January 21, 2025
ከተለያዩ ክልሎች መሸኛ በመያዝ በአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት ምዝገባ ለማግኘት ከጠየቁ አመልካቾች ውስጥ፤ ከ25 ሺህ በላይ የሚሆኑት ያቀረቧቸው ሰነዶች ለተጨማሪ ምርመራ ለሚመለከታቸው አካላት እንደተላኩ የከተማይቱ የሲቪል እና የነዋሪነት ምዝገባ አገልግሎት ኤጀንሲ ገለጸ። የመሸኛ ማስረጃዎች የተላኩላቸው ክልሎች፤ ምርመራቸውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አጠናቅቀው ምላሻቸውን ያሳውቃሉ ተብሏል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኘው የሲቪል እና የነዋሪነት ምዝገባ አገልግሎት ኤጀንሲ ይህን የገለጸው፤ የዘንድሮውን በጀት ዓመት የመንፈቅ የስራ አፈጻጸም በተመለከተ በዛሬው ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። መግለጫውን የሰጡት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ በመግለጫው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል “የመሸኛ አገልግሎት” እንደገና መጀመር ይገኝበታል።
ተቋሙ ከሌሎች ክልሎች ወደ አዲስ አበባ መጥተው በከተማ ነዋሪነት ለመመዘገብ ጥያቄ ካቀረቡ አመልካቾች ውስጥ በአንድ ሶስተኛው ላይ “የመሸኛ አገልግሎትን” አግዶ መቆየቱን አቶ ዮናስ በዛሬው መግለጫ ላይ አስታውሰዋል። እገዳው የተጣለባቸው “በቂ ምክንያት ሳይኖራቸው” ወደ አዲስ አበባ ከተማ “የተዘዋወሩ” አመልካቾች ላይ እንደሆነም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
“በስራ ዝውውር፤ ያ ማለት ስራቸው እዚህ በቋሚነት የሆኑ፤ በትዳር ምክንያት ወደዚህ ለተዘዋወሩ እና ለሌሎች አገልግሎት ስንሰጥ ቆይተናል። ቤተሰብ ወደዚህ move እያደረገ ያለ፣ በትምህርት ወደዚህ የተዘዋወረ፣ ለህክምና ወደዚህ የመጣ፣ ‘የአዲስ አበባ የአየር ንብረት ለራስ ጤና የተሻለ ነው’ ለተባለ ሰው፤ አገልግሎት እየሰጠን ቆይተናል” ሲሉ አቶ ዮናስ አብራርተዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ለተቋሙ የመሸኛ ሰነዳቸውን አስገብተው፤ የነዋሪነት ምዝገባ ለማከናወን ጥያቄ ያቀረቡ ሰዎች ብዛት 57,214 መሆናቸውን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የእነዚህ አመልካቾች መረጃ በመስሪያ ቤቱ ማዕከል ተጠናቅሮ መቀመጡን ዋና ዳይሬክተሩ በዛሬው መግለጫቸው አመልክተዋል።
“ይህ መረጃ ሲጠናቀር፤ ማን ነው እሱ? ከየት መጣ? ወዘተ የሚለውን መረጃ ተንትነናል። በዚህ መሰረት የአዲስ አበባ ከተማን የመሸኛ ደረጃ አሟልተው approve የተደረጉ [አሉ]። [ከእነዚህ] ውጭ ያሉት፤ የመረጃ ጉድለት እና ትክክለኛነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያጠራጥሩ፣ ያልተሟሉ መሸኛዎች መሆናቸውን አይተናል” ሲሉ አቶ ዮናስ ሂደቱን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
“እኛ ባገኘነው መረጃ ሀሰተኛ መሸኛዎች ወደ ከተማችን ይመጣሉ። መሸኛዎቹ በትክክል የሰዎቹን ማንነት የሚገልጹ፣ ከመዋቅሩ ያልወጣ፣ ወይም ደግሞ ማንነታቸውን ቀይረው የመጡ ስለመሆናቸው ባደረግነው ማጣራት ውስጥ እንደዚህ አይነት መረጃዎችን አግኝተናል”– አቶ ዮናስ አለማየሁ፤ የአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል እና የነዋሪነት ምዝገባ አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር
“እኛ ባገኘነው መረጃ ሀሰተኛ መሸኛዎች ወደ ከተማችን ይመጣሉ። መሸኛዎቹ በትክክል የሰዎቹን ማንነት የሚገልጹ፣ ከመዋቅሩ ያልወጣ፣ ወይም ደግሞ ማንነታቸውን ቀይረው የመጡ ስለመሆናቸው ባደረግነው ማጣራት ውስጥ እንደዚህ አይነት መረጃዎችን አግኝተናል” ሲሉም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አክለዋል።
የአዲስ አበባ የነዋሪነት ምዝገባ ጉዳይ ከከተማው “ሰላም፣ ጸጥታ፣ ደህንነት ጋር የሚገናኝ” እንደሆነ የጠቆሙት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር፤ የመሸኛ ሰነዶችን ላይ የታዩ አጠራጣሪ ጉዳዮችን ክልሎች አጣርተው እንዲልኩ የማድረጉ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ተቋሙ “ሊጣሩ ይገባሉ” ያላቸውን 25,581 የመሸኛ ደብዳቤዎች፤ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ እንዲሁም ለክልሎች መላኩን በዛሬው መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።
“ይህ ማጣራት የሚያመጣቸው ሁለት ጉዳዮች ይኖራሉ። አንድም በምንሰጠው አገልግሎት ውስጥ ለከተማ ነዋሪነት የሚያመለክቱ ሰዎች ይዘው የሚቀርቡት ማስረጃ ምን ያህል ትክክለኛ ነው? ፎርጂድ ነው፤ አይደለም? በውስጡ የማንነት ስርቆት አለው፤ የለውም? አበበ የነበረው፤ ከበደ ሆኖ መጥቷል ወይስ አልመጣም? ብለን እናጠራለን። ሰውየው ራሱ እዚያ አካባቢ exist ያደርጋል ወይ? የቀበሌ ሊቀመንበርም እንበለው የወረዳ አስተዳደር፤ ይህን ተቋም የሚመራው እዚያ ክልል ላይ ያለው ደብዳቤውን የሰጠው አካል፤ ትክክለኛ መረጃ ልኳል ወይ? ተጣርቶ ሲመጣ የምንደርስበት ይሆናል” ሲሉ ከምርመራው የሚጠበቀውን ውጤት አቶ ዮናስ አብራርተዋል።
ለኤጀንሲው መሸኛ አስገብተው በመጠባበቅ ላይ ካሉ አመልካቾች ውስጥ የ9,504ቱ ተጣርቶ የነዋሪነት ምዝገባ ፈቃድ እንዲያገኙ መደረጉንም የመስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር በዛሬው መግለጫቸው ላይ አንስተዋል። እነዚህ አመልካቾች መስሪያ ቤቱ ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ቀርበው ሪፖርት ያደረጉ እና የፋይዳ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ያከናወኑ ናቸው ተብሏል።
የተሰጣቸውን የመሸኛ ደብዳቤ ለተቋሙ አስገብተው የነዋሪነት ምዝገባ ሲጠባበቁ የነበሩ “በጣም ብዙ ሰዎች” አገልግሎቱ በመታገዱ ምክንያት መቸገራቸውን ያመኑት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር፤ በዚህ ምክንያት ለተፈጠረው ችግር አመልካቾችን በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል። አገልግሎቱ የዘገየው፤ የአዲስ አበባ ከተማን ህዝብ “ሰላም፣ ጸጥታ እና ደህንነት” ለማረጋገጥ ሲባል እንደሆነም አስረድተዋል።
መረጃዎችን ለማጣራት በሚደረገው ጥረት ላይ በአመልካቾች ዘንድ ተገቢውን ምላሽ የመስጠት ችግር እንደሚስተዋልም አቶ ዮናስ አመልክተዋል። “ ‘ኑና ሪፖርት አድርጉ፣ እኛም ወደ ክልሎች እንልካለን፣ አጣርተንም ተገቢውን አገልግሎት እንሰጣችኋለን’ ስንል የሚንጠባጠበውም ሰው ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ እንድታውቁት ነው” ሲሉ መዘግየቱ በኤጀንሲው በኩል ብቻ የሚስተዋል እንዳልሆነ አስገንዘበዋል።
“መሸኛን ማጥራት” በተመለከተ፤ የአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል እና የነዋሪነት ምዝገባ አገልግሎት ኤጀንሲ በቀጣይ “አዲስ አሰራር” የመዘርጋት እቅድ እንዳለው ዋና ዳይሬክተሩ በዛሬው መግለጫቸው ጥቆማ ሰጥተዋል። አዲሱ አሰራር “ግለሰቦች ከከተማ ከተማ እንዳይጨበረብሩ፣ ማንነታቸውን እንዳይቀይሩ አጋዥ ይሆናል” ሲሉም ተስፋቸውን አጋርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)