድሶ በኪነ ሕንፃ ቅርሶች ላይ የሚያደርሱትን የታሪክ አሻራን ውድመት በመቃወም ነበር፡፡ ይህ የጆን ረስኪን የታሪካዊ ህንፃዎች ፍቅርና ቅናት ወደ ዊሊያም ሞሪስም ተሸጋግሮ ነበር፤ አርክቴክቱ ዊሊያም ሞሪስ በወቅቱ ጊልበርት ስኮት በስመ ተሃድሶ የታሪክን አሻራ ስለመደምሰሱ የተናገረው ይህን ይመስላል፦
“እንግሊዝን ዝናኛ ያደረጉትን ጥንታዊ ሕንፃዎችን ከጥፋት ለመታደግ ጊዜው ረፍዷልን? ከእንግዲህ ታሪካዊ ሕንፃዎቻቸንን ከንፋስና ከመጥፎ የአየር ሁኔታ ለመከላከል ከምንወስደው ጥንቃቄ በበለጠ በተሃድሶ ስም ከሚደርሱ ጥፋቶችም በመታደጉ ሂደት ለህዝቡ በቂ ግንዛቤን የሚያስጨብጥና በሁለት እግሩ ቆሞ መሄድ የሚችል ማህበር መመስረት አለብን፡፡ ጥንታዊ ህንጻዎቻችን ከሰማይ የወረዱ አሻንጉሊቶች አይደሉም፤የህዝባችን ዕድገትና ተስፋ፣ የተከበሩ ቅርሶቻችን እንጂ! ” ምንጭ፤ Scrape and Anti Scrape , The Future of the Past, New York 1976። እንግዲህ ከዚህና መሰል ፀረ- አውዳሚ ተሃድሶ እንቅስቃሴዎች በኋላ ነበር ከላይ የጠቀስኩት የ’SPAB” ማህበር የተቋቋመው፡፡
ለመሆኑ ጥንታዊ ሕንፃዎችን ወደ ኋላ ለመመለስ የሚደረገው ሙከራ ቆሞ፣ ባሉበት ሁኔታ እንዲጠበቁና እንዲጠገኑ የተፈለገበት ምክንያት ምን ይሆን? Why Preservation? የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት አለበት፡፡ ታሪካዊ ሕንፃዎችን ለምን “Preserve” ማድረግ እንዳለብን ከሚጠቁሙ ምክንያቶች ውስጥ የተወሰኑትን እንደሚከተለው ላቅርብ፦
1. ጥንታዊ ሕንፃዎቻቸን እኛን ከትናንት ጋር የሚያቆራኙን አካላዊ(Physical) እሴቶቻችን ናቸው፡፡ እርጅናቸው የራሳቸውን የትናንት ማንነትን ብቻ ሳይሆን የኛንም የትናንት ማንነታችን ጠቋሚ አሻራዎች ናቸው፡፡ ይህን የጥንታዊ ሕንፃዎቻችንን ተፈጥሮአዊ ጉዞአቸውን አስቁሞና አርትፊሻል በሆነ መልኩ በስመ ተሃድሶ ወደ ኋላ ቀልብሶ ከዜሮ ለማስጀመር መሞከር፣ ጦርነቶች በቅርሶች ላይ ከሚያደርሱት አደጋ ጋር የሚነጻጻር ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በዕድሜ መመንደግ የተነሳ የተሸበሸበ ቆዳን በፕላስቲክ ሰርጀሪ ወደ ልጅነት ዘመን ቆዳ ለመመለስ እንደመሞከር ነው፡፡
አንድ ጥንታዊ ሕንፃ ዕድሜው እየጨመረ በመጣ ቁጥር ታሪካዊ ዋጋውም እኩል ይጨምራል፡፡ ዕድሜው የሥነ ውበቱ(Aesthetics) አንዱም ገፅታው ነው፡፡ በዚህ መልኩ በእርጅና ውስጥ የተሰወረ ውበትን አንዳንዶች “The Aesthetics of Ageing” በማለት ይጠሩታል፡፡ ቢገባንም ባይገባንም ጥንታዊ ሕንፃዎችን በአካል በምንጎበኝበት ወቅት አንድም የምናጣጥመው ይህን ዕድሜ የወለደውን ውበት ነው፡፡ ይህ እውነት የገባት ጣሊያናዊቷ የአካዳሚ አዋርድ አሸናፊ አና ማግኒያኒ ለሜኬአፕ አርትስቷ ሰርክ የምትሰጠው ማስጠንቀቂያ ይህን ይመስል ነበር፦ “Don’t touch any of my wrinkles; it took me ages to get them…growing old gracefully” የፋሲል ቤተመንግስትም አፍ ቢኖረው ኖሮ ልክ እንደ አና ማግኒያኒ…Don’t touch my patina…” የሚል ግብረ መልስ ይሰጥ ነበር፡፡
2. ጥንታዊ ሕንፃዎችን ባሉበትሁኔታ “preserve” ማድረግ ያለብን፣ ቅርሶች ዕድሜአቸውን ለቱርስቶች የሚናገሩት የጊዜ አሻራ ባረፈባቸው የፊት ገጽታዎቸው በመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በአሁኑ ወቅት ቀደም ሲል የፋሲልን ቤተመንግስት ጎብኝቶ የማያውቅ አንድ ቱርስት ወደ ጎንደር አቅንቶ የሕንፃዎቹን ዕድሜ ከፊት ገፅታዎቻቸው ለመገመት ቢሞክር ውዝግብ ውስጥ ነው የሚገባው፡፡ አሁን የተነካካው የሕንፃዎቹ ገፅታ ዕድሜውን በተመለከተ ለቱርስቱ የሚሰጠው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው፤ “Restoration” የጥንታዊ ሕንጻዎችን “Authenticity”ን መቀመቅ ከትቶ ለተመልካች የተሳሳተ መረጃን ይሰጣል የሚባለውም ከዚህ የተነሳ ነው፡፡
3. ከጥንታዊ ሕንጻዎቻችን ጋር ያለን ቁርኝት ከታሪካዊና ከዕድሜ ጠገብነት ባሻገር ከወልና ከግል ትውስታዎቻቻንም(Collective and Individual Memories) ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ትውስታና የምንኖርበት አካባቢ ያላቸው ቁርኝት እጅግ ጥልቅ ነው፡፡ ጥንታዊ ሕንፃዎች የተለመደው ነባሩ መልካቸው በተሃድሶ ሰበብ ሲደመሰስና አዲስ ገጽታን ሲላበሱ ቀደም ሲል ከነበረው ገፅታ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ትውስታዎቻችንም አደጋ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ወፎች ያረፉበት ዛፍ ሲቆረጥባቸው ሌላ ዛፍ ፍለጋ ከለመዱበት እንደሚፈናቀሉ ትውስታዎቻችንም ተፀንሰው ከተወለዱበት ቀዬአቸው ይፈናቀላሉ፤ በሂደትም ደብዛቸው ይጠፋል፡፡ ይህ ክስተት በመንግስታት ለፖለቲካ ጥቅም ሊውል እንደሚችል የሚያሳዩ አያሌ ጥናቶች አሉ፡፡ One can call that “The Politicization of Architecture”. ማንዴላ ለ27 ዓመታት ከታሰረበት ከሮበን ደሴት እንደተፈታ በነዚያ ዓመታት ሁሉ የቁም ስቅል ሲያሳዩ የነበሩ ዘረኛ የአፓርታይድ ፖሊሲ አራማጆች ነባሩን የእስር ቤት ገፅታውንና አካባቢውን ለማጥፋት ያላደረጉት ሙከራ አልነበረም፡፡ ዓለማቸው ነባሩን ገፅታ በመለወጥ እነ ማንዴላ ለጥቁሮች መብት የከፈሉትን ዋጋ ለማረሳሳትና የእነሱንም የግፍ ትውስታን ከጥቁሮቹ አዕምሮ ማጥፋት ነበር፡፡ ስለዚህም ማንዴላ እንደተፈታ ታስሮ የነበረበት አካባቢ ወደ “Zoo” እንዲቀየር ሐሳብ አቀረቡ፡፡ ተንኮላቸውንና ዓላማቸውን ቀድመው የተረዱ ጥቁር የደቡብ አፍሪካ አርክቴክቶች ግን የነጮቹን ሐሳብ ውድቅ አደረጉ፡፡ ከቦታው ጋር የተቆራኘውና ለጥቁሮች መብት መከበር የተከፈለው የመስዋዕትነት ትውስታ እንዳይደመሰስ ቦታው በሙዚየምነት ተሰይሞ በሕዝብ እየተጎበኘ እንዲቀጥል ወሰኑ፡፡
የቦታና የትውስታ ቁርኝት ከእኛም የዕለት ተዕለት ህይወታችን የተሰወረ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሰው የቤተሰብ አባሉን በሞት በሚያጣበት ወቅት ነባሩን ትውስታ ለማጥፋት የሚሞክረው ሰፈር በመቀየር ነው፡፡ ይህ ካልተቻለም የቤቱን የውስጥና የውጭ ቀለም እንዲሁም አቅሙ ካለ ሟቹ ሲጠቀምባቸው የነበራቸው እቃዎችን ሙሉ በሙሉ መቀየር አላአስፋላጊ ትውስታዎችን ከመርሳት አኳያ የበኩሉን አስተዋፅዖ ያደርጋል፡፡ ቀለም ሲቀየር መልካምም ሆነ መጥፎ ትውስታ ይፈናቃለል፡፡ በነገራችን ላይ የቀለምና የትውሰታ ቀርኝት በፊልም እንዱስትሪውም(Cineamatographic Colors) የአንድ ፊልም ቀለማት በሚወሰኑበት ወቅት በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውል ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡
4. ሌላውና መሠረታዊው የ”Preservation” ጠቀሜታ በቀደመው ፅሑፌ ጠቀስ እንዳደረኩት ከኦሪጅናሊቲ ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ በተለይም የጥንታዊ ሕንፃዎች የመጀመሪያ ቀለማቸው ምን እንደነበረ በእርግጠኝነት ማስቀመጥ በጣም አስቸጋሪ የሚሆንበት አያሌ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ምክንያቱም ሕንጻዎቹ በታነፁበት ወቅት እንኳንስ የከለር ፎቶግራፊ ቴክኖሎጂ ይቅርና የጥቁርና ነጭ የፎቶግራፊ ቴክኖሎጂሞ ከነአካቴው ላይኖር ይችላል፡፡ ስለዚህም እርግጠኛ ባልሆንንበትና በቂ መረጃ በሌለን ሁኔታ ውስጥ ሆነን …ሕንፃው ሲታነፅ ቀለሙ ነጭ ነበር…በሚል ውሳኔ ወደ “Restoration” ሥራ ውስጥ መግባት የቅርሱን ኦሪጂናሊቲ ለያሳጣው ይችላል፡፡ ከዚህ ውሳኔ ይልቅ በጊዜ ቅብብሎሽ እጃችን የገባውን ታሪካዊ ቅርስ በ”Preseravtion” መርህ ባለበት ሁኔታ ጠብቆ መንከባከቡ የተሻለ ይሆናል፡፡
ለማጠቃላል ያህልም አንዳንድ ወዳጆቻችን የፋሲል ቤተመንግስት ተሰርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ማሄሱ ምንም ትርጉም የለውም ለማለት ሲሞክሩ አያስተዋልን ነው፡፡ በመሠረቱ ሂስ በየትኛውም የጥበብ ዘርፍ የሚሰጠው በተጠናቀቀ ሥራ ላይ ነው፤ ለምሳሌ በሥነ ፅሑፍ ዓለም ባልተፃፈ መፅሐፍ ላይ ሂስ አይሰጥም፤ በተመሳሳይ መልኩ ገና ለመድረክ ባልቀረበ ቲያትር ላይም ሂስ አይቀርብም፡፡ ሂስ በዋናነት በግብዓትነት ጥቅም ላይ የሚውለው ወደፊት በሚሰሩ የጥበብ ሥራዎች ውስጥ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚነስትር የሆኑት ሰላማዊት ካሳ በጥቅምት 23 2017 ዓ.ም. የጎንደር ፋሲል ቤተመንግስትን ከጎበኙ በኋላ ቀጣይ መሰል ፕሮጀክቶችን በተመለከተ የተናገሩትን ፋና በእንግሊዘኛ አምዱ የዘገበው እንደዚህ በማለት ነበር፦
“She mentioned that the work of developing tourist destinations is being undertaken in different cities of the country. In addition to the ongoing renovationto Fasil Ghebbi, maintenance work has also started in Jimmaand other historical places.”
ከዚህ በኋላ የፋሲል ቤተመንግስትን ገጽታ ወደነበረበት ታሪካዊ አሻራና የእርጅና ውበት መመለስ ከባድ ነው፡፡ መደማመጡ ካለ አሁን በየአቅጣጫው እየሰነዘሩ ያሉ ሂሶች በቱሪዝም ሚስትሯ በቀጣይነት እየተሰሩ እንዳሉ ይፋ በሆኑ ፕሮጀክቶች ጥቅም ላይ ቢውሉ መልካም ይመስለኛል፡፡
ይህ ፅሑፍ ባዘጋጁበት ወቅት በዋናነት በዋቢነት የተጠቀምኩት የሚከተሉትን መፅሐፍት ነው፡፡
1. The Ageing of Materials and Structures: Towards Scientific Solutions for the Ageing of Our Assets, Edited by Klaas van Breugel and 2 more.
2. A Richer Heritage: Historic Preservation in the Twenty-First Century, by Robert E. Stipe
3. Historic Preservation Technology: A Primer
By Robert E. Stipe
4. William Morris and the Society for the Protection of Ancient Buildings,
By Andrea Elizabeth Donovan
5. Why Old Places Matter: How Historic Places Affect Our Identity and Well-Being, By Thompson Mayes
6. The Place of Collective Memory in the Study of Historic Preservation, by Melinda J. Milligan
(Journal Article)
አመሰግናለሁ