
25 ጥር 2025
ግጭት በሚካሄድባቸው የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከፍርድ ውጭ የሚፈጸሙ ግድያዎች በአሳሳቢነት መቀጠላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
ግድያዎቹ የተፈጸሙት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም በክልሎቹ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች እንደሆነ ኢሰመኮ አርብ፣ ጥር 16/ 2017 ዓ.ም ያወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ለታጣቂዎቹ ድጋፍ ታደርጋላችሁ በሚል እንዲሁም ታጣቂዎቹ ገዢውን መንግሥት ትደግፋላችሁ በሚል እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎች አሳሳቢ እንደሆኑ ነው ኢሰመኮ በግጭት ዓውድ ውስጥ ባሉ አካካቢዎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ገምግሞ ጥር 16/ 2017 ዓ.ም ባወጣው የሩብ ዓመቱ ሪፖርት ያስታወቀው።
በክልሎቹ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የሚፈፀመውን የድሮን ጥቃትን ጨምሮ በአማራ ክልል ከፋኖ ጋር እንዲሁም በኦሮሚያ ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር እየተደረጉ ያሉ ፍልሚያዎች የሰላማዊ ሰዎችን ግድያ፣ የንብረት እና መሰረተ ልማት ውድመትን ማስከተሉም በዚህ ሪፖርት ተካቷል።
ግጭት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ከፍርድ ውጭ ከሚፈጸም ግድያ በተጨማሪ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትህ እጦት እንዲሁም አስገድዶ መሰወር አሳሳቢ ሆነው ቀጥለዋል ብሏል።
ሪፖርቱ ጨምሮም እገታ፣ በመዘዋወር መብትና በመጓጓዣ መንገዶች ላይ የሚፈጸም ሕገወጥ ገደብ ፣ የአገር ውስጥ መፈናቀል እና የዳኝነት ነጻነት መሸርሸር ተባባሶ መቀጠላቸውን ተመልክቷል።
ግጭት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች በነጻነት ተንቀሳቅሶ የተሟላ ክትትልና ምርመራ ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ፣ ሪፖርቱ በግጭት ዓውድ ውስጥ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በሙሉ የሚሸፍን አይደለም ብሏል።
በአማራ ክልል የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ታጣቂውን የፋኖን ኃይል ትደግፋላችሁ ወይም የፋኖ ቤተሰብ ናችሁ ባሏቸው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ግድያ መፈጸማቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል።ታጣቂው ፋኖ ለመንግሥት ድጋፍ ያደርጋሉ ባላቸው ነዋሪዎች ላይ ግድያዎችን መፈጸሙም በሪፖርቱ ተካቷል።
በሪፖርቱ ከተጠቀሱት መካከል ከመስከረም አጋማሽ እስከ ጥቅምት አጋማሽ በምሥራቅ ጎጃም ዞን በ11 ሰላማዊ ሰዎች የተፈጸመው ግድያ ይገኝበታል።
- በአማራ ክልል ሁለት ዞኖች በአንድ ቀን 20 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን ቤተሰቦች እና የዓይን እማኞች ተናገሩ24 ጥር 2025
- በዋግ ኽምራ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በከፍተኛ ምግብ እጥረት በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ መሆናቸው ተነገረ22 ጥር 2025
- የኢትዮጵያ መንግሥት ጥሰት የፈጸሙ ኃላፊዎችን ከስልጣን እንዲያነሳ የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ መከሩ19 ታህሳስ 2024
በዞኑ ቢቡኝ ወረዳ፣ ወይን ውሃ ቀበሌ በተለያዩ ጊዜያት የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት በመሄድ “ፋኖን ትደግፋላችሁ” እንዲሁም “የፋኖ ቤተሰብ ናችሁ” ያሏቸውን 11 ሰላማዊ ዜጎች ወይን ውሃ ቀበሌ ወደሚገኘው የመከላከያ ካምፕ በመውሰድ እንደገደሏቸው ኢሰመኮ ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ከተጎጂ ቤተሰቦች መስማቱን በሪፖርቱ ገልጿል።
የተገደሉ ሰዎች የቀብር ሥነ ስርዓት እንዳይካሄድ ክልከላ የነበረ መሆኑንም ከመረጃ ምንጮች ሰምቻለሁ ብሏል።
በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ሊቦ ከምከም ወረዳ፣ አግድ ቀበሌ በተባለ አካባቢ መስከረም 22/ 2017 ዓ.ም በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ የነበረውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎም የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች አካባቢውን ከተቆጣጠሩ በኋላ ቤት ለቤት በመግባት በስምንት ሰላማዊ ዜጎች ላይ ግድያ መፈጸማቸው በዚሁ ሪፖርት ተጠቅሷል።
“የፋኖ ቤተሰብ ናችሁ” እንዲሁም “ፋኖን ትደግፋላችሁ” በሚል የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከፈጸሟቸው ግድያዎች መካከል 1 የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር እናትን ጨምሮ 3 ሴቶች እና 1 ህጻን እንዳሉበት ተገልጿል።
መስከረም 25 እና 26/ 2017 ዓ.ም በምስራቅ ጎጃም ዞን፣ በደባይ ጥላት ግን ወረዳ፣ በቁይ ከተማ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ በውጊያው የሞቱ ሰዎች ሥርዓተ ቀብር ሲፈጽሙ የነበሩ 3 ሰላማዊ ሰዎች ለምን ትቀብራላችሁ በሚል መገደላቸውም ሪፖርቱ ያካተተው ሌላኛው ጥሰት ነው።
የቀብር ሥነ ስርዓት ለምን ታካሂዳላችሁ በሚል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከተገደሉት መካከል አንዱ መስማት የተሳነው መሆኑን ኢሰመኮ የአካባቢው ነዋሪዎችን ዋቢ አድርጎ በሪፖርቱ አካቷል።
በሌላ በኩል መስከረም 26/ 2017 ዓ.ም በምዕራብ ጎንደር ዞን፣ በቋራ ወረዳ የፋኖ አባላት ይካሆ እና ገለጉ በተሰኙ ቀበሌዎች በሚገኙ መኖሪያ ቤቶች በመግባት “የብልጽግናን መንግሥት ትደግፋላችሁ” እንዲሁም “ከመከላከያ ጋር ሆናችሁ ፋኖን ተዋግታችኋል” በሚል ስምንት ሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸማቸውን ኢሰመኮ ጠቅሷል።
በተጨማሪ 60 የሚሆኑ ሰዎችን ገለጉ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ለቀናት እንዳሰሩ እንዲሁም በርካታ የቀንድና የጋማ ከብቶችን ዘርፈዋል ብሏል ሪፖርቱ።
መስከረም 29/ 2017 ዓ.ም በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ደጋ ዳሞት ወረዳ የተደረገ የተኩስ ልውውጥን ተከትሎም የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወረዳዋን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ ፋኖ ወደ ወረዳው መቀመጫ ፈረስ ቤት ከተማ በመግባት በርካታ የወረዳ አመራሮችን፣ የሥራ ኃላፊዎችን እንዲሁም “የመንግሥት የመረጃ ምንጭ” የተባሉ ቢያንስ 80 ሰዎችን ማሰራቸው ተገልጿል።
በቁጥጥር ሥር ውለው ከነበሩት መካከል 38 ሰዎች ኅዳር 27 / 2017 ዓ.ም ልዩ ቦታው ፈረስ ሚካኤል በተሰኘ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በፋኖ ታጣቂዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ ከአካባቢው ነዋሪዎች እና የአገር ሽማግሌዎች መረዳቱን ጠቅሷል።
ከእነዚህም መካከል 22ቱን ኢሰመኮ በስም መለየት መቻሉን ሪፖርቱ አትቷል።
በኦሮሚያ ክልልም በተመሳሳይ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ወይም በተለምዶ ኦነግ ሸኔ ከተሰኘው ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት አላችሁ እና ስንቅ እና መረጃ ታቀብላላችሁ በሚል ግድያዎች እንደሚፈጸሙ ሪፖርቱ ጠቅሷል።
ኢሰመኮ በዚህ ረፖርቱ መንግሥትን ጨምሮ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሠሩ ጠይቋል።
“በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት በማናቸውም የግጭት ሂደት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰትን ከመፈጸም እንዲቆጠቡ፤ በግጭቱ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን በይፋ እንዲያወግዙ እና ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ፤ እንዲሁም በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ሰብአዊ መብቶችን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ፤ በሲቪል ሰዎች ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡ” ጥሪውን አቅርቧል።