January 23, 2025

እነዶ/ር ደብረፅዮን እና በጠ/ሚ ዐብይ አህመድ በተሾሙት የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት መሪዎች እነጌታቸው ረዳ መካከል የነበረው አለመግባባት ተካርሮ ሰራዊቱን ወደውግንና አስገብቷል።
የትግራይ ሐይል አዛዦች ትላንት ባወጡት መግለጫ ውግንናቸው ከእነዶ/ር ደብረፅዮን ጋር መኾኑን አስታውቀዋል።
የትግራይ ሐይል አዛዦች በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ያለው ሃምሳ ሲደመር አንድ ድርሻ እንዲረከብ እንደሚሹ አቋማቸውን ይፋ አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ያሉ ታጣቂዎች በትግራይ ሰላም እና ፀጥታ ሴክሬታሪያት ስር እንዲሆኑ፥ ከዚህ ውጪ በሆነ ላይ ግን እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
በሌላ በኩል ፓርቲውን ለማፍረስ እና አመራሩን ለመበተን እያሴሩ ነው በማለት ህወሓት የኢትዮጵያ መንግስትን እና የምርጫ ቦርድን ወንጅሏል። በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራዉ የህወሓት ክንፍ ቁጥጥር ኮምሽን ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ በአስቸኳይ የህወሓት ሕጋዊነት ሰውነት ሊመለስ ይገባል ብሏል።
በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ትላንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ
የትግራይ ሐይል አዛዦች ያስተላለፉት ውሳኔ በትግራይ ሥርዓት አልበኝነትን የሚያነግስ ነው በማለት አስቸኳይ የካቢኔ ስብሰባ መጥራቱን ይፋ አድርጓል።
መግለጫው እንደሚለው የትግራይ ሐይሎች ከፍተኛ አዛዦች “ከተልእኳቸው ውጭ ለአንድ ሕገወጥ ቡድን ወግነው ግዚያዊ አስተዳደሩን የማፍረስ፣ ስርዓት አልባነት የማንገስ እና ሰራዊት የመበተን ግልፅ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን አሳውቀዋል” ብሏል።
የትግራይ ሐይል አዛዦች በትላንትናው ዕለት ያስተላለፉትን ውሳኔ ግዚያዊ አስተዳደሩ የማያውቀውና “ሕጋዊ ይሁን ሞራላዊ ቅቡልነት የሌለው” ሲል ያመለከተው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር መግለጫ፤ ከዚህ በተጨማሪ የፕሪቶርያ ውልንም ለአደጋ የሚያጋልጥ እና ኃላፊነት የጎደለው ብሎታል።
(ከጀርመን ድምፅ ተወስዶ የተቀናበረ)