ጄፍ ቤዞስ እና ሊላን መስክ
የምስሉ መግለጫ,ቢሊየነሮቹ ጄፍ ቤዞስ እና ሊላን መስክ

ከ 5 ሰአት በፊት

ብሉ ኦሪጂን የተሰኘው የጄፍ ቤዞስ የጠፈር ኩባንያ በፍሎሪዳ ከሚገኘው ኬፕ ካናቬራል የጠፈር ጣቢያ ኒው ግሌን የተባለውን ሮኬት ወደ ምህዋር ለማምጠቅ በዝግጅት ላይ ነው።

ሰኞ ዕለት ለማምጠቅ የተያዘው መርሃ ግብር በቴክኒክ ችግር ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተላልፏል። የአማዞን መሥራቹ ቤዞስ ሙከራውን በድጋሚ እንደሚያከናውን ይጠበቃል።

የኢላን መስክ ስፔስኤክስ ኩባንያ ደግሞ በዚህ ረገድ በርካታ ስኬታማ ገድሎችን ፈጽሟል። ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የግዙፉን ስታርሺፕ አካል መልሶ ማስወንጨፊያው ላይ እንዲያርፍ በማድረግ ስኬታማ ሆኗል።

የሁለቱ ቢሊየነሮች የጠፈር ኩባንያዎች የተመሠረቱት ከ20 ዓመታት በፊት ነው። ስፔስኤክስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቀዳሚ ሀኖ በመገስገስ ላይ ይገኛል። የኒው ግሌን ፕሮጀክት ያለ እንከን ከተከናወነ በሁለቱ ባለፀጎች መካከል ያለውን ክፍተት ምን ያህል ያጠበዋል?

ስፔስኤክስ እና ብሉ ኦሪጅን ምን አሳኩ?

ስፔስኤክስ በአውሮፓውያኑ 2008 ፋልከን 1 የተሰኘውን ሮኬቱን ወደ ምህዋር ለማድረስ በቅቷል። በ2012 ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ (አይኤስኤስ) ዕቃ አጓጉዟል። እስካሁን ከ400 በላይ የሚሆኑ ፋልከን 9 ሮኬቶችን ወደ ህዋ አምጥቋል። ሳተላይቶችን፣ ጠፈርተኞችን እና ዕቃ ወደ አይኤስኤስ በስኬት አድርሷል።

ብሉ ኦሪጅን ኒው ሼፐርድ ሮኬቱን አስወነጭፏል። ዘጠኝ ሰዎችን ማሳፈር ችሏል። ወደ ጠፈር ቢጓዝም ወደ ምህዋር መግባት አልሆነለትም። እስካሁን ድረስ መንኮራኩር ወደ ምህዋር አላመጠቀም።

ሁለቱም ኩባንያዎች ሮኬት በሰዎች ቁጥጥር እየተደረገበት እንዲያርፍ እና እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ፈር ቀዳጅ ሆነዋል። ይህም የጠፈር ጉዞ ዋጋ በጣም ዝቅ እንዲል በር ከፍተዋል።

ስፔስኤክስ ሁለት ትላልቅ መንኮራኩሮችን ሠርቷል፡ ፋልከን ሄቪ እና ስታር ሺፕ ይሰኛሉ። ፋልከን ሄቪ አገልግሎት እየሰጠ ያለ እና እስካሁን ከተሠሩት ትልቁ እና ከፍተኛ ጉልበት ያለው የጠፈር መንኮራኩር ነው። ስታርሺፕ ስድስት ሙከራዎችን አድርጎ ሁለት ጊዜ አስገራሚ ፍንዳታዎች ገጥሞታል።

በ2024 ደግሞ ስፔስኤክስ በዓለም የመጀመሪያውን “ቾፕስቲክ” የተሰኘ ሙከራ አከናወነ። በዚህም መሠረት የስታርሺፕ የታችኛው ክፍል ወደ ማስወንጨፊያው ሲመለስ አየር ላይ በሁለት ግዙፍ መካኒካዊ ‘እጆች’ ይያዛል።

አማዞኑ መሥራች ጄፍ ቤዞስ
የምስሉ መግለጫ,አማዞኑ መሥራች ጄፍ ቤዞስ

የብሉ ኦሪጂን ኒው ግሌን ከፋልከን ሄቪ ቢበልጥም ግን ከስታርሺፕ ያነሰ ነው።

የኒው ግሌን የጉልበት መስጫም እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውል ታስቦ የተሠራ ነው።

ከመጠቀ በኋላ የጉልበት መስጫው ከተቀረው ሮኬት በመለየት በቤዞስ እናት ጃክሊን ስም ተሰይሞ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ በሚገኝ እና ለዚሁ ተብሎ በተሠራ መርከብ ላይ እንዲያርፍ ነው ዓላማው።

ብሉ ኦሪጂን በመጀመሪያው ሙከራው በተሳካ ሁኔታ ማረፍ “ትልቁ ስኬቱ” እንደሚሆን በመግለጽ የሚጠብቀው ነገር ውስን መሆኑን ግልጽ አድርጓል።

የብሉ ኦሪጅን በጠፈር ቱሪዝም መርሃ ግብር ትንሹ የጠፈር ተመራማሪ ሆነውን የ18 ዓመቱን ኦሊቨር ዴመንን፣ የ90 ዓመት አዛውንቱን ኤድ ድዋይትን ወደ ጠፈር ጫፍ ወስዷል። የስታር ትሬክ ተዋናዩ ዊልያም ሻትነር እና ቢሊየነሩ ቤዞስ ተካተውበታል።

“ስፔስኤክስ በፍጥነት ዕድገት እንዳሳየ እና ከብሉ ኦሪጂን የበለጠ ስኬት እንዳስመዘገበ የሚካድ አይደለም” ሲሉ በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ የህዋ ጥናት ሥነ ምግባር እና ፖለቲካ ባለሙያው ዶ/ር ጂል ስቱዋርት ተናግረዋል።

“ዋናው ነገር የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በበርካታ ኩባንያዎች መካከል ውድድር እንዲኖር ፍላጎት አለው . . . ይህም ቅልጥፍናን እና ፈጠራን ያመጣል” ብለዋል።

ስፔስኤክስ ከመንግስት ጋር ብዙ ሥራዎችን የሚከውንበት ውሎች አሉት

ቢሊየነሮቹ ለምንድን ነው በህዋ ላይ ገንዘባቸውን የሚያፈሱት?

መስክ የኤክስ (የቀድሞው ትዊተር)፣ የቴስላ እና የስፔስኤክስ ባቤት ሲሆን የዓለማችን ቁጥር አንድ ሃብታም ነው።

የሰው ልጅ ለራሱ ህልውና ሲል “በበርካታ ፕላኔቶች” መኖር እንዳለበት አስታውቋል። የሰው ልጅ ማርስን ቅኝ መግዛት አለበት የሚለውን ራዕዩንም ለረዥም ጊዜ ተናግሯል።

“ያለ አንድ ሰው እውነተኛ ርዕዮተ ዓለማዊ ቁርጠኝነት፣ የጠፈር ሥልጣኔን ለማሳካት ለመሆን ምንም ዓይነት አቅጣጫ ያለን አይመስልም” ሲል እአአ በ2016 ዕቅዱን ዘርዝሯል።

የአማዞን መሥራች የሆነውን ጄፍ ቤዞስ የዓለማችን ሁለተኛው ሀብታም ሰው መሆኑን ፎርብስ አስታውቋል።

ብሉ ኦሪጂን ላይ የበለጠ ለማተኮር ቤዞስ በ2021 የአማዞን ዋና ሥራ አስፈፃሚነት ሥራውን ለቀቀ።

“ልጆቻችን እና ልጆቻቸው ዕታ ፈንታቸውን እንዲገነቡ በማሰብ የጠፈርን መንገድ ለመሥራት” ዓላማ እንዳለው ከዚህ ቀደም ተናግሯል። “እዚህ በምድር ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ይህን ማድረግ አለብን።”

ብሉ ኦሪጂን የተቋቋመው “በጠፈር ውስጥ የሚኖሩ እና ለምድር ጥቅም በሚሠሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ራዕይ ነው” ብሏል።

የቢሊየነሮቹ የጠፈር ውድድር እንደ አየር ንብረት ለውጥ እና ክትባት ላሉ ችግሮች የተሻለ ጥቅም ላይ የሚውል ገንዘብን በማይሆን ቦታ አውሏል በሚል አንዳንዶች ተችተዋል።

ለበርካታ ዓመታት ቁጥር አንድ ሃብታም በመሆን ሲመራ የነበረው የማይክሮሶፍት መሥራቹ ቢል ጌትስ “ወደ ማርስ መሄድ በጣም ውድ ነው። የኩፍኝ ክትባቶችን በመግዛት በአንድ ሺህ ዶላር ህይወት ማዳን ይቻላል” ሲል በ2023 ለቢቢሲ ተናግሯል።

የኒው ግሌን ማስወንጨፊያ

የኒው ግሌን ስኬት ምን ያመላክታል?

የኒው ግሌን በተሳካ ሁኔታ መጀመር ለብሉ ኦሪጂን “ትልቅ ምዕራፍ” ይሆናል። “የስፔስ ኢንደስትሪውን የውድድር ገጽታ መልሶ ሊቀይር ይችላል” ሲሉ የለንደን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት የስፔስ ፖሊሲ ፕሮግራም ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ዲሚትሪዮስ ስትሮኮስ ተናግረዋል።

“በረጅም ጊዜም የስፔስኤክስን ፋልከን 9 ጭነትን በእጥፍ የመሸከም አቅሙ የስፔእስኤክስን የበላይነት በእጅጉ ሊፈታተን ይችላል” ሲሉም አክለዋል።

የመስክ የበላይነት ግን “ከማስወንጨፍም በዘለለ” በስፔስኤክስ የስታርሊንክ ሳተላይቶች በዓለም ዙሪያ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት መስጠትንም እንደሚያካትት ዶ/ር ስትሮኮስ ተናግረዋል። እነዚህም ኩባንያው “በቴክኖሎጂ ተደራሽነት እና በዓለም አቀፍ ትስስር ላይ ከፍተኛ የበላይነት” እንደሚሰጡት ተናግረዋል።

ቁልፍ ፉክክር የሚሆነው ማን ትልቁን ሮኬት ማስወንጨፍ ቻለ የሚለው ላይሆን ይችላል። ዋናው ነገር የመንግሥት ኮንትራቶችን ማን አገኘ የሚለው ነው።

“የህዋ ምርምር እና ጉዞ አሁንም በመንግሥት ወጪ የተያዙ ናቸው። የግል ኩባንያዎች በዋነኛነት የሚወዳደሩት የመንግሥት ኮንትራቶችን በመሥራት ላይ ነው” ሲሉ በዱራም ዩንቨርስቲ የአስትሮ ፖለቲካ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ብሌዲን ቦወን ተናግረዋል።

ኢላን መስክ እና ጄፍ ቤዞስ
የምስሉ መግለጫ,ኢላን መስክ እና ጄፍ ቤዞስ

መስክ እና ቤዞስ ምን እና ምን ናቸው?

ሁለቱ ቢሊየነሮች በአደባባይ እርስ በርስ የመፎካር ታሪክ አላቸው።

ለምሳሌ እአአ በ2021 ብሉ ኦሪጅን በመስኩ ስፔስኤክስ ያጣውን የ2.9 ቢሊዮን ዶላር የናሳ ውልን በተመለከተ የፌደራል መንግሥቱን ከስሶ ነበር።

ብሉ ኦሪጂን በክሱ ቢሸነፍም ግን በኋላ ላይ ወደ ጨረቃ የሚደረግ ጉዞ ኮንትራት ተሰጠው።

ዶ/ር ስቱዋርት ወደፊት በርካታ ክሶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይናገራሉ።

“እንደ ኤለን መስክ ያሉ ሰዎች ቁጥጥር የሌለበት እንደሆነ ለማስመሰል ከመውደዳቸውም ባለፈ በህዋ ውስጥ የሚፈልጉትን ማድረግ እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። እውነታው ግን ወደ ጠፈር ጉዞ ከማድረግ በፊት በርካታ የደኅንነት ስጋቶችን እና የአካባቢ ጥበቃ ሂደቶችን ማለፍ አለባቸው” ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በመስክ እና በአዲሱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መካከል ያለው የጠበቀ ግንኙነት የግል ኩባንያዎች በአሜሪካ የጠፈር መርሃ ግብሮች የሚኖራቸው ተሳትፎ ምን ሊሆን ይችላል የሚል ግምት እንዲሰጥ አድርጓል።

ትራምፕ ሥልጣን በተረከቡበት ዕለት ባደረጉት ንግግር ላይ በመጪዎቹ አራት ዓመታት ለማሳካት ከሚፈልጓቸው ቁልፍ ጉዳዮች መካከል የአሜሪካንን ሰንደቅ ዓላማ ማርስ ላይ መትከል መሆኑን በመናገር ለህዋ ጉዞዎች ያላቸውን ትኩረት አመልክተዋል።

በመስክ እና በፕሬዝዳንት ትራምፕ መካከል ያለው የቀረበ ግንኙነት ቤዞስ በሚያደርገው ፉክክር ላይ ምንም የሚያሰጋው ነገር እንደሌለ ለሮይተርስ ተናግሯል።

“ኢላን ይህን የሚያደርገው ለሕዝብ ጥቅም እንደሆነ እና ለግል ጥቅሙ አለመሆኑን ግልጽ አድርጓል። ይህንንም ሙሉ ለሙሉ እወስደዋለሁ” ብሏል።

ከሰኞ የማስወንጨፊያ ሙከራ በፊት መስክ በኤክስ ላይ “መልካም ዕድል” በማለት ለብሉ ኦሪጂን ምኞቱን አስተላልፏል።

ብሉ ኦሪጂን ከስፔስኤክስ እኩል ለመጓዝ መሞከሩን ስለሚቀጥል፣ የወዳጅነት ስሜቱ ላይቆይ ይችላል።

የብሉ ኦሪጂን ኒው ግሌን ሮኬት
የምስሉ መግለጫ,የብሉ ኦሪጂን ኒው ግሌን ሮኬት