

ዜና አዲሱ የኢሰመኮ ኮሚሽነር ከአስፈጻሚው ጋር በመተባበር እሠራለሁ አሉ
ቀን: February 2, 2025
- ‹‹የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ጠንካራ አመራርና ውጤታማ የሰብዓዊ መብቶች ሥራ የሚጠይቅ ነው››
ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ
ለሰባት ወራት ያህል በምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ሲመራ የነበረውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በዋና ኮሚሽነርነት እንዲመሩ የተሾሙት አቶ ብርሃኑ አዴሎ፣ በሥልጣን ዘመናቸው ከአስፈጻሚው መንግሥት ጋር በትብብር እንደሚሠሩ አስታወቁ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ጉባዔው አቶ ብርሃኑ አዴሎን ዋና ኮሚሽነር አድርጎ መሾሙ ይታወሳል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ ሹመታቸው በፓርላማ ካፀደቀላቸው በኋላ ለአንድ የመንግሥት ሚዲያ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹አገርን ማገልገል የመሰለ ነገር የለም፣ ትልቅ ክብር ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ውጤት የሚመጣው ተባብሮ ሲሠራ ስለሆነ በእኔ ሹመት ወቅት በጎሪጥ ሳይሆን ተባብሮ መሥራት ትልቁ ተግባራችን ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
በመሆኑም ሰብዓዊ መብቶችን ለማሻሻል፣ ግንዛቤ ለማስጨበጥና ጥሰቶችን ለማስቆም ከመንግሥት አካላት ጋር ተባብረው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡
‹‹በዋነኝነት ለአገሬ የሚሆኑ ጥሩ ጥሩ ሥራዎች እሠራለሁ፤›› ያሉት አዲሱ ዋና ኮሚሽነር፣ ‹‹ከአስፈጻሚ አካላት ጋር ነፃነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ ተቀራርበን የመብት ጥሰት እንዳይኖር፣ ሰብዓዊ መብትን ማክበር ምን እንደሆነ እየተግባባንና እየተማማርን እንሠራለን፤›› ብለዋል፡፡
የዕጩ ዋና ኮሚሽነር አመላመልን በተመለከተ የተዘጋጀውን የውሳኔ ሐሳብ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ በአጠቃላይ በሕዝብ ከተጠቆሙት 45 ወንዶችና አምስት ሴቶች ዕጩዎች መካከል አቶ ብርሃኑ ከፍተኛውን ውጤት ማምጣታቸውን መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
የውሳኔ ሐሳቡ ከተሰማ በኋላ አስተያየት የሰጡት የአብን የምክር ቤት ተወካይ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ ‹‹እኔ ሥጋቴ ለምሳሌ የቀድሞውን ዋና ኮሚሽነር የዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ዓይነት ሰው ሲሾም፣ ለአገራችን የሰብዓዊ ምኅዳር ብሎም ለገዥው ፓርቲ ጥሩ ገጽታ ሰጥቶ ነበር ብዬ አስባለሁ፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ብርሃኑ የብልፅግና ፓርቲ አባል ይሁኑ አይሁኑ እንደማያውቁ የገለጹት ደሳለኝ (ዶ/ር)፣ ኮሚቴው ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በመውሰድ፣ በግልጽ የሚታይ የፖለቲካ ተሳትፎና አመራር የሌላቸው ሰዎች ጠፍተው ነው ወይ ሲሉ ጠይቀው ነበር፡፡
አክለውም ለአብነት ያህል በተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነርነት እያገለገሉ የነበሩት ዓይነት ሰዎች ተቋሙን የተሻለ ገለልተኛ በማድረግ፣ ከአስፈጻሚው አካል ተፅዕኖ ነፃ በሆነ መንገድ ይመሩት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በስፋት የሚታይ ተቋም በመሆኑ ሹመቱ ጥሩ ያልሆነ ገጽታ አያመጣም ወይ ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የምክር ቤት ተወካይ አብርሃም በርታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኮሚሽኑ ገለልተኛ ሆኖ ሊመራ እንደሚገባና መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽም እንዲያስተካክል ግፊት ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም የገለልተኝነት ጥያቄ ሲነሳበት እንደነበር የገለጹት አባሉ፣ ባለፉት ጊዜያት ኮሚሽኑ ያወጣቸው ሪፖርቶች የዚህን መንግሥት ገጽታ ግንባታ ያስተካከሉ ናቸው ብለዋል፡፡
አፈ ጉባዔው ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ የተሾሙት ግለሰብ እያንዳንዱ ዕጩ ምን መሥራት እንዳሰበ ዕቅዱን እንዲያቀርብ ተደርጎ ከተገመገመ በኋላ በተሰጠ ነጥብ አብላጫ ያገኙ መሆናቸውን ገልጸው፣ በውድድሩ ኮሚሽኑ ውስጥ ያሉ አካላት ጭምር ተሳትፈውበታል ብለዋል፡፡ አፈ ጉባዔው ተሿሚው ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
የአምስት ዓመታት የዋና ኮሚሽነርነት ጊዜያቸውን አጠናቅው ከተሰናበቱ ሰባት ወራት የሆናቸውን ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)ን የሚተኩት አቶ ብርሃኑ፣ የካፋ ዞን ተወላጅ መሆናቸውን፣ በሕግ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው መሆኑን አፈ ጉባዔው አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር፣ የአዕምሯዊ ንብረት ዋና ዳይሬክተር የክልል የፀጥታና ደኅንነት ኃላፊነት በመሆን የሠሩ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡
አዲሱ ሹመት ከመፅደቁ አስቀድሞ በርካቶች ኮሚሽኑን በምክትል ዋና ኮሚሽነርነት እየመሩ የሚገኙት ራኬብ መሰለ የዋና ኮሚሽነርነት ቦታውን ይይዛሉ የሚል ሰፊ ግምት ተሰጥቷቸው ነበር፡፡
አቶ ብርሃኑ የዋና ኮሚሽነርነት ሹመቱ ከፀደቀላቸው በኋላ፣ የኮሚሽኑ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር የነበሩትን ራኬብን ጠቅሶ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ወቅታዊው የአገሪቱ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ጠንካራ አመራርና ውጤታማ የሰብዓዊ መብቶች ሥራ የሚጠይቅ ነው፤›› ማለታቸውን አስታውቋል፡፡