

የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ
ዜና ለመዋቅርና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎቻቸው ምላሽ የተነፈጉት የሲቪል አቪዬሽን ሠራተኞች እየለቀቁ መሆኑን ፓርላማው…
ቀን: January 26, 2025
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የመዋቅርና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ላቀረቡ የሠራተኞች ምላሽ በመንፈጉ የሠራተኛ ፍልሰት ማጋጠሙን፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማት ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ይህንን ያስታወቀው ጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም. የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማትን የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ሲገመግም ነው፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ታለፍ ፍትሐወርቅ፣ በሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የተጀመረው ሪፎርምና የሰው ኃይል አደረጃጀት የመዋቅር ጥናት አለመጠናቀቁን በመስክ ጉብኝት በተደረገ ምልከታ መረጋገጡን፣ የሠራተኞች አደረጃጀት መዋቅርና ጥቅማ ጥቅም ባለመስተካከሉ ምክንያት፣ ሠራተኞች ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ ባለማግኘታቸው ፍልሰት እያጋጠመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ዳንጌ ቦሩ ከቋሚ ኮሚቴው ጉዳዩን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ የመዋቅርና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ከዚህ ቀደም ሲነሳ የነበረ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ከባለሥልጣኑ ጋር በመሆን ከማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን፣ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ዘርፍን በተቀናጀ መንገድ ለማሻሻል ሁለት ዓበይት ጥናቶች ተደርገው ለኮሚቴው በሁለት ዙሮች መቅረቡን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና ሌሎችም ተጠሪ ተቋማት እንደሚገኙበት ገልጸው፣ ጥያቄዎች ተበታትነው ሳይሆን በአንድ ማዕቀፍ ይቅረቡ በመባሉንና ውይይት እየተደረገበት መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
‹‹እኛም ልዩ ትኩረት ከሰጠናቸው ጉዳዮች አንዱ የሠራተኞች የጥቅማ ጥቅም ጉዳይ ነው፤›› ብለው፣ በሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በኩል ስትራቴጂካዊ ጥናቶች እየተከናወኑ እንደሆነ፣ ለአብነትም ‹‹አቪዬሽን ፈንድ›› ይቋቋም የሚለው ይገኝበታል ብለዋል፡፡
የአቪዬሽን ፈንድ በማቋቋም ባለሥልጣኑ የራሱ ገቢ እንዲኖው በማድረግ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለምና በአፍሪካ ስመ ጥር እየሆነ በመምጣቱ፣ የተቋሙን የማስተዳደርና የመቆጣጠር አቅሙን ለማሳደግ ትኩረት በመሰጠቱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በዚህም የተቋሙ ሠራተኞች የመዋቅርና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄያቸውን ምላሽ ለማግኘት እየተጠባበቁ መሆናቸውን ነው አቶ ዳንጌ የገለጹት፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ቋሚ ኮሚቴው የአገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጡ አውሮፕላኖች ላይ ተደጋጋሚ የቴክኒክ ችግር እያጋጠመ እንደሆነ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ፣ አስተማማኝ የቅድመ በረራ የቴክኒክና የደኅንነት ኦዲት ቁጥጥር ሥራዎች ጥራት ምን ያህል እንደሆነ፣ ችግሩ እንዳይደገም በጥልቀት ፈትሾ የእርምት ዕርምጃ ከመውሰድ አንፃር ተቋሙ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል የሚልም ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ፣ ከአውሮፕላን የቴክኒክ ችግር አኳያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአየር ትራንስፖርት ደኅንነቱ በአስተማማኝነት የተጠበቀ ነው ብለዋል፡፡
‹‹ይህ እኛ ስላልነው ሳይሆን ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ኦዲት አድርጎ ከአፍሪካና ከአደጉ አገሮች ጭምር ውጤቱ የተሻለ ሆኖ መገኘቱን ነው፤›› ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የሌሎች አገሮችን የቴክኒክና መሰል ችግሮችን በተመለከተ ኦዲት እንደሚደረጉ የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ በግኝቱ መሠረት አጥጋቢ አፈጻጸም እንዳላቸው መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡
ያም ሆኖ አልፎ አልፎ በበረራ ወቅት የቴክኒክ ችግሮችና ሌሎች አደጋዎች እንደሚያጋጥሙ ገልጸው፣ እነዚህ አደጋዎች በሦስት ደረጃዎች እንደሚታዩ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ እስካሁን መካከለኛና ከፍተኛ ጉዳት ያስከተሉ የቴክኒክም ሆነ ሌሎች ችግሮች በተያዘው ስድስት ወራት ውስጥ እንደልተከሰተ ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ያጋጠመ ከፍተኛ አደጋ እንደሌለ ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ነገር ግን ከወፎች ጋር መጋጨትና መለስተኛ የቴክኒክ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ጠቁመዋል፡፡
እንዲህ ዓይነት ችግሮች ሲያጋጥሙ ባለሥልጣኑ ምርመራ እንደሚያደርግና ልዩ መለያውም አደጋ በድጋሚ እንዳይከሰት ማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ምክንያት አደጋ ተመልሶ የመድረስ አጋጣሚ ዝቅተኛ መሆኑን በመግለጽ፣ ከላይ የደረሱ ችግሮችና በኦፕሬተሮች በኩል የማሻሻያ ዕርምጃዎች እየተወሰደባቸው መሆኑን አቶ ጌታቸው አክለዋል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ አቶ ዓለሙ ስሜ በስድስት ወራት የተከናወኑ ጉዳዮችን ሲያብራሩ፣ መንግሥት የትራንስፖርት ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተለያዩ የአሠራር ማሻሻያዎችን፣ መመርያዎችንና ስታንዳርዶችን በማዘጋጀት ተግባራዊ የማድረግ ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል።
የተሽከርካሪ መቀመጫ ቀበቶ አጠቃቀም፣ የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ መግጠምና ማስተዳደር፣ የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ መመርያዎች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች ተደራሽነት ለማስፋት መናኸሪያዎችንና ደረቅ ወደብ ለአገልግሎት ምቹ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለአብነትም የሞጆ ደረቅ ወደብን ለማስፋፋት እየተከናወነ ያለውን ሥራ ጠቁመው፣ በአሁኑ ጊዜ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 80 በመቶ አካባቢ መድረሱንና በዘርፉ የግል ባለሀብቶች እንዲገቡበት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ መጨመር በዜጎች ላይ የሚያሳድረውን ጫና መቅረፍ የሚያስችል ሥራ ሲያከናውን መቆየቱን፣ ይህም ተጠናክሮ መቀጠሉን ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል።
ተገቢ ባልሆነ መንገድ የነዳጅ ድጎማን በሚጠቀሙ አሽከርካሪዎች ላይ አስፈላጊውን ሕጋዊ ተጠያቂነት ለማስፈን እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሚኒስቴሩ ለኅብረተሰቡ ቀልጣፋና የዘመነ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ሊበረታቱና ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል፡፡
‹‹የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ታሳቢ ባደረገ መንገድ የትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽነቱን ማዘመን የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅበታል፤›› ብለዋል።
የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የማሠልጠኛ ተቋማትን አሠራር መፈተሽና ማዘመን እንደሚገባ ገልጸው፣ ከሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላትን አቅም ማሳደግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡