ማኅበራዊ
በልማት ምክንያት ተቋማቸው የፈረሰባቸው አካል ጉዳተኛ ነጋዴዎች ወደ ልመና መሰማራታቸውን ገለጹ

አበበ ፍቅር

ቀን: February 2, 2025

በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ባለው የኮሪደር ልማት መሥሪያ ቦታቸው ከፈረሰባቸው አካል ጉዳተኛ ነጋዴዎች አብዛኛዎቹ ወደ ልመና መሰማራታቸው ተነገረ፡፡

በልማት የተነሱና ምትክ ቦታ ያልተሰጣቸው አብዛኛዎቹ አካል ጉዳተኛ ነጋዴዎች፣ በቤተ ክርስቲያን በርና በጎዳናዎች ላይ ለልመና መሰማራታቸውን፣ የአዲስ አበባ አካል ጉዳተኛ ነጋዴዎች ማኅበር ሰብሳቢ አቶ እዮብ ደስታ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

መሥሪያ ቦታቸው ለኮሪደር ልማት ሲፈርስ ምትክ ቦታ ይሰጣችኋል ተብለው እንደነበር የተናገሩት አቶ እዮብ፣ ከፈረሰ በኋላ ምንም ዓይነት ቦታ እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

 ከቂርቆስና ከአዲስ ከተማ ክፍላተ ከተሞች በልማት ከተነሱ 380 አካል ጉዳተኞች 20 በመቶ የሚሆኑት እንኳን ወደ ሥራ እንዳልገቡ ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡

ከአዲስ ከተማ ብቻ እሳቸውን ጨምሮ ከ90 በላይ የአካል ጉዳተኞች እንዳሉ የጠቀሱት አቶ እዮብ፣ ከሚድሮክ ኩባንያ ይሰጣሉ የተባሉ አምስት ኮንቴይነሮችን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ኮንቴይነሮቹ አንድ ለአምስት ለተደራጁ ለ25 አካል ጉዳተኞች ይሰጣሉ ቢባልም፣ እስካሁን ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንደሌለ አቶ እዮብ አብራርተዋል፡፡

በዚህም በርካታ አካል ጉዳተኞች ጎዳና ላይ ለልመና መውጣታቸውን የተናገሩት ሰብሳቢው፣ ልጆቻችንን ጎዳና ይዘን አንወጣም ያሉ አካል ጉዳተኞች ወደ ድሬዳዋ፣ ሐረርና ጅግጅጋ ከተሞች እየሄዱ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

ቀደም ሲል በአካል ጉዳተኞች ላይ ችግር ሲደርስ ወደ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በመሄድ ቅሬታ ያቀርቡ እንደነበር የተናገሩት አቶ እዮብ፣ አሁን ግን ሁሉም ተስፋ በመቁረጥ ወደ ልመና ተሰማርተዋል ሲሉ አክለዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከአገር ጥበብ ማደራጃ ማኅበር የተሰናበቱ ከ100 በላይ አካል ጉዳተኛ ሠራተኞች ለልመና ወደ ጎዳና መውጣታቸውን፣ የድርጅቱ አስተባባሪ አቶ ዋሴ ብርሃኔ ተናግረዋል፡፡

የአገር ጥበብ ማደራጃ ድርጅት በ1959 ዓ.ም. በየካ ክፍለ ከተማ እንደ ተቋቋመ የጠቀሱት አቶ ዋሴ፣ በ2013 ዓ.ም. የ49 ዓመት ያልተከፈለ የመሬት ግብር ግማሽ ሚሊዮን ብር መክፈላቸውን ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ ከመንግሥት የሚጠበቅበትን ግብር በአግባቡ በመክፈል ከ150 በላይ ሠራተኞችን በመያዝ የተለያዩ የዕደ ጥበብ ምርቶችን በማምረት ይተዳደሩ እንደነበር አቶ እዮብ አስረድተዋል፡፡

ድርጅቱ በኮሪደር ልማት ምክንያት በመፍረሱ ሠራተኞች ተበትነው ግማሾቹ ለልመና ጎዳና ሲወጡ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ወደ መቄዶኒያ አረጋዊያን መረጃ ማዕከል መግባታቸውን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

ሠራተኞቹ በሽመና፣ በምንጣፍ ሥራ፣ በኅትመት፣ በቤትና ቢሮ ዕቃዎች፣ በልብስ ስፌት ሥራና በሌሎች በርካታ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ሲሠሩ መቆየታቸውን አቶ ዋሴ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ተቋሙ ከ25 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የአካል ጉዳተኞችን የሚወክል ነበር ያሉት አስተባባሪው፣ አሁን ግን ሁሉም ሠራተኞች ተሰናብተው ቦታው ታጥሮ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በውስጡ የነበሩ የመሥሪያ ማሽኖች በአንድ የመንግሥት ተቋም መጋዘን ታሽገው እየተጠበቁ መሆኑን አቶ ዋሴ ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ ፈርሶ በምትኩ ሱቅና ሌሎች ሼዶች ይሰጣችሁ ተብለው እንደነበር የተናገሩት አቶ ዋሴ፣ ነገር ግን አሠራሩ ውስን ሰዎችን ብቻ ተጠቃሚ ስለሚያደርግና የድርጅቱን ህልውና ጨርሶ የሚያጠፋ በመሆኑ ሳይስማሙ መቅረታቸውን አክለዋል፡፡ ድርጅቱን በነበረበት አሠራር የሚያስቀጥል ምትክ ቦታ ተሠርቶ እንዲሰጣቸው እንደሚፈልጉ ነው አቶ ዋሴ ያስረዱት፡፡

ተቋሙ ነገ ሌሎች አካል ጉዳተኞች የሚጠቀሙበት በመሆኑ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊመለከተው እንደሚገባ የተናገሩት አስተባባሪው፣ በመንግሥት በኩል ምትክ ቦታ እስካሁን አለመሰጠቱን አብራርተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ባለመኖሩና ሠራተኞች ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው ለልመና ጎዳና ላይ መውጣታቸውን አቶ ዋሴ ገልጸዋል፡፡

የድርጅቱ ሠራተኞች ከሥራቸው ተፈናቅለው በልመና ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ አንዲት ስማቸውን መናገር ያልፈቀዱ እናት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከሚሰጣቸው ደመወዝ ጡረታና ግብርን ጨምሮ መንግሥት የሚጠይቃቸውን ማንኛውንም መዋጮ እንደ መንግሥት ሠራተኛ ይከፍሉ እንደነበር የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢዋ፣ ልጆች አሳዳጊዎችና ቤተሰብ አስተዳዳሪዎች የቤት ኪራይ መክፈል አቅቷቸው ችግር ላይ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

‹‹አካል ጉዳተኛ መሆናችን ሳይበግረን ሠርተን ነበር ልጆቻችንን የምናስተምረው፤›› ያሉት እኝህ እናት፣ ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ ሳይሰጣቸው ተገደው እንዲወጡ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ከተለያዩ ድርጅቶች በልገሳ ያገኟቸው ማሽኖች ተሰባብረው ከጥቅም ውጪ ሆነዋል ብለዋል፡፡