በደምሰው ሽፈራው
በአዲስ አበባ ከተማ ባለፈው መንፈቅ ዓመት በይፋ የተመዘገበው የፍቺ መጠን፤ አምና በተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ34 በመቶ መጨመሩን የከተማይቱ የሲቪል እና የነዋሪነት ምዝገባ አገልግሎት ኤጀንሲ አስታወቀ። በዚሁ ጊዜ የተመዘገበው የጋብቻ መጠን፤ ባለፈው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከተመዘገበው በሰባት በመቶ መቀነሱንም ኤጀንሲው ገልጿል።
ተቋሙ ይህን የገለጸው የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸሙን አስመልክቶ፤ ዛሬ ማክሰኞ ጥር 13 በዋና መስሪያ ቤቱ በሰጠው መግለጫ ነው። የመታወቂያ ስርጭት፣ የልደት እና የሞት ምዝገባ፣ ያላገባ የምስክር ወረቀት፣ የማስረጃ የማረጋገጥ ስራን ለመዲናይቱ ነዋሪዎች የሚሰጠው ኤጀንሲው፤ በከተማይቱ የተከናወኑ ጋብቻ እና ፍቺዎችንም ያከናውናል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ፤ መስሪያ ቤታቸው ባለፉት ስድስት ወራት የመዘገበው ፍቺ 3,769 መሆኑን በዛሬው መግለጫ ላይ አመልክተዋል። ኤጀንሲው ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የመዘገበው ፍቺ 2,832 እንደነበር የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የዘንድሮው የፍቺ መጠን በ34 በመቶ ጭማሪ ያሳየ እንደሆነ አስገንዘበዋል።
በአንጻሩ ባለፈው መንፈቅ ዓመት በኤጀንሲው የተመዘገበው የጋብቻ መጠን፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲወዳደር በሰባት በመቶ መቀነሱን ተቋሙ አስታውቋል። የሲቪል እና የነዋሪነት ምዝገባ አገልግሎት ኤጀንሲ ባለፈው ስድስት ወራት የተመዘገበው የጋብቻ መጠን 15,574 ነው። መስሪያ ቤቱ በዚሁ ጊዜ ለመመዘገብ አቅዶ የነበረው የጋብቻ ብዛት 21,674 ነበር።
የከተማይቱ ነዋሪዎች “አስገዳጅ ሁኔታዎች ካላጋጠሟቸው በስተቀር” ወደ ተቋሙ በመምጣት ወሳኝ ኩነቶችን የማስመዝገብ ልምዳቸውን “አነስተኛ” መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የዘንድሮው የጋብቻ መጠን ለመቀነሱ ይህ አንዱ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። “ሰዉ፤ ፎቶ መነሳት ብቻ ጋብቻ ይመስለዋል” ያሉት አቶ ዮናስ፤ በህብረተሰቡ ዘንድ ጋብቻን ማስመዘገብ ያለውን ጥቅም እና አስፈላጊነት “በአግባቡ ያለመረዳት” ችግር እንዳለ ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)