ናርዶስ ዮሴፍ

January 26, 2025

አቶ መላኩ አለበል የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሪፖርቱን በፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ለአምራች ኢንዱስትሪ የቀረበው የውጭ ምንዛሪ ከዕቅዱ ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር በማነሱና እንዲሁም ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከታቀደው በ107 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ማለቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄ አስነሳ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ሐሙስ ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ለፓርላማ አባላት ባቀረቡት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ለአምራች ኢንዱስትሪ 468,420,000 ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማቅረብ ታቅዶ 369,110,000 ዶላር መቅረቡን፣ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 257 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ 149.34 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

ለአምራች ኢንዱስትሪው የቀረበው የውጭ ምንዛሪ ማነስን አስመልክቶ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ዕቅዱ ሙሉ በሙሉ ያልተከናወነበት ምክንያት፣ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ለማቅረብ የሚጠይቁት የማስያዣ ገንዘብ (deposit) መጠን ከወትሮው ከፍ ያለ በመሆኑ ነው፤›› ብለዋል።

በሌላ በኩል ከወጪ ምርት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በስድስት ወራት ለማግኘት ከታቀደው ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዝቅ ስላለበት ምክንያት ሲያስረዱም፣ ‹‹የተላከው የምርት መጠን ከፍተኛ ሆኖ የተገኘው የዶላር መጠን አነስተኛ የሆነበት ምክንያት፣ ወደ ውጭ የሚላኩት ምርቶች ዋጋቸው አነስተኛ (under invoice) ተደርጎ የሚወጡ በመሆናቸው ነው። ይህንን ችግር ለመቆጣጠር ወደ ውጭ የሚላኩ 29 ምርቶች ላይ ዝቅተኛ ዋጋ በመተመን ሥራ ላይ እንዲውል እየተደረገ ይገኛል። የዓለም አቀፍ ሁኔታዎች መቀያየር በተለይም የሎጂስቲክስ ዋጋ ግሽበትና የባህር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሥጋት፣ ወደ አውሮፓ ለመድረስ በመደበኛነት ከሚወስደው ከ45 ቀናት የማይበልጠውን ጊዜ ወደ 65 ቀናት እንዲያድግ አስገድዷል፡፡ ይህም በምርት ተወዳዳሪነት ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የስድስት ወራት ሪፖርቱ መደመጡን ተከትሎ የፓርላማ አባላት ለውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ይሆናሉ በሚል ስለተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች አፈጻጸም፣ የመንግሥት የስኳር ፋብሪካዎች ከሥራ ውጪ መሆን፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በአንድ ባትሪ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር በደረሰ ግምት አገሪቱን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የማስወጣት ሥጋትን የተመለከቱና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

በዚህም መሠረት ፈቲማ ሃዲ (ዶ/ር) የተባሉ ተወካይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የገቡ ዘርፎች ከአገሪቱ የረዥም ጊዜ ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ጋር እንዴት እንደሚጣጣሙ፣ በአጠቃላይ የፈጠሩት የሥራ ዕድል፣ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችንና ሸቀጦችን ከመቀነስ፣ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ከማምጣት፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር በተያያዘ ሙሉ መግለጫና ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቀዋል።

ፀዳለ አበራ የተባሉ ተወካይ በበኩላቸው፣ ‹‹የኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት በዋናነት የፌዴራል መንግሥት ማንዴት [ኃላፊነት] መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ እንደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ምንም ዓይነት የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ አልተከናወነም። ለፓርክ ግንባታ የሚሆን ቦታ ክልሉ አዘጋጅቶ ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ማስረከብ ቢችልም፣ እስካሁን ግንባታው አልተጀመረም፤›› በማለት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ቀጣይ ዕቅዱ ምን እንደሆነ እንዲያሳውቅ ጥያቄ አቅርበዋል።

አንድ ሌላ ተወካይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ትኩረት የሚያደርጉበት ዘርፍ በሚገነቡበት አካባቢ ካለው ፀጋ ጋር ተናቦ የሚከናወን መሆኑ ላይ ጥያቄ እንዳላቸው ገልጸው፣ ለአብነትም የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች አብዛኛው በሥራ ላይ እንደማይገኙ አስረድተዋል። ‹‹ኢንዱስትሪዎች ምን ያህል ተጠንተው ነው ወደ ሥራ የሚገባው?›› ሲሉ ጠይቀዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ጥያቄዎች በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ጥያቄዎች ናቸው። ይህንን ከዚህ በፊትም እንዳነሳነው አሁን ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ውጤታማነት ከዚህ በላይ ማሳደግና ምላሹን መለካት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል።

‹‹የምናወጣው እያንዳንዱ ገንዘብ ምን ያህል ትርፍ ይዞ ይመጣል የሚለውን መለካት መቻል አለብን። ከዚህ በፊት እንደተሠራጩት፣ በፖለቲካ እንደተዘሩት ዓይነት ኢንዱስትሪ ፓርኮች የምናደርገው ከሆነ ተመልሰን አገርን ዕዳ ውስጥ ነው የምናስገባውና ይህንን ታሳቢ ያደረጉ ውሳኔዎች ነው እየተሰጡ የሚሄዱት። ስለዚህ ከአጭር ጊዜ አኳያ አዲስ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንገነባም፣ መገንባት አለብን የሚል እምነትም የለንም። ያሉትን በደንብ ውጤታማ ማድረግ አለብን የሚል እምነት ተይዞ ነው እየተሠራ ያለው፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

ግብዓትን መሠረት ሳያደርጉ የተገነቡ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በተመለከተ በምሳሌነት ስለተነሳው የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተመለከተም አቶ መላኩ፣ ‹‹ጅማ ላይ ኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባቱ አስፈላጊና ተገቢ ትክክል ነው የሚል እምነት አለኝ። ግን ያ የምንገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ ምን ላይ ትኩረት (specialize) አድርጎ ነው መንቀሳቀስ ያለበት የሚለው ከአካባቢው የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ጋር መታረቅ መቻል ነበረበት፤ እዚያ አካባቢ የነበሩ ክፍተቶች ነበሩ፤›› ብለዋል። የጠቀሱትን ክፍተት የማስተካከል ሥራ እየተሠራ መሆኑንና በይበልጥ በአካባቢው የሚገኙ ጥሬ ዕቃዎችን ለመጠቀም ወደ ሚችል ኢንዱስትሪ ለውጥ እየተደረገ እንደሆነም አስረድተዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች አጠቃላይ ውጤታማነታቸው ሲታይ ተጨማሪ ጥናቶችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ነገር ግን በኢንዱስትሪ ሚኒስቴሩ በኩል ‹‹ለኢንዱስትሪ ፓርኮች በጣም የተጋነነ ዕይታ ነበር፡፡ ከሚገባቸው በላይ ዋጋ ሰጥተናል›› የሚል እምነት እንዳለ ገልጸዋል።

‹‹አሁን ባለው አጠቃላይ የኤክስፖርት ድርሻ ውስጥ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ካሉት ኢንዱስትሪዎች ይልቅ፣ ከፓርኮቹ ውጪ ያሉት ኢንዱስትሪዎች ያላቸው አስተዋጽኦ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው። እሱ ላይ አንዱ ትልቁ ችግር የጥሬ ዕቃ ትስስሩ (backward integration) ታስቦ ታቅዶ አልተሠራበትም። አብዛኞቹ በፓርኮቹ ውስጥ ያስገባናቸው ኢንዱስትሪዎች፣ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነውን ጥሬ ዕቃቸውን ከውጭ አምጥተው እንዲሠሩ በሚያስችል አካሄድ ነው የተሠራው፣ ይህ ትክክል አይደለም። የአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎችን ማሳደግ ማስፋት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል።

ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም. በተካሄደው መደበኛ ስብሰባ ከተገኙት የምክር ቤቱ አባላት መካከል ተስፋሁን ቦጋለ የተባሉ ተወካይ፣ ‹‹በሰጠናችሁ አዋጅ 1263/2014 የትኛውንም ፋብሪካ በአጋርነትና በቅንጅት እንደምትሠሩ ይታወቃል። የመንግሥት ስኳር ፋብሪካዎች አሁን በጣም ችግር ውስጥ ናቸው። የበለስ ስኳር ፋብሪካ ብቻን ብናነሳ በዓመት ወደ 242 ቶን ሊያመርት የሚችል ነው። አሁን ግን በኃይል አቅርቦትና በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሥራ አቁሟል፣ በማቆሙም የአራት ወር ደመወዝ ለሠራተኛው እየከፈለ አይደለም። ማነው ወደ ሥራ የሚያስገባው? እንዴት ነው ቅንጅታችሁ የሚለው ጥያቄ ከእኛ ጋ አለ፤›› ብለዋል፡፡

ተወካዩ ለአባላቱ ለጥያቄዎቻቸው መነሻ ምክንያቱን ሲያስረዱም፣ የስኳር ፋብሪካዎች ሞላሰስ የተባለ ኬሚካልና ስኳርን በግብዓትነት ለሚፈልጉ ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ወሳኝ በመሆኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በአዋጅ የተሰጡንን ግዴታዎች ተግባር ላይ እያዋልን ነው። ከዚህ በፊትም እዚሁ ምክር ቤት ላይ ተነስቶ እንደነበረው፣ የስኳር ፋብሪካዎቹ በጣም ውስብስብ ችግር ያለባቸው ናቸው፣ ከፋብሪካ ፋብሪካ ልዩነት አለ፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የስኳር ፋብሪካዎች ስላሉባቸው ተግዳሮቶች በሰጡት ገለጻም የተወሰኑት ከመሠረተ ልማት ጋር የሚያያዝ ችግር፣ አንዳንዶቹ ከመለዋወጫ ጋር የተያያዘ፣ ከእርሻቸው ጋር፣ እንዲሁም ከፀጥታ ጋር የተያያዘ ችግር ያለባቸውም ፋብሪካዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል።

ሚኒስቴሩ የፋብሪካዎችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በኩል የተቋቋመው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ካውንስል በዝርዝር ያልጠቀሱትን ሥራዎች እየሠራ ነው ብለው፣ ደረጃ በደረጃ ችግሩ ይቃለላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም፣ ‹‹ወደ ግል ድርጅቶች በሽያጭ እንዲዘዋወሩ (privatize) ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ስላሉ አንዳንዶቹ ከመንግሥት እጅ ወጥተው በግል ዘርፉ የሚመሩበት ሁኔታ እየታየ ስላለ እሱ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ ይችላል፤›› ብለዋል።

ፈቲማ (ዶ/ር) በበኩላቸው በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ሥር በቅርብ ጊዜ በከፍተኛ ቁጥር እየጨመረ የመጣው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የመጠቀም ልምድ በሰፊው እየታየ ወደ አገሪቱ የሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥርም የመገጣጠሚያ ፋብሪካዎች ብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪ አምራች ፋብሪካ አለመኖሩ በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ወጭ ላይ የደቀነውን ሥጋት ገልጸዋል።

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ነባራዊ ልምድ የአንድ የኤሌክትሪክ መኪና የባትሪ ዋጋ ከአምስት ሺሕ ዶላር እስከ 25,000 ዶላር ነው የሚገመተው። ይህ ደግሞ በአገራችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ወደፊት ማስከተሉ አይቀርም። በአሁኑ ወቅት ያለውን የአንድ አነስተኛ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪ ዋጋ ወደ ብር ስንመነዝረው ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ፈታኝ የሚሆነው የእነዚህ ተሽከርካሪዎች ባትሪዎች ዋጋ ውድ መሆኑና ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ማነቆዎች እንዳይፈጠሩ፣ የረዥም ጊዜ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በቅድሚያ መሥራት ማስፈለጉ ነው፤›› ብለዋል።

በአገር ውስጥ የባትሪ ማምረቻ ፋብሪካ ማቋቋም ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት የምክር ቤቱ ተወካይ፣ ሚኒስቴሩ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪና ለባትሪ ሥነ ምኅዳር ልማት እንደ ጥሬ ዕቃ፣ ባትሪ ማምረቻ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋልና የሰው ሀብት ልማት የሚያካትት አጠቃላይ አገራዊ ስትራቴጂ ከመዘርጋት አንጻር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ካሉ ማብራሪያ ይቅረብ ብለዋል።

‹‹የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለወደፊት የባትሪ ማምረቻ ዘርፍ አስፈላጊ የሆኑትን እንደ ሊትየም፣ ኮባልት፣ ኒኬል መሰል የአቅርቦት ሰንሰለቶችን ለማሟላት እንዴት አድርጎ እየሠራ ነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ ስለጉዳዩ በሰጡት ምላሽ፣ ከተወካዩ የቀረቡት ጥያቄዎች ትክክል መሆናቸውን ገልጸው፣ ነገር ግን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪዎች የአገልግሎት ዘመን እስከ አሥር ዓመት መሆኑን ተናግረዋል። ይህንና ባትሪዎችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት መሥሪያ ቤታቸው ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርፆ ባለሀብቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው በዘርፉ እንዲሰማሩ ለማድረግ እየተሠራ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡