ተፈናቃይ ልጅ

ከ 6 ሰአት በፊት

አብዛኞቹ ወደ ሰሜናዊ ጋዛ የተመለሱ ፍልስጤማውያን ቤታቸው ፈራርሶ ነው የጠበቃቸው።

የ44 ዓመቷ ሳብሪን ዛኑን ወደ ቤታቸው ከተመለሱት ተፈናቃዮች አንዷ ናት።

“ቤተሰቦቻችንን ስናይ ደስ አለን። ግን ቤታችን ወድሞ ማየት አሳዘነን። ሰዎች የሚያምረውን ሰፈር ለማየት ይመጡ ነበር። አሁን ግን ምንም አልተረፈም” ትላለች።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ቤታቸውን በነበረበት አላገኙትም። እስራኤልና ሐማስ የተኩስ አቁም ተስማምተው ወደ ቀያቸው ቢመለሱም መኖሪያ የላቸውም።

ሳብሪን እንደ ሌሎቹ ፍልስጤማውያን ከአንድ ጊዜ በላይ ነው የተፈናቀለችው። በቅርቡ ከዴር-አል-ባላህ ተፈናቅላለች።

ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ለመመለስ አል-ራሺድ ጎዳና ላይ ሲጠባበቁ ከነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አንዷ ነበረች።

አንድ የጋዛ የፀጥታ ባልደረባ ለኤኤፍፒ እንዳሉት፣ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች መንገዱን አቋርጠው ወደ መንደራቸው ተመልሰዋል።

መንገድ ላይ ሳለች ከቢቢሲ ጋር ያወራችው የ24 ዓመቷ ኢስራ ሻኸን “በጣም ረዥምና አድካሚ መንገድ ነበር። እስከ መንገዱ ግማሽ ድረስ ሰዎች በደስታ ሲዘፍኑ ነበር። ግን መንገዱ ሲረዝም መዳከም ጀመርን። ከዚያ ‘እንኳን ወደ ጋዛ በደኅና መጣችሁ’ የሚል ምልክት፣ የፍልስጤም ሰንደቅ አላማ እና በሀሴት የሚጠብቁን ሰዎች አየንና እኛም ደስታችን ተመለሰ” ብላለች።

“በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። መንገዱ ሞልቷል። በመመለሴ ደስ ቢለኝም ቤቴ እንደማይጠብቀኝ ሳስብ አዝናለሁ” ስትል የ42 ዓመቷ ዋፋ ሀሱና ተናግራለች።

ሰሜናዊ ጋዛ ሲደርሱ ባዩት ውድመት ደንግጠዋል። መሐመድ ኢማድ አል-ዲን ቤቱ ፈራርሶና ተዘርፎ ነው የጠበቀው።

ሉብና ናስር ከሁለት ልጆቿና ባለቤቷ ጋር ለመገናኘት በጉጉት ትጠብቅ ነበር። ቤተሰቦቿን ብታገኝም ቤታቸው ፈርሷል።

“የመገናኘታችን ደስታ በቤታችን መፍረስ እውነታ ተሸፈነ በደቡብ ጋዛ ከምንኖርበት ድንኳን ወደ ሰሜን ጋዛ ድንኳን ተሻገርን” ትላች።

አንድ ፍልስጤማዊ “ነፍሰ ጡር ባለቤቴና ልጄ አብረውኝ ባይኖሩ ወደ ሰሜን ጋዛ በሩጫ ነበር የምገባው። ጦርነቱ ይቆምና የወደመውን መልሰን እንገነባለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

ተፈናቃዮች

ሌላ ፍልስጤማዊ እንዳለው ወንድሙ ደውሎ እንዲመለስ ነግሮታል።

“መንደሩ ወድሟል። ሰዎች ጎዳና ላይ እየተኙ ነው። የሚረዳቸው የለም” ብሎ ወንድሙ እንደነገረው ይገልጻል።

በታል አል-ሀዋ መንደር አብዛኛው መኖሪያ ወድሟል።

“አብዛኛው ነገር ወድሟል። ቤቱን ባለበት የሚያገኝ ሰው ዕድለኛ ነው” ትላለች ሳብሪን።