መቀለ
የምስሉ መግለጫ,መቀለ

31 ጥር 2025

ትግራይ ከአውዳሚው ጦርነት ማብቃት በኋላ ከጦርነቱ ጉዳት ለማገገም ጥረት እያደረገች ቢሆንም፣ የክልሉ አንጋፋ የፖለቲካ ፓርቲ በሆነው ህወሓት አመራሮች መካከል ለወራት የዘለቀው አለመግባባት ተካሮ በሕዝቡ ላይ ሌላ ስጋት አስከትሏል።

ለሁለት በተከፈሉት የህወሓት አመራሮች መካከል በተለይ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ከተካሄደው 14ኛ የድርጅቱ ጉባኤ በኋላ በሊቀ መንበሩ እና በምክትሉ የሚመሩት ሁለት ወገኖች ለወራት በከፍተኛ አለመግባባት እና መካሰስ ውስጥ ቆይተዋል።

ይህ በህወሓት ፖለቲካዊ አመራሮች መካከል የቆየው ውዝግብ አስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ የደረሰ እንደነበር አይዘነጋም። ነገር ግን ለወራት በገለልተኝነት የቆዩት የትግራይ ወታደራዊ አመራሮች አብዛኞቹ ባለፈው ሳምንት በደብረጽዮን ለሚመራው ወገን ድጋፍ መስጠታቸውን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ስጋት ተፈጥሯል።

እነዚህ ወታደራዊ መኮንኖች በህወሓት ሊቀመንበር የሚመራው የድርጅቱ ክንፍ በምክትሉ እና በሌሎችም የአመራሮች እንዲሁም በምርጫ ቦርድ ተቀባይነት ያላገኘውን የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ በመደገፍ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መልሶ እንዲዋቀር ጠይቀዋል።

ይህ የወታደራዊ አመራሮች ጥያቄ በአቶ ጌታቸው ረዳ ከሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ፍጥጫ ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ሆኗል። ይህንንም ተከትሎ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች አንደኛውን ወገን በመቃውም እና ሌላኛውን በመደገፍ ሰልፎች ተካሂደዋል።

ይህ በሁለቱ የህወሓት ፖለቲካዊ አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እና ወታደራዊ አዛዦቹ ደግሞ አንዱን ወገን ደግፈው መቆማቸው በሕዝቡ ውስጥ ክፍፍል ከመፍጠሩ ባሻገር ሁኔታው ወደ ግጭት እንዳያመራ ፍርሃት ፈጥሯል።

በአለመግባባቱ ከፖለቲከኞች አልፎ ወታደራዊ አመራሮቹ መግባታቸው ሁኔታውን ወደ ግጭት ሊመራው ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

ከቀናት በፊት በደብረጽዮን ከሚመራው ቡድን የተላከ አንድ ግለሰብ ከአምስት ታጣቂዎች ጋር በመሆን በመቐለ ከተማ የሚገኘውን የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያን ለመቆጣጠር ሙከራ ማድረጉ ይታወሳል።

የወታደራዊ መሪዎቹ አቋም፣ በተለያዩ ከተሞች የተካሄዱት የድጋፍ እና የተቃውሞ ሰልፎች ተደማምረው ቀጠይ ሊከሰት የሚችለው ነገር ያሰጋቸው በርካታ የመቐለ ከተማ እና በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ቅድመ ጥንቃቄ የሚመስሉ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው።

በዚህም ምክንያት በጦርነት የተዳከመው እና የተሰላቸው የክልሉ ሕዝብ ምን ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት እየታየበት ነው። በፖለቲከኞቹ አለመግባባት የተነሳ አቅም ያላቸው የመሠረታዊ ሸቀጦችን መሸመት፣ ከባንክ ብር አውጥቶ መያዝ፣ አንዳንዶችም ወደ አዲስ አበባ የመሄድ አዝማሚያዎች እየታዩ መሆናቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በርካታ ሰዎች በባንክ ያላቸውን ገንዘብ በእጃቸው ለማድረግ በባንክ ቅርንጫፎች ረጃጃም ሰልፎች እየታዩ መሆናቸውን ቢቢሲ ያናገራቸው የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ከባንኮችም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እየወጣ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ባንኮች ወጪ እንዲደረግ የፈቀዱትን 50 ሺህ ብር መጠን ወደ 10 ሺህ ብር ዝቅ ማድረጋቸውን አንዳንድ ነዋሪዎች የተናገሩ ሲሆን፣ ቢቢሲ ይህንን ለማረጋገጥ ሁለት ባንኮችን ቢጠይቅም ምላሽ ማግኘት አልቻለም።

ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት በከፍተኛ ሁኔታ ተጎጂ የነበሩት ወጣቶች መሆናቸው ይታወቃል። አሁንም በክልሉ ያለው ሁኔታ ያሰጋቸው ወጣቶች በብዛት ወደ አዲስ አበባ እንደሚሄዱ ቢቢሲ ያናገራቸው ሰዎች አመልክተዋል።

ነዋሪዎች ለቅድመ ጥንቃቄ በሚል ባላቸው ገንዘብ የመሠረታዊ ፍጆታ ሸቀጦችን በመሸመት ላይ በመሆናቸው በእቃዎች ላይ ባለፉት ቀናት የዋጋ ጭማሪ መታየቱንም ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያናገራት የመቐለ ነዋሪ “የምኖረው ቀዳማይ ወያነ አካባቢ ነው፤ እና ምንም የተለየ ነገር አላየሁም። ነገር ግን የዋጋ ጭማሪ አለ። ዘይት፣ ማካሮኒ እና ሌሎች የፍጆታ ዕቃዎች ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ከ50 እስከ 60 ብር ጨምረዋል” ስትል ተናግራለች።

ነዋሪዎች በጦርነቱ ወቅት የነበረው የክልሉ መዘጋት ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል ሸቆጦች እንዳይገቡ በማድረግ ያስከተለውን ችግር በማስታወስ ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይገጥማቸው ሸቀጦችን እየሸመቱ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ነዋሪዋ አብዛኛው ሕዝብ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ስለሚኖር የሚያስፈልገውን ነገር ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ እንደሌላቸው እና በባንክ ገንዘብ ያላቸውም ከ10 ሺህ ብር በላይ ማውጣት አለመቻሉን አመልክታለች።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ እያጋጠመው የነዳጅ እጥረት በትግራይ ውስጥም መኖሩን ነዋሪዎች ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት በነዳጅ እና በትራንስፖርት ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ተከስቷል።

በተለይም በህወሓት አመራሮች መካከል በቆየው ውዝግብ ውስጥ ወታደራዊ መኮንኖች ከአንደኛው ወገን ጋር ቆመው መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ የነዋሪው ስጋት እና በአቅርቦት ዋጋ ላይ የሚታየው ንረት ጨምሯል ይላሉ።

“ቤንዚን በሊትር 300 ብር ገብቷል። በዚህም ለአንድ ባጃጅ ጉዞ እንከፍለው የነበረው 30 ብር አሁን 50 ብር ሆኗል” ስትል የመቐለ ነዋሪዋ ከሳምንት በፊት እና በኋላ የታየውን የዋጋ ጭማሪ በምሳሌ አስረድታለች።

ሌላ ነዋሪም “በከተማው ነዳጅ የለም፤ ከሳምንት በፊት 15 ብር የነበረው ታክሲ ጉዞ አሁን 30 ብር እየከፈልን ነው” በማለት አንዳንድ ቦታዎች ላይ የዋጋ ጭማሪው እጥፍ መሆኑን ገልጿል።

“አቅም እና ገንዘብ ያለው ትግራይ ውስጥ መቆየት አይፈልግም። ከክልሉ የመውጣት ዕቅድ ነው ያለው። ብዙ ወጣቶች ወደ አዲስ አበባ እንሄዳለን እያሉ ነው። ወንድሞቼም ተመሳሳይ ነገር ይነግሩኛል” ስትል የተፈጠረው ስጋት ነዋሪውን ከክልሉ ለመውጣት እያነሳሳው መሆኑን ገልጻለች።

ሌላ የመቐለ ከተማ ነዋሪ ወጣትም ብዙ ሰዎች ወደ አዲስ አበባ እየሄዱ መሆናቸውን እና ከመቐለ ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱ በረራዎች ሙሉ መሆናቸውን ተናግሯል። ብዙ ሰውም የአውሮፕላን ጉዞ እየተጠቀመ በመሆኑ ትኬት ለማግኘት ለቀናት መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አስረድቷል።

የተከሰተውን ፖለቲካዊ ውጥረት እና በሕዝቡ ውስጥ የተፈጠረውን ስጋት በመጠቀም የበለጠ ትርፍ ለማግኘት የሚፈልጉ ነጋዴዎችም እጥረት በሌለባቸው ሸቀጦች ላይ ሳይቀር የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ላይ እንሆኑ ይኸው ነዋሪ ተናግሯል።

በሁለቱ የህወሓት አንጃዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ውዝግብ በክልሉ ሕዝብ የዕለት ከዕለት ሕይወት ላይ ከባድ ጫና እያስከተለ ቢሆንም፤ ፖለቲከኞቹ አስካሁን ይህንን ስጋት ከሚያረግብ መግባባት ይልቅ፣ ደጋፊዎቻቸውን ከጎናቸው በማሰለፍ ሰልፎችን አድርገዋል።