መጽሐፉ ሲመረቅ

ኪንና ባህል ሕገ መንግሥቱንና ፌዴራሊዝም ሥርዓትን የቃኘው መጽሐፍ

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: February 2, 2025

የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ አቶ ተስፋዬ ንዋይ፣ በአፋን ኦሮሞ የጻፉት ሕገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም ሥርዓት (Heerafi Sirna Federaalizimii) የተሰኘ መጽሐፋቸውን ጥር 18 ቀን 2017 ዓ.ም. ለንባብ አብቅተዋል፡፡

 መጽሐፉ ሕገ መንግሥትና ፌደራሊዝም ላይ በማተኮር በሕገ መንግሥቱ ሒደት ላይ የነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን ለይቶ ለማስቀመጥ የሞከረ መሆኑን ጸሐፊው በምረቃው ዕለት ተናግረዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብታቸውን እንዲያስጠብቁ በሚያስችል መልኩ የተደራጀ በመሆኑ፣ ይህንንም መነሻ በማድረግ ለመተንተን መሞከራቸውን የገለጹት ጸሐፊው፣ በቀጣይ ወደ አማርኛና ወደ ሌሎች ቋንቋዎች በመተርጐም ተደራሽነቱን ለማስፋት እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡

‹‹በተለይ በሌሎች መጽሐፎች ያልተሞከረ፣ ነገር ግን እኔ የሞከርኩት ብዬ የማስበው›› ሲሉ የተናገሩት፣ ሕገ መንግሥቱ ላይ ትኩረት በማድረግ አጠቃላይ የፌዴራል ሥርዓቱን  ለመገምገም መሞከራቸውን አመልክተዋል፡፡

መጽሐፉ ሰባተኛ ሥራቸው ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ካሳተሟቸው መካከል የፕሮጀክት አመራር ሳይንስና ጥበብ፣ የአመራር ክህሎት፣ የመሬት ጉዳይ ሕጉና አተገባበሩ፣ የፍትሕ ጉዳይ የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡