https://www.ethiopianreporter.com/137964/

ዜና ጉባዔና ምርጫ አድርጎ ርክክብ የፈጸመው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት የፍርድ…

ታምሩ ጽጌ

ቀን: February 2, 2025

ከሁለት ሳምንታት በፊት ጥር 11 ቀን 2017 ዓ.ም. 18ኛውን ጠቅላላ ጉባዔ በማድረግ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና የቦርድ አባላትን በመምረጥ፣ የሥልጣን ርክክብ ፈጽሞ የነበረው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ ድርጊቱን የፈጸመው፣ የማኅበራት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 341/1995 እና በ2004 ዓ.ም. የወጣውን መተዳደሪያ ደንብ ድንጋጌዎች የጣሰና ፍርድ ቤት ጥር 7 ቀን 2017 ዓ.ም. የሰጠውን ትዕዛዝ የጣሰ በመሆኑ በትዕዛዙ መሠረት እንዲፈጽም ጥያቄ ቀረበ፡፡

የምክር ቤቱ የቦርድ አባል አቶ አበራ አበጋዝ እሸቴ በጠበቃቸው አማካይነት ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም.፣ ክስ መሥርተውባቸው ለነበሩት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ ለምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት (በተደረገው 18ኛ ጠቅላላ ጉባዔ  ተቀይረዋል) ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጥና ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ባቀረቡት ደብዳቤ፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ኢንቨስትመንት ምድብ ሦስተኛ ንግድ ችሎት ጥር 7 ቀን 2017 ዓ.ም. የሰጠው ትዕዛዝ ተፈጻሚ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

የጉዳዩ መነሻ አቶ አበራ አበጋዝ ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባልነታቸው መታገዳቸው ሲሆን፣ አቶ አበራ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 154 እና 205 ድንጋጌዎች መሠረት፣ የተጣለባቸው ዕድግ እንዲነሳላቸውና ምክር ቤቱ በሚያደርገው 18ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በዕጩነት እንዳይወዳደሩ ምክር ቤቱና ፕሬዚዳንቷ ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ያስተላለፉት ውሳኔ እንዲሻርላቸው፣ ከላይ ለተጠቀሰው ፍርድ ቤት ማቅረባቸው በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ክስ የቀረበለት የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ንግድና ኢንቨስትመንት ምድብ ሦስተኛ ችሎት፣ በቀረበለት ክስ መሠረት ምክር ቤቱ ሊያካሂድ የነበረውን ጠቅላላ ጉባዔ እንዳይካሄድ ዕግድ በመጣሉ፣ ከሳሽና ተከሳሾች ጉዳዩን በዕርቅ ለመጨረስ ስምምነት ላይ ደርሰው እንደነበር የፍርድ ቤት ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ሰነዱ እንደሚገልጸው ጉዳዩን በዕርቅ ለመጨረስና ሁሉንም ነገር በሕግና በሕግ ብቻ ለመፈጸም ጥያቄውን ያቀረቡት፣ ንግድ ምክር ቤቱና ፕሬዚዳንቷ ወ/ሮ መሰንበት መሆናቸውንም ሰነዱ ያብራራል፡፡

ፍርድ ቤቱም ሁለቱ ወገኖች ጉዳዩን በዕርቅ ለመፈጸም ተማምነውና ፈቅደው ያደረጉት መሆኑን አረጋግጦ፣ ክሱ እንዲቋረጥና መዝገቡ እንዲዘጋ ማድረጉንም ሰነዱ ይገልጻል፡፡

ከሳሽ አቶ አበራ፣ በወ/ሮ መሰንበት ፊርማ ከአባልነት የታገዱትና በ18ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ዕጩ ሆነው እንዳይቀርቡ ታኅሳስ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. የተሰጣቸው የዕግድ ደብዳቤ፣ የምክር ቤቱን መተዳደሪያ ደንብ የሚጥስ በመሆኑ፣ ደብዳቤው መሻሩ ተገልጾ በአድራሻ ለተላከላቸው ለምክር ቤቱና ለምክር ቤቱ ዳይሬክተሮች ቦርድ አባሎች፣ እንዲሁም ግልባጭ ለተደረገላቸው ተቋማት በሙሉ ለመጻፍ ሁለቱም ወገኖች መስማማታቸውን ሰነዱ ያስረዳል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ለጠቅላላ ጉባዔ ጥሪ የተደረገላቸው አባላት እንዲገኙ የማድረግ፣ የማስተባበርና የመፈጸም፣ አስፈላጊ ዝግጅቶችን የማከናወን ተግባርና ኃላፊነት እንዳለበት ከሳሽና ተከሳሾች ተማምነው ስምምነት መፈጸማቸውም ተገልጿል፡፡ ምክር ቤቱ ለጠቅላላ ጉባዔ አባላት ጥሪ የሚያደርግበት፣ የሚያሳትፍበት፣ ምርጫ የሚያከናውንበት፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት የሚመረጡበት፣ ብቸኛ ተፈጻሚነት ያለው ሕግ የማኅበራት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 341/95 እና በ2004 ዓ.ም. ፀድቆና ተመዝግቦ የሚገኘው መተዳደሪያ ደንብ መሆኑንም ተስማምተውና ተማምነው በፊርማቸው በማፅደቅ ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት ሰነድ ይገልጻል፡፡

በአጠቃላይ የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ የሚካሄደው፣ በነበሩትና ባልተለወጡት አሠራሮች፣ በንግድና ዘርፍ ማኅበራት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 341/95 እና በሥራ ላይ በሚገኘውና በምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት መሆኑን ከሳሽ አቶ አበራና ፕሬዚዳንቷ ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ (በራሳቸውና ምክር ቤቱን ወክለው) ለፍርድ ቤቱ በፊርማቸው አፅድቀው ያቀረቡት የስምምነት ሰነድ ያሳያል፡፡ ፍርድ ቤቱም ሁለቱ አካላት ያቀረቡትን የስምምነት ሰነድ ከመረመረ በኋላ፣ ምክር ቤቱና ፕሬዚዳንቷ ከሳሽ ለጠበቃ፣ ለዳኝነትና ለቴሌምብር ቀረጥ የከፈሉትን 200,090 ብር ለሁለት ተካፍለው፣ ኪሳራውን እንዲሸፍኑ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ በስምምነቱ መሠረት ተፈጻሚ እንዲሆን ውሳኔ መስጠቱንና መዝገቡን ጥር 7 ቀን 2017 ዓ.ም. መዝጋቱን ሰነዶቹ ያብራራሉ፡፡

ከሳሽ አቶ አበራ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት ተከሳሾች (ምክር ቤቱና ፕሬዚዳንቷ ወ/ሮ መሰንበት) እንዲፈጽሙ ሐሙስ ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት 18ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ጥር 11 ቀን 2017 ዓ.ም. በማድረግ አዲስ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና የቦርድ አባላት ምርጫ  አድርጎ፣ የሥልጣን ርክክብ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ምርጫው በውዝግብ የተሞላ እንደነበርና ምክንያቱ ደግሞ፣ የምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብና የማኅበራት ማቋቋሚያ አዋጅን ያልተከተለ በምርጫ አመቻች ኮሚቴ አማካይነት ከሁሉም ክፍላተ ከተሞች ከምርጫው አንድ ቀን በፊት የአባልነት ፎርም በመሙላት ተወክለዋል ከተባሉ 55 አባል ነጋዴዎች መካከል 11ን ለቦርድ አባልነት በመምረጥ ለጉባዔው መቅረባቸው ሕገወጥና ተገቢ አይደለም በሚል መሆኑ በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ነባር ነጋዴዎችና አባላት በ18ኛው የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተፈጽመዋል የሚሏቸው ስህተቶች በርካታ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ በአዋጁና በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ቀኑና ቦታው ተወስኖ ጠቅላላ ጉባዔው እንደገና እንዲደረግ፣ ለአባላቱ በመገናኛ ብዙኃን ጥሪ እንዲተላለፍ፣ የ2016 ዓ.ም. ሥራ አፈጻጸምና የኦዲት ሪፖርት ታትሞ እንዲዘጋጅ፣ እንዲፈርስ የተደረገው የክሪደንሺያል ኮሚቴ ወደ ሥራው እንዲመለስ፣ ቢያንስ ከ500 በላይ የሚሆነውና የአባልነት ክፍያቸውን ያጠናቀቁና ውዝፍ ዕዳ የሌለባቸው አባላት መኖራቸውን በማረጋገጥ ምርጫውም በእጅ ማውጣት ሳይሆን በታተመ የምርጫ ካርድ በሚስጥር በሳጥን ውስጥ እየተከተተ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና የቦርድ አባላት ምርጫ መካሄድ እንደለበትና የስብሰባው አጠቃላይ ሒደት ቃለ ጉባዔ ለንግድ ቢሮ መቅረብ ቢኖበትም፣ ያ ሳይደረግ ምርጫው ተደርጓል ማለት ‹‹ሪፎርም እየተባለ ነጋ ጠባ ሲነገር የነበረውን ሕግ የማፍረስና የመጣስ›› ሒደት በመሆኑ፣ ምርጫው በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት እንደገና መካሄድ አለበት የሚል አቤቱታ እያሰሙ መሆኑ ታውቋል፡፡