የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ጃክ ስሚዝ

ከ 6 ሰአት በፊት

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከእሳቸው ጋር በተያያዘ ሁለት የወንጀል ጉዳዮች ላይ ሲሠሩ በነበሩ ከ12 በላይ የፍትህ ቢሮ ጠበቆችን አሰናበተ።

“ፕሬዚዳንቱን ለመክሰስ በሚጫወቱት ጉልህ ሚና ምክንያት የፕሬዚዳንቱን አጀንዳ በታማኝነት ለማስፈጸም እምነት ሊጣልባቸው እንደማይቻል” በተጠባባቂ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጀምስ ማክሄንሪ ድምዳሜ ላይ በመደረሱ መባረራቸውን አንድ የቢሮው ባለስልጣን ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

ጠበቆቹ የትራምፕ ሚስጥራዊ ሰነዶችን አላግባብ አያያዝን እና እአአ በ 2020 ምርጫ የደረሰባቸውን ሽንፈት ለመቀልበስ ሞክረዋል በሚል የተከፈተውን ምርመራ የመሩት የቀድሞ የልዩ አማካሪ የጃክ ስሚዝ ቡድን አባል ነበሩ።

ሰኞ የተደረገው ከሥራ የማባረር እርምጃ ወዲያውኑ ተግባራዊ ሆኗል።

ስሚዝ በ2022 የትራምፕን ሁለቱን የፍትህ ቢሮ ጉዳዮችን ለመቆጣጠር ልዩ አማካሪ ሆነው ተሹመዋል። ፕሬዚዳንቱ ስልጣን ከያዙ በኋላ “በሁለት ሰከንድ ውስጥ” እንደሚያባርሯቸው ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም ስሚዝ ከበዓለ ሲመቱ በፊት ሥራቸውን አቁመዋል።

ሁለቱም ጉዳዮች ጥፋተኛ አይደለሁም ባሉት ትራምፕ ላይ የወንጀል ክስ አስከትለዋል።

በህዳር ወር ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ክሶቹ ተዘግተዋል። የፍትህ መምሪያ ደንቦች በሥራ ላይ በሚገኙ ፕሬዝዳንት ላይ ክስ መመስረት እንደማይፈቅድ አቃቤ ህግ አስታውቋል።

የትኛዎቹ የስሚዝ ቡድን አባላት እንደተባረሩ አልታወቀም።

በስሚዝ ቡድን ውስጥ ከሠሩት ውስጥ ብዙዎቹ ሙስና እና የብሄራዊ ደህንነት ዓቃብያነ ህጎች ሲሆኑ በተለያዩ አስተዳደሮች ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ናቸው።

ፕሬዚዳንቱን በመመርመር እና በመክሰስ የነበራቸው ሚና በቢሮው ውስጥ ለመሥራት ብቁ እንደማያደርጋቸው የሚገልጽ ደብዳቤ ሰኞ ዕለት እንደደረሳቸው ተዘግቧል።

“አቃብያነ ህግ እንዲሠሩ በተመደቡባቸው ጉዳዮች ምክንያት ከሥራ መባረራቸው ተቀባይነት የለውም። ህግ እና ፀረ-ዴሞክራሲ ህግ ነው” ሲሉ የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ አቃቤ ህግ ጆይስ ቫንስ ለኤንቢሲ ኒውስ ገልጸዋል።

ከሥራ የማሰናበቱ ጉዳይ የተሰማው አንዳንድ በአገር ደኅንነት እና በህዝብ ሙስና ላይ በተለያዩ ዘርፎች ልምድ ያላቸው የፍትህ ቢሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በድጋሚ ወደተለያየ ክፍል መመደባቸውን ተከትሎ ነው። ሰኞ ዕለት ከመካከላቸው አንዱ የሆኑት የህዝብ ጉዳዮች ኃላፊ ከስልጣን መነሳታቸው ተነግሯል።

ትራምፕ እና ቡድናቸው የፍትህ ቢሮው በእርሳቸው፣ በባልደረቦቻቸው እና በሪፐብሊካኖች ላይ ፖለቲካዊ ዓላማ ያነገቡ ክሶችን እንደከፈተባቸው ገልጸዋል። ትራምፕ በድጋሚ ለመመረጥ የምርጫ ቅስቀሳ ባካሄዱበት ወቅት “በማጥቂያነት” ጥቅም ላይ ዋለውን ቢሮ አፋጣኝ ማሻሻያ እንደሚያደርጉበት ቃል ገብተዋል።

የፍትህ ክፍሉን እንዲመሩ የተሾሙት ፓም ቦንዲ የትራምፕን አስተያየት በማስተጋባት የተከፈተባቸው ክስ ፖለቲካዊ ነው በማለት ቢሮው “ለዓመታት መሳሪያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል” ሲሉ አስተጋብተዋል።

ስሚዝ ሥራቸውን በይፋ ተከላክለዋል። እአአ ከ2020 ምርጫ በኋላ የትራምፕን ድርጊት አስመልክቶ የተዘጋጀውን የመጨረሻ ረቂቅ በያዘው ደብዳቤ ላይ “እንደ አቃቤ ህግ ያደረኳቸው ውሳኔዎች በባይደን አስተዳደር ወይም በሌሎች የፖለቲካ ተዋናዮች ተጽዕኖ ተደርጎበታል የሚለው [የትራምፕ] ጥያቄ አስቂኝ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።

በመቶዎች ከሚቆጠሩ የካፒቶል ሂል ሁከት ክሶች ጀርባ በተሰጠው ውሳኔ ላይ የውስጥ ግምገማ መጀመን ሩየዋሽንግተን ዲሲ ከፍተኛ የፌደራል አቃቤ ህግ ሰኞ ዕለት አስታውቋል ሲል ሲቢኤስ ዘግቧል።

በትራምፕ የተሾሙት የዩናይትድ ስቴትስ ተጠባባቂ አቃቤ ህግ ኤድዋርድ ማርቲን የቀድሞ አስተዳደር ከ200 በላይ የካፒቶል ሁከት ተከሳሾች ላይ የእገዳ ክስ እንዲመሰረት ከተሰጡ ውሳኔዎች ጋር የተያያዙ ሰነዶችን፣ ኢሜሎችን እና ሌሎች መረጃዎችን ለጽህፈት ቤታቸው እንዲያቀርቡ አቃቤ ህጎችን አዘዋል።