
February 2, 2025
በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ እርሻዎችን ጨምሮ ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች የተለያዩ የክልሉ የውኃ ምንጮችን በመጠቀም ከሚያገኙት ገቢ ላይ እስከ አሥር በመቶ የሚሆነውን ለኦሮሚያ የውኃ ሀብት ልማት ፈንድ ገቢ እንዲያደርጉ የሚያዘው አዋጅ መተግበራዊ መደረግ መጀመሩ ተጠቆመ፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የካቲት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. የኦሮሚያ ክልል የውኃ ሀብት ልማት ፈንድን ለማቋቋም ያወጣውን አዋጅ ተከትሎ ባወጣው ማስፈጸሚያ መመርያ መሠረት በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች በመመርያው በተጠቀሰው ታሪፍ መሠረት ለሚጠቀሙበት ውኃ ክፍያ መፈጸም እንደሚኖርባቸው ያመለክታል፡፡
የአዋጁ ማስፈጸሚያ ድንጋጌ በ2015 ዓ.ም. የወጣ ቢሆንም ሳይተገበር ቆይቶ ካለፈው ሦስት ሳምንት ወዲህ ግን ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን የሚገልጽ ደብዳቤ ለሚመለከታቸው ተቋማት ሁሉ እንዲደርሳቸው መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከሰሞኑ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ይህ መመርያ ጉድጓድ ቆፍረው ወይም ከወንዝ ጠልፈው የውኃ ምንጮችን የሚጠቀሙ ድርጅቶች እንደ አገልግሎት ዓይነታቸው በሜትር ኪውብ ታሳቢ የሚደረግ ተመን የተካተተበት ነው፡፡
ነገር ግን ንፁህ ውኃ ወይም የታሽጎ ውኃ አመምርተው የሚሸጡ ፋብሪካዎች የተጣለባቸው ክፍያ ከዓመታዊ ጥቅል ገበያቸው አንድ በመቶ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
በተመሳሳይ በእርሻና ከፍተኛ የውኃ ፍጆታ ያላቸው እንደ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ዘርፎች ደግሞ በተመሳሳይ ከዓመታዊ ገበያቸው 0.5 በመቶ ለክልሉ ውኃ ሀብት ልማት ፈንድ ገቢ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተደንግጓል፡፡
ከዚህም ሌላ በመመርያው ያለ ቆጣሪ ውኃ የሚጠቀሙ ተጠቃሚዎች የሚከፍሉትን ክፍያ በተመለከተ ግለሰብ፣ የጤና ድርጅት፣ የትምህርት ድርጅቶች፣ ፋብሪካዎች፣ ሆቴሎች ወይም ማንኛውም ሌላ አካል በራሱ የሚያመነጨውን ማንኛውም ውኃ ያለ ውኃ ቆጣሪ የሚጠቀም እንደ ፍጆታ መጠኑ ታሪፍ ተቀምጦለታል፡፡ በዚህም መሠረት በወር እስከ ሦስት ሜትር ኪውብ የሚጠቀሙ በሜትር ኪውብ አምስት ብር ክፍያ ይፈጽማሉ፡፡ ይህ ታሪፍ እንደሚጠቀሙት የውኃ መጠን ክፍያው እየጨመረ የሚሄድ ሲሆን፣ በወር እስከ 35 ሜትር ኪዮብ የሚጠቀሙ ከሆነ በአንድ ሜትር ኪውብ 35 ብር ይከፍላሉ፡፡ ከ36 ሜትር ኪውብ በላይ የሚጠቀሙ ደግሞ በአንድ ሜትር ኪውብ 40 ብር ምክፈል እንደሚኖርባቸው ይደነገጋል፡፡
የመጠጥ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት የሚጠቀሙ ደንበኞችና ድርጅቶችን በተመለከተ የወጣው ታሪፍ በወር ከሁለት እስከ 15 ሜትር ኪውብ የሚጠቀሙ ግለሰቦች በሜትር ኪውብ ከ0.50 ሳንቲም እስከ ሁለት ብር መክፈል ይኖርባቸዋል፡፡ ነጋዴዎች፣ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ከሆኑ እስከ አምስት ብር በሜትር ኪውብ ይከፍላሉ፡፡
ከዚህ ሌላ ለቤተሰቦቹ ጥቅም ብቻ ውኃ እንዲመነጭ በማድረግ የሚጠቀም ማንኛውም ሰው በዓመት 25 ብር ይከፍላል፡፡ ውኃ በማመንጨት፣ በመስኖ ወይም በመሳብ ውኃ የሚሸጥ ሰው የሚከፍለው ክፍያ የጉድጓድ ውኃ ያመነጨ፣ የወንዝ ወይም የሐይቅ ወይም ከወንዝ በመጎተት ወይም ለመስኖ የሚሸጥ ማንኛውም ሰው ከሚፈጽመው ሽያጭ ውስጥ ሶስት በመቶ መክፈል እንደሚኖርበትም መመርያው ያመለክታል፡፡
ውኃ በማመንጨት፣ በመስኖ ወይም በመሳብ ምርት የሚያመርት ሰው የሚከፍለው ክፍያ የወንዝ ውኃ ወይም የሐይቅ መስኖ ወይም ውኃ በመሳብ ወይም የጉድጓድ ውኃ በማውጣት የሸንኮራ፣ የአበባ ወይም ማንኛውንም የደጃፍ ምርት በማምረት የሚሸጥ ማንኛውም ሰው ከሚሸጠው ጠቅላላ ዋጋ 0.5 በመቶ የሚከፍል መሆኑንም ያመለክታል፡፡
የወንዝ ውኃ ወይም የሐይቅ መስኖ ወይም ውኃ በመሳብ ወይም የጉድጓድ ውኃ በማውጣት የሸንኮራ፣ አበባ፣ የገለባ እህሎች ወይም ጥሬ እህሎችን ወይም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በጠባብ ቦታ ላይ በማምረት ለሽያጭ የሚያቀርብ ማንኛውንም የደጃፍ ምርት በማምረት የሚሸጥ ማንኛውም ሰው ከሚሸጠው ጠቅላላ ዋጋ 0.25 በመቶ ይከፍላል፡፡
የወንዝ ውኃ ወይም የሐይቅ መስኖ ወይም ውኃ በመሳብ ወይም የጉድጓድ ውኃ በማውጣት ምርት በማምረት ለቤተሰቦቹ ቀለብ የሚጠቀም ማንኛውም ሰው በአንድ ሔክታር መቶ ብር ይከፍላል፡፡
አንድ የእህል ዓይነት በአንድ ሔክታርና ከዚያ በታች በሆነ ይዞታ ላይ ለቤተሰቦቹ ቀለብ የሚውል በማምረት የሚጠቀም ማንኛውም ሰው ክፍያ ከመፈጸም ነፃ መሆኑንም ደንግጓል፡፡
የውኃ ላይ ትራንስፖርት አገልግሎት ወይም መዝናኛ አገልግሎት የሚሰጥ ግለሰብም ይህ ክፍያ የሚመለከተው ሲሆን በዚህ መሠረት ትራንስፖርት አገልግሎት ወይም መዝናኛ አገልግሎት የሚሰጥ ማንኛውም ግለሰብ ከጠቅላላ የአገልግሎት ሽያጭ ውስጥ የሚከፍለው ሦስት በመቶ እንደሚሆን ተተምኗል።
ዓሳ የማርባት ወይም የማስገር ሥራ የሚሠራ ግለሰብ የሚከፍለው ክፍያ በተፈጥሮ ሐይቅ ወይም በተፈጥሮ ወንዝ ውስጥ ሰው ከሚያደርግለት ድጋፍ ውጪ የሚራቡ ዓሳዎችን በማስገር የሚሸጥ ማንኛውም ግለሰብ ከሚፈጽመው ጠቅላላ ሽያጭ ውስጥ አምስት በመቶ የሚከፍል ይሆናል፡፡
በሐይቅ ወይም በወንዝ ውስጥ ወይም በተኛ ውኃ ውስጥ ዓሳ በማርባት በማስገር የሚሸጥ ማንኛውም ግለሰብ ከሚፈጽመው ጠቅላላ ሽያጭ ውስጥ አንድ በመቶ ገቢ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
በዚህ ድንጋጌ ከጠቅላላ ገቢያቸው ሳይሆን ከሚያገኙት ትርፍ ታሳቢ ተደርጎ ክፍያ ከሚፈጽሙ ዘርፎች ከነዚህ መካከል ሌላ ግለሰብ ያረባቸውን ዓሳዎች በዕርባታ ቦታ በመግዛት በማስረግ ለገበያ አቅርቦ የሚሸጡ ተብለው የተለዩ ናቸው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች የሚሸጥ ማንኛውም ግለሰብ ከሚያገኙት ጠቅላላ ትርፍ ውስጥ ሁለት በመቶ የሚከፍል ይሆናል፡፡
የመብራት ኃይል ክፍያ ከውኃ ኃይል የሚያመነጭ ወይም የመብራት ኃይል የሚያመርት ማንኛውም ግለሰብ ከጠቅላላ የሽያጭ ዋጋ ውስጥ 0.5 በመቶ መክፈል እንደሚኖርበት እንዲሁም በውኃ ልማት ወይም ግንባታ ሥራ ምክር አገልግሎት የሚሰጥ ግለሰብ ከሚከፈለው ጠቅላላ ዋጋ ውስጥ አንድ በመቶ ይከፍላል፡፡
የመጠጥ ውኃ አቅራቢዎች ወይም ውኃ የሚያስቀይሱ የሚከፍሉት ክፍያዎች ንፁህ የመጠጥ ውኃ የሚሸጥ ድርጅት ከሚሸጠው ሽያጭ ውስጥ አንድ በመቶ ታሪፍ ተጥሎበታል፡፡ እንዲህ ያሉ ድንጋጌዎች በተለያዩ ዘርፎች በዝርዝር የቀረቡ ሌሎች ታሪፎችን የያዘው ይህ መመርያ ተፈጻሚ እንዲሆን የክልሉ የውኃና ኢነርጂ ሀብት ልማት ቢሮ እንቅስቃሴ እያደረገ ሲሆን፣ በዚህ መመርያ መሠረት ክፍያ ማስፈጸም የተጀመረባቸው ቦታዎች መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ የክልሉ መመርያ ግን በየዘርፉ ባሉ ተቋማት ቅሬታ ያስነሳ ሲሆን ለፈንዱ ገቢ ይሆናል ተብሎ የተቀመጠው ተመን የአምራቹን ወጪ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል ያሉ የተለያዩ በየዘርፎች በማኅበራት መመርያው ላይ ያላቸውን ቅሬታ ለክልሉ የውኃና ኢነርጂ ቢሮ አቤት እስከማለት መድረሳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ በተቀመጠው መመርያ መሠረት ክፍያ ካልፈጸሙ የውኃ ጉድጓድ የመጠቀም ፈቃዳቸው እንደማይታደስላቸው የተገለጸላቸው እንዳሉ ሁሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከሰሞኑ መመርያውን ለማስፈጸም የተደረጉ እንቅስቃሴዎች ያልተገባ ክፍያ እስከመጠየቅ የተደረሰበት በመሆኑ ጉዳዩን ለቢሮ በማመልከት ውይይት መደረጉንም ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ በአዋጁም ሆነ በመመርያው ላይ የሚመለከታቸው አካላት ውይይት ሳያደርጉበት የወጣ ስለመሆኑ የሚገልጹ የተለያዩ አምራች ዘርፎች ተወካዮች ስለጉዳዩ እንድንወያይበት የተደረገው አዋጁ ከፀደቀ በኋላ ነው ይላሉ፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው አንድ የውኃ አምራች ባለቤት በወጣው መመርያ መሠረት ለተጠቀምበት ውኃ እንድንከፍል እየተጠየቅን ያነው ከአጠቃላይ ሽያጫችን አንድ በመቶ በመሆኑ የውኃ አምራችን ወጪ ያንራል ይላሉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አከፋፈሉ ከአጠቃላይ ወጪ ከመሆን ይልቅ ከታክስ በኋላ ቢሆን የተሻለ እንደነበር ጠቅሰው ይህንኑ ጉዳይ በማኅበራቸው በኩል ቢያመለክቱም ተቀባይነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ችግሩ ይህ ብቻ ያለመሆኑን የሚጠቅሱት እኝሁ የታሸገ ውኃ አምራች ባለቤት እንዲህ ያለው ድንጋጌ ወደ ተትግበራ የገባው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ብቻ መሆን በገበያ ላይ ተፅዕኖ ያሳርፋል የሚል ሥጋትም አላቸው፡፡
ይህም ለውኃ ፈንድ ተብሎ ከየፋብሪካዎቹ የሚሰበሰበው ገቢ በክልሉ ያሉ የውኃ አምራች ላይ ብቻ የሚፈጸም ከሆነ በሌሎች ክልሎች ላይ ያሉ አምራቾች የማይመለከታቸው ከሆነ ፈንዱ የማይመለከታቸው ፋብሪካዎች ዋጋ ቀንሰው ገበያ ውስጥ አሸናፊ እንዲሆኑ ዕድል ይፈጥራል በማለትም አብራርተዋል፡፡ የታሸገ ውኃ ደግሞ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላኛው ክልል በመሄድ ጭምር የሚሽ በመሆኑ ገበያ ላይ ችግር ስለሚፈጥር ይህም ጉዳይ ችግር እንደሆነባቸው ጠቅሰዋል፡፡
በአትክልት አበባና ፍራፍሬ ምርት ላይ የተሰማሩ እርሻዎች ከፍተኛ ገቢ የሚሰበሰብባቸው ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከነዚህ እርሻዎች ለፈንዱ ገቢ የሚሆን ወጪያቸው ከጠቅላላ ገቢያቸው 0.5 በመቶ ታሳቢ ተደርጎ እንዲከፍሉ የሚደረግ በመሆኑ ታውቋል፡፡ አዲሱን መመርያ ከማስተግበር አንፃር በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ከክልሉ ባለሥልጣናት ጋር ከአንድ ሳምንት በፊት የተለያዩ ሲሆን፣ በመመርያው በተቀመጠው ታሪፍ መሠረት ክፍያ መፈጸም እንዲጀምሩ ተገልጾላቸዋል፡፡
በአንዳንድ የክልሉ ከተሞች ክፍያውን ለመፈጸም የቀረበ እርሻዎች የተጠየቅነው የገንዘብ መጠን በመመርያው ከተቀመጠው በላይ ነው በሚል ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት የኦሮሚያ ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ጉዳዩን ዓይቶ ዕርምት እንደሚወስድበት እንደተገለጸላቸው ተችሏል፡፡ ከዚህ ውጭ መመርያውን መተግበር ግድ መሆኑ እንደተገለጸላቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ሆኖም እንዲህ ያለው አዲስ ክፍያ በተለይ ላኪዎች ላይ ጫና የሚፈጥር ነው የሚሉት እንደሚያለክተው በአበባ አትክትልና ፍራፍሬ አምራች የሆኑ ኢንቨስተሮች ለውኃ ፈንድ ተብሎ የተባለው ታሪፍ ከዚህ ቀደም ይከፍሉ ከነበሩት በእጅጉ የጨመረ በመሆኑ የእርሻዎች ወጪ እንዲያደርግ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ይህም የማምረቻ ወጪን የሚጨምር በመሆኑ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ዋጋ ለማቅረብ ሊፈትን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ለአገር ውስጥ የሚቀርበውም ምርት ቢሆን ዋጋውን ከፍ ስለሚያደርግ ክልሉ መመርያውን ዳግም ቢፈትሽ የተሻለ ይሆናል ብለዋል፡፡ በመስኖ የሚመሩ የተለያዩ እርሻዎችም ይህ ክፍያ የሚመለከታቸው በመሆኑ የመስኖ ሥራ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችልም የገለጹ አሉ፡፡ ከሰሞኑ ከቢሮው ጋር ውይይት ያደረጉ የእርሻ ባለሀብቶች በአተገባበር ላይ ችግር ካለ ቢሮው ማስተካከያዎችን እንዲያደርግ የገለጸላቸው ቢሆንም አጠቃላይ የአዋጁ ይዘት ግን ብዙ ሊሻሻሉ የሚገቡት ነገሮች እንደነበሩት ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
የኦሮሚያ ክልል እንዲህ ያለውን መመርያ ያወጣበትን ምክንያት በተመለከተ በአዋጁ መግቢያ ላይ የክልሉን የውኃ ሀብት በመንከባከብና በመጠበቅ የውኃ ሀብትን ከመድረቅና ከብክለት ለመጠበቅ በዘላቂነት ጥቅም ላይ ማዋልንና የመጪውን ትውልድ ጥቅም ማስጠበቅ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ከዚህም ሌላ በክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው የተሠሩ የውኃ ፕሮጀክቶች ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ ለማስቻል ድንጋጌው ማስፈለጉንም አመልክቷል፡፡
በተለይም የውኃ ሀብት ልማት ሥራዎችን በመንግሥት አቅም ብቻ በመፈጸም እየጨመረ የሚሄደውን የውኃ ፍላጎት የማይችል በመሆኑ የውኃ ሀብት ፈንድ በማቋቋም ለእነዚህ ሥራዎች የሚል ቋሚ የፋይናንስ ምንጭ እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት ከተለያዩ ተቋማት እንደ የአገልግሎታቸው የማሰባሰብ ፈንድ እንደተጠበቀ ሆኖ ፈንዱን ለማቋቋም የተለያዩ የገቢ ምንጮችንም ታሳቢ በማድረግ በድንጋጌው እንዲካተት ተደርጓል፡፡
የፈንዱ ገቢም የኦሮሚያ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የክልሉ መንግሥት ለፈንዱ የሚመድበውን በጀት፣ በጀቱ ከታወጀ በኋላ በፈንዱ የባንክ ሒሳብ ቁጥር ገቢ የሚደረግ መሆኑንም በአዋጁ ተጠቅሷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በውኃ ተፋሰሶች አጠቃቀም ላይ አስገዳጅ ታሪፍ የሚጥል አስገዳጅ ደንብ ዝግጅት መጠናቀቁንና ይህም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ መገለጹ አይዘነጋም፡፡ የተቀናጀ የውኃ ሀብት አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደተደረገበት ታውቋል፡፡