የምክር ቤት አባላቱ ጠረጴዛ ተሸክመው
የምስሉ መግለጫ,በምክር ቤቱ አባላት መካከል የተከሰተውን ግጭት ለማብረድ ፖሊስ ተጠርቷል።

ከ 1 ሰአት በፊት

ሐሙስ ምሽት፣ ጥር 22/ 2017 ዓ.ም በጋና ምክር ቤት ውስጥ በተነሳ ግጭት አባላቱ እርስ በርስ ከመቧቀስ በተጨማሪ የምክር ቤቱን ቁሳቁሶችን አወደሙ።

ይህ የሆነው ምክር ቤቱ የአዲስ ሚኒስትሮችን ሹመትን ለማጣራት ስብሰባ እያካሄደ በነበረበት ወቅት ነው።

በአባላቱ ዘንድ በተፈጠረው አለመግባባትም የምክር ቤት አባላቱ ወንበሮችን፣ ጠረጴዛዎችን እና ማይክራፎኖች በማውደማቸው ፖሊስ ጣልቃ እንዲገባ ተደርጓል።

ሹመቱን የሚያጣራው ኮሚቴ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ያልተስማማ ሲሆን፣አንዳንዶች ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት ፖለቲካዊ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ሒደቱን እያጓተቱ ነው ሲሉ ከሰዋል።

አርብ ጥዋትም የአጣሪ ኮሚቴው ሊቀመንበር “የተፈጠረው ክስተት ተቀባይነት የለውም” ሲሉ የጋናን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀዋል።

የተለያዩ ፓርቲ አባላትን የያዘው ኮሚቴው የገዥውን ብሔራዊ ዲሞክራቲክ ኮንግረንስ ፓርቲ (ኤንዲሲ) ሦስት ሕግ አውጪዎችን ሹመት ለማጣራት ነበር ፕሮግራም ይዞ የነበረው።

ሦስቱ ሕግ አውጪዎች ባለፈው ታኅሳስ ወር በተካሄደው ምርጫ ኤንዲሲ፣ ኒው ፓትሪዎቲክ ፓርቲን (ኤንፒፒ)ን አሸንፎ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ነበር ለሚኒስትርነት የታጩት።

ሆኖም የኤንዲሲ የፓርላማ አባላት፣የታጩትን ሚኒስትሮች ሹመት ለአላስፈላጊ ረዥም ጊዜ እያጓተቱ ነው ሲሉ በፓርላማው የኤንፒፒ ፓርቲ መሪ የሆኑትን አሌክሳንደር አፌንዮ ማርኪን ከሰዋል።

አጣሪው ኮሚቴው ከ5 ሰዓት በላይ በወሰደው ስብሰባ ማጽደቅ የቻለውም የአንድ እጩን ሹመት ብቻ ሲሆን ሳሙኤል ናርቴይ ጆርጅን የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር አድርጎ ሾሟል።

ሹመታቸውን በተመለከተ የተፈጠረው ንትርክም፣ተሿሚው ጆርጅ በቀድሞው ፕሬዚደንት እና በኤንፒፒ መሪ ናና አኩፎ -አዶ እና በአኩፎ አዶ ምክትል ፕሬዚደንት መሃመዱ ባውሚያ ላይ የሚሰነዝሩትን ትችት እንዲያነሱ በሚፈልጉና በኮሚቴው ውስጥ ባሉ የተቃዋሚ ፓርላማ አባላት ፓለቲካዊ ጥቅም ለማግኘት የተደረገ ሴራ እንደሆነ በርካታ የኤንዲሲ የፓርላማ አባላት ያምናሉ።

በመጨረሻም ስብሰባው በጩኸት፣ እርስ በእርስ በመገፋፋት እና በመገፈታተር እንዲሁም ጠረጴዛዎችን በመገለባበጥ ሊጠናቀቅ ችሏል።

ይህንንም ተከትሎም የፓርላማው አፈ ጉባኤ ከኤንፒፒ ሦስት እና ከመንግሥት ፓርቲ ደግሞ አንድ አባልን በአጠቃላይ አራት ሕግ አውጪዎችን ለሁለት ሳምንት አግደዋል።

የኤንፒፒው መሪ አፌንዮ ማርኪን በበኩላቸው የፓርላማው ደንብ “የኮሚቴው አባላት እያንዳንዱ የፕሬዚደንት እጩዎች ላይ ያለ ምንም ገደብ ጥያቄ እንዲያነሱ ይፈቅዳል” ሲሉ አርብ ዕለት ተናግረዋል።

ሆኖም ኤንዲሲ ይህንን ሕጋዊ አሰራር እያሰናከለ ነው ሲሉ ከሰዋል።

በተፈጠረው ትርምስ ምክንያትም ስብሰባውን በመጪው አርብ ለማካሄድ ተወስኗል።