የአዲስ አበባ ትሪፊክ ማኔጅመንት ውይይቱን ባካሄደበት ወቅት

ማኅበራዊ በአዲስ አበባ ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር ለሞት የሚዳርጉ አምስት መንገዶች መለየታቸው ተገለጸ

ሔለን ተስፋዬ

ቀን: January 26, 2025

በአዲስ አበባ ከተማ ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር ከፍተኛ የሞት አደጋ የሚያስከትሉ አምስት መንገዶች መለየታቸውን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት መምህር ተፈሪ አበጋዝ (ዶ/ር)፣ ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንትን ጨምሮ፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ስለመንገድ ደኅንነት ውይይት ሲደረግ እንደተናገሩት፣ ከፍተኛ የሞት አደጋ ያስከትላሉ ተብለው የተለዩት መገናኛ፣ ኃይሌ ጋርመንት፣ ቦሌ ሚካኤል፣ ጦር ኃይሎችና ቻይና ካምፕ መንገዶች ናቸው ብለዋል፡፡ በአማካይ በዓመት ከስድስት እስከ 13 ዜጎች በእነዚህ መንገዶች በሚደርሱ የተሽከርካሪ አደጋቸው ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ገልጸዋል፡፡

ከመንገዶቹ አንዳንዶቹ የእግረኛ መተላለፊያ እንደሌላቸው፣ አሽከርካሪዎች ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት ከፍጥነት ወሰን በላይ እያሽከረክሩ እንደሚያደርሱ አስረድተዋል፡፡

ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር በሚደርሰው የትራፊክ አደጋ፣ በአብዛኛው ሕይወታቸውን የሚያጡት ወንዶች እንደሆኑ የገለጹት ተፈሪ (ዶ/ር)፣ መገናኛ አካባቢ አደጋ ከደረሰባቸው 13 ሰዎች አብዛኞቹ ወንዶች መሞታቸውን አስረድተዋል፡፡ በተደረገው ዳሰሳም አደጋ የሚደርሰው ከቀኑ 6፡00 ሰዓት እስከ 8፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሆነ፣ በተለይም ሰንበት ወይም የዕረፍት ቀናት ከመንገድ መጨናነቅ ነፃ ስለሚሆኑ፣ ተከትሎ በፍጥነት ማሽከርከር ምክንያት የሞት ምጣኔው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ አደጋዎች የሚያሳዩት ተቆጣጣሪ ተቋማትም ሆኑ አደጋ አድራሾችና ተጎጂዎች የሚያደርጉት ጥንቃቄ ዝቅተኛ እንደሆነ ነው ገልጸዋል፡፡

ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ከባድ ተሽከርካሪዎች፣ ከሌሎች የተሽከርካሪ ዓይነቶች አብላጫውን አደጋ የሚያደርሱት ናቸው ብለዋል፡፡

በዓለም የጤና ድርጅት የትራፊክ አደጋ ሥጋት መንስዔዎች ተብለው የተለዩት በፍጥነት ማሽከርከር፣ ጠጥቶ ማሽከረከር፣ የደኅንነት ቀበቶ አለመጠቀምና የራስ ቅል መሸፈኛ አለመጠቀም ከፍተኛውን ቦታ እንደሚይዙ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2020 ድረስ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችሉ አራቱ የዓለም የጤና ድርጅት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ መሠራቱን ገልጸው፣ በአሁኑ ጊዜ ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር በ47 በመቶ መቀነሱን አክለዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም 43 በመቶ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አሽከርካሪዎች ከፍጥነት ወሰን በላይ እንደሚያሽከረክሩ፣ በዚህ ምክንያት ችግሩ ትኩረት ያሻዋል ብለዋል፡፡  

በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በየዓመቱ ከ400 የሚበልጡ ሰዎች በትራፊክ አደጋ እንደሚሞቱ የገለጹት ተፈሪ (ዶ/ር)፣ የጥናቶች የትኩረት አቅጣጫም የፍጥነት መገደቢያ መጠቀምና ሥር ነቀል የማኅበረሰብ ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡   

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ እንደገለጹት፣ በከተማዋ የመንገድ ደኅንነትን ለማስጠበቅ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

 ለትራፊክ አደጋ መከሰት መንስዔ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየትም የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን ጨምሮ የቁጥጥር ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣኑን ጨምሮ 15 ተቋማትን ያካተተ የመንገድ ደኅንነት ምክር ቤት በማቋቋም፣ የትራፊክ አደጋዎችን መቀነስ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተው፣ በቀጣይም የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሠራር ማጎልበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የብሉምበርግ ዓለም አቀፍ የበጎ ፈቃደኞች መርሐ ግብር ዋና ዳይሬክተር ሬቤካ ባቪንገር በበኩላቸው፣ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ሥራዎች በትኩረት መከናወን አለባቸው ብለዋል።

በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የእግረኛ መንገዶችን ማስፋፋት ጨምሮ፣ ሌሎች የመሠረት ልማቶች የትራፊክ አደጋ እንዲቀንስ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ላይ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች አመርቂ መሆናቸውን ገልጸው፣ የቁጥጥር ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውና የቀረበው ጥናት እ.ኤ.አ. በ2023 እና በ2024 የተሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡