
ከ 4 ሰአት በፊት
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ባለፈው እሁድ ጀምሮ በተካሄደው ውጊያ ቢያንስ 700 ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።
ጦርነቱ በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል በምትገኘው ትልቋ ከተማ ጎማ ተፋፍሟል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች እንደተናገሩት በሩዋንዳ የሚደገፉት የኤም23 አማጺያን የሰሜን ኪቩ ግዛት መዲና የሆነችውን ጎማን ለመቆጣጠር በተደረገው ፍልሚያ ከተገደሉት በተጨማሪ 2 ሺህ 800 ሰዎች ቆስለዋል።
ጎማን የተቆጣጠሩት አማጽያኑ ወደ ደቡባዊ ኪቩ መዲና ቡካቩ እየገሰገሱ መሆኑ ተነግሯል።
የምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጦርነት በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ቢጀመርም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ተባብሷል።
የቱትሲ ብሔርን ያቀፈው የኤም23 አማጺያን ለአናሳዎች መብት እንደሚታገሉ ቢናገሩም የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግሥት በበኩሉ በሩዋንዳ የሚደገፉት አማጺያኑ በማዕድን ሃብታም የሆነውን የምስራቃዊውን ሰፊ ሥፍራ ለመቆጣጠር ይፈልጋሉ ሲል ይወቅሳል።
የተመድ ቃል አቀባይ ዱጃሪች እንደተናገሩት የሟቾቹ አኃዝ የዓለም ጤና ድርጅት እና አጋሮቹ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ መንግሥት ጋር በመጣመር ከእሁድ እስከ ሐሙስ ባሉት ቀናት መካከል ባደረጉት ግምገማ ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል።
ቃል አቀባዩ የሟቾቹ ቁጥር ከዚህም በላይ እንደሚጨምር አስጠንቅቀዋል።
የኤም23ን ግስጋሴ ለመግታት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጦር ከጎማ ወደ ቡካቩ በሚወስደው መንገድ ላይ የመከላከያ መስመር መዘርጋቱን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
- ተፈሪ አሰፋ፡ የከበሮ ምትን ያመጠቀው የሙዚቃ ሊቅከ 5 ሰአት በፊት
- ካናዳ፣ሜክሲኮ እና ቻይና ከዛሬ ጀምሮ ታሪፍ እንደሚጣልባቸው ዋይት ሃውስ አስታወቀከ 5 ሰአት በፊት
- የፖለቲከኞች እና የወታደራዊ አዛዦች ውዝግብ እና መግለጫ በትግራይ የፈጠረው ስጋት31 ጥር 2025
ቡካቩን በአማጽያኑ ሥር እንዳትወድቅ ለመከላከል በመቶዎች የሚቆጠሩ በጎ ፈቃደኞች ለመዋጋት መመዝገባቸው ተገልጿል።
አማጽያኑ እየገሰገሱባት ያለው የደቡባዊ ኪቩ ገዥ ዣን ጃኪውስ ፑሩሲ ሳዲኪ በበኩላቸው የመንግሥት ጦር እና አጋሮቹ በጋራ አማጺያኑን እየመከቱ እንደሆነ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ኤም23 በምዕራብ አቅጣጫ 2 ሺህ 600 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን ዋና ከተማዋን ኪንሻሳን እስኪቆጣጠሩ ድረስ በፍልሚያቸው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።
የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴሬዝ ካይክዋምባ ዋግነር ሩዋንዳ ኮንጎን በሕገወጥ መንገድ በመቆጣጠር የሥርዓት ለውጥ ለማድረግ እየሞከረች ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሩዋንዳውን ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜን ለአስርት ዓመታት ያህል ዓለም አቀፍ ሕግን በመጣስ ተጠያቂ ማድረግ እንደተሳነው ተናግረዋል።
የሩዋንዳ መንግሥት ቃል አቀባይ ዮላንዴ ማኮሎ በበኩላቸው የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለው የአገራቸው ጦር የተሰማራው ግጭቱ ወደ ግዛታቸው እንዳይንሰራፋ ለመከላከል ብቻ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
“ጦርነት አንፈልግም፤ ግዛት በኃይል መያዝ አንፈልግም እንዲሁም የሥርዓት ለውጥ የማድረግ ፍላጎት የለንም” ሲሉ ማኮሎ ለቢቢሲ ኒውስደይ ፕሮግራም ተናግረዋል።
ሩዋንዳ በምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከኤም23 ጋር የሚንቀሳቀሱ ከ3,000 እስከ 4,000 የሚደርሱ ወታደሮች እንዳሏት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎች ግምቱን አስቀምጧል።