
ዜና ‹‹ሥርዓት ሊያናጋ የሚችል ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ አንድምታ ያለውን የሙስና ወንጀል መቆጣጠር እየተቻለ…
ቀን: February 2, 2025
በሀብት ማስመለስ አዋጁ አሥር ዓመት ወደ ኋላ ተመልሶ የሚታየው የፍታብሔር እንጂ የወንጀል ጉዳይ አይደለም
የፍትሕ ሚኒስቴር
የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነሩ ተቋማዊ የሆኑና ሥርዓታዊ የሆኑ ሥርዓቱን ሊያናጉ የሚችሉ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ አንድምታ ያላቸውን የሙስና ወንጀሎች መቆጣጠር እየተቻለ መሆኑን ገለጹ፡፡
ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርካቶ (ደ/ር) የስድስት ወራት ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት፣ ፖለቲካና ሥርዓታዊ አንድምታ ያለውን ሙስና መቆጣጠር መቻሉን ጠቅሰው፣ አስተዳደራዊ የሆኑ ሙስናዎች የሕግ ማስከበሩን ሥራ አጠናክሮ ማስቀጠል ከተቻለ ወደ ሥርዓታዊና ተቋማዊ ሙስና እንዳያድጉ ከምንጩ ማድረቅ ይችላል ብለዋል፡፡
ኮሚሽነሩ እንደገለጹት አስተዳደራዊ የሆኑ፣ በግለሰብ ደረጃ የሚፈጸሙ በሚሊዮኖችና በትንንሽ ገንዘቦች፣ በብዙ ሔክታሮች የሚደረጉ ስርቆቶች ስለመኖራቸው ግን እርግጠኛ ሆነን መናገር እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡
በተቋም ደረጃ ሥርዓት ዘርግቶ ሙስና እንሥራ በሚል ትስስር የሚፈጥሩ አካላት ዕድላቸው በጣም ዝቅተኛ መሆኑን በግምገማ አረጋግጠናል ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ‹‹ሥርዓትና አሠራር ዘርግተው ከተለያዩ አካላት ጋር ትስስር ፈጥረው በመደበኛነት ተቋምን ለስርቆት ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት ግን ዕድሉ ቀንሷል፤›› ብለዋል፡፡
የሀብት ማስመለስ አዋጅ ወደ መሬት እንዲወርድ የሚቀረፁ አዋጆች በፍጥነት እንዲፈጸሙ የጠየቁት ኮሚሽነሩ፣ ይህ ከተፈጸመ ሀብት ከአገር እንዳይሸሽና በአገር ውስጥም ያለው ሙስና ከምንጩ እንዲደርቅ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡
የሙስና ወንጀል ፍሬ ነገር ያላቸው 136 ጥቆማዎች ለተቋማቸው ቀርበው ለፖሊስ መላኩን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ በንብረት ማስመለስ አዋጅ አማካይነት ተጣርቶ ሪፖርቱ በቀጣይ ይቀርባል ብለዋል፡፡ ሀብታቸውን የሚያስረዳ ማስረጃ አቅርበው ማስረዳት ካልቻሉ ‹‹እናንተ ባፀደቃችሁት የሀብት ማስመለስ አዋጅ መሠረት ሀብቱን እንወርሳለን፤›› ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የፍትሕ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሃና አርዓያ ሥላሴ የሀብት ማስመለስ አዋጅን አስመልክተው ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በመርሕ ደረጃ የንብረት ማስመለስ ውሳኔ የሚወሰነው በወንጀል ጥፋተኝነት ላይ በተመሠረተ መልኩ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
በዚህ አዋጁ መካከል ወደ ኋላ አሥር ዓመታት ተመልሶ ይሠራል ሲባል፣ የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነትን እንጂ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል አለመሆኑን ገልጸው፣ የወንጀል ሕግ ወደ ኋላ ተመልሶ አይሠራም ከሚለው ድንጋጌ ጋር ምንም የሚጣረስ አይደለም ብለዋል፡፡
በመሆኑም ምንጩ ያልታወቀ ንብረት የሚያስከትለው የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነት እንጂ የወንጀል ተጠያቂነት የማያስከትል በመሆኑ፣ ከሕጋዊነት መርሕ ጋር ተጣጥሞ የሚተገበር ነው ብለዋል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴርና በዓቃቤ ሕግ በሚደረገው ማጣራት እንዳለ ሆኖ፣ በመጨረሻ ከወንጀል ነፃ ያገኘው ፍሬ ነው ወይም በወንጀል የተገኘ ነው የሚለው ውሳኔ በፍርድ ቤት የሚወሰን እንደሚሆንም አብራርተዋል፡፡
ሚኒስትሯ አንድ ሰው ላይ የንብረት ማስምለስ ወይም የንብረት መወረስ ውሳኔ ለመወሰን የሚቻለው፣ የመጨረሻ የወንጀል ጥፋተኝነት ውሳኔ በፍርድ ቤት ሲሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በልዩ ሁኔታ በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ የንብረት መወረስ ሊወሰን እንደሚቻል አስረድተው፣ የወንጀል ጥፋተኝነትን በተመለከተ ሁኔታ የንብረት መወረስ ውሳኔ ሊወስን ይችላል ብለዋል፡፡
ለአብነትም በወንጀል ድርጊት የተጠረጠረ ሰው ሲሞትና ከአገር ሲሸሽ በንብረት ማስመለስ አዋጅ አማካይነት ሊፈጸም እንደሚችለ ተናግረዋል፡፡ በአስፈጻሚ አካል በዘፈቀደ የሚተገበር አይደለም ያሉት ሚኒስትሯ ሒደቱና ውሳኔው በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል፡፡ የንብረት ማስመለስ አዋጅ ጥሮና ለፍቶ ለሚሠራው ሕዝብ መልካም ዜና ነው ሲሉም ገልጸውታል፡፡