የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የሰብዓዊነት ትምህርት ቤት በይፋ ሥራ መጀመር አስመልክቶ በስካይ ላይት ሆቴል ባዘጋጀው ፕሮግራም

ማኅበራዊየሰብዓዊነት ትምህርት ቤት የከፈተው ቀይ መስቀል

የማነ ብርሃኑ

ቀን: January 29, 2025

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ላለፉት 90 ዓመታት በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት ለጉዳት ለተጋለጡ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

ማኅበሩ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ከገባችበት ውስብስብ ሰብዓዊ ቀውስ እንድትወጣና ፍትሐዊ፣ ሰላማዊና ሁሉን አቀፍ ማኅበረሰብ መገንባት እንዲቻል የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ እያደረጋቸው ከሚገኙ ጥረቶች መካከልም በሕዝብ ዘንድ የመተሳሰብና የመከባበር እሴት በማጎልበት በፈጠራ፣ በምርምርና በማስተማር ላይ በማተኮር ሰብዓዊነት የተላበሰ ትውልድ ለማፍራት ያስችላል ያለውን ‹‹የሰብዓዊነት ትምህርት ቤት›› (School of Humanity) አቋቁሟል፡፡

ማኅበሩ ሰኞ ጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም. የትምህርት ቤቱን በይፋ ሥራ መጀመር አስመልክቶ በስካይ ላይት ሆቴል ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ቶላ እንደተናገሩት፣ የሰብዓዊነት ትምህርት ቤቱ የተከፈተበት ዋና ዓላማ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንደ አገር ለሰው እየተሰጠው ያለው ዋጋና ክብር እያነሰና ትርጉም እያጣ በመምጣቱ ነው፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ድንቅና ግሩም የሆነ የመተሳሰብ፣ የመከባበር፣ የመረዳዳትና አብሮ በጋራ የመኖር እሴትን ያጎለበቱ ሕዝቦች ናቸው፤›› የሚሉት አቶ አበራ፣ ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነኚህ እሴቶችና ባህሎች ተሸርሽረው ወገን በወገኑ ላይ እንዲነሳና እንዲጨካከን ሆኗል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች ብዙ ጥፋቶችና ጭካኔዎች ተፈጽመዋል፡፡ ለማየትና ለመስማት የሚከብዱ ግፎች በሰዎች ላይ ደርሰዋል፡፡ መሆን የሌለበት ነገር ሁሉ ሆኗል፡፡ በመሆኑም ይህን መሰል ድርጊት ወደፊት እንዳይደገም ትውልድ ላይ መሥራት የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ በዚህ መነሻነት ወጣቱን ትውልድ በሰብዓዊነት ለማነጽና ትውልድ በሥነ ምግባር ተኮትኩቶ እንዲያድግ ለማስቻል ትምህርት ቤቱ እንዲቋቋም ሆኗል፡፡

እንደ አቶ አበራ፣ በትምህርት ቤቱ የሚሰጠው ሥልጠና ሠልጣኞችን ብቻ ሳይሆን ቤተሰባቸውን፣ አካባቢያቸውንና ማኅበረሰቡን ይለውጣል ተብሎ የታመነበት ነው፡፡

በትምህርት ቤቱ የሚሰጡ ኮርሶች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች በተውጣጡ ምሁራን የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ሞራል ኢቲክስ፣ ሒውማኒቴሪያል ዲፕሎማሲ፣ ኢንቫይሮመንታል ኤቲክስን ጨምሮ ሌሎችም አሥራ ሁለት ኮርሶች ለመማር ማስተማሪያ ግብዓትነት እንዲያገለግሉ ተዘጋጅተዋል፡፡

በመጀመሪያ ዙር 50 ተማሪዎችን ተቀብሎ በዲፕሎማ መርሐ ግብር ትምህርት ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች የተጠናቀቁ መሆናቸውን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ሰብዓዊነትን በትምህርት በማስተማር እንደ አገር የሚታዩ ችግሮችን ማስወገድ ይቻላል የሚል እምነት ያላቸው ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሎሚ በዶ እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የተከፈተው የሰብዓዊነት ትምህርት ቤት በአገር ደረጃ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ መፈታት የሚገባቸው በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ እነኚህ ችግሮችም የማኅበረሰቡን አብሮ የመኖር እሴት ሳይሸረሽሩና ሰላሙን ሳያደፈርሱ በንግግርና በውይይት እንዲፈቱ መንግሥት እየሠራ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርም ሰብዓዊነትን፣ አብሮነትንና መቻቻልን በሕዝቦች ዘንድ ለማምጣት በማሰብ ትምህርት ቤት መክፈቱ መንግሥት እየሠራ ለሚገኘው ሥራ ትልቅ ዕገዛ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ሰብዓዊነት ካሪኩለም ተዘጋጅቶለት በትምህርት ደረጃ መሰጠቱ ሰላምን በማምጣትና አብሮነትን ለማጎልበት ረገድ የሚኖረው ሚና የጎላ ስለመሆኑ የተናገሩት አፈ ጉባዔዋ፣ ሃይማኖት፣ ፆታ፣ ብሔርንና ቀለምን መሠረት ያላደረገ አገርና ሕዝብ እንዲኖር ለማስቻልም የላቀ አበርክቶ የሚኖረው ነው፡፡  

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር፣ እንዲሁም በቀይ መስቀል ማኅበር የሰብዓዊነት ትምህርት ቤት ዲን የሆኑት ደመቀ አቺሶ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድነትን ለማጠንከርና ኅብረትን ለመፍጠር የተሠሩ ሥራዎች አነስተኛ በመሆናቸው፣ አገሪቱ ዛሬ በሰላም ዕጦት ቀውስ ውስጥ እንድትገኝ ሆናለች፡፡ ስለሆነም አገሪቱን ከሰላም ዕጦት ቀውስ ለማውጣትና የሚታዩ ችግሮችም እንዲቀረፉ ለማስቻል የሰብዓዊነት ትምህርት ቤቱ መክፈት አዎንታዊ ጎን ያለው ነው፡፡

‹‹በሰብዓዊነት ላይ መማር እፈልጋሁ የሚል ማንኛውም ግለሰብ የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን ይችላል፤›› ያሉት ደመቀ (ዶ/ር)፣ ወደ ትምህርት ቤቱ ገብቶ ለመሠልጠን የሚፈልግ ሰው በማንኛውም የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪ ሊኖረው እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ በዲፕሎማ መርሐ ግብር ለጊዜው ትምህርት መስጠት የሚጀምር ቢሆንም፣ በቀጣይ በመጀመሪያና በሁለተኛ የዲግሪ መርሐ ግብር ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያሠለጥን መሆኑን ዲኑ አክለው ገልጸዋል፡፡