ተሟገት ስለዓለም የተነሳው ዘርፈ ብዙ ትግል ለአፍሪካ ምኗ ነው?

አንባቢ

ቀን: February 2, 2025

(የነፍስ ወይስ የአጋዥነት ትግሏ?)

በታደሰ ሻንቆ

ቀደም ብሎ እንደተነገረው የዓለማችን ችግሮችና አደጋዎች ባለ ብዙ ፈርጅ መፍትሔንና ትግግዞችን የሚሹ ናቸው፡፡ ከትንንሽ እስከ ትልልቅ አገሮች ያለው የጥቅም ግብግብ ግን ዓለም አቀፍ ዕይታ ያጣ፣ በቅርብ አዳሪ ጥቅሞች የሚዘወር፣ በጥቅሉ እንደ ሰው ልጅ ራስን በራስ በማጥፋት ትልቅ ማጥ ውስጥ የሚዳክር ነው፡፡ ይህንን ተገንዝቦ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ከማድረግ አኳያ፣ አፍሪካ የቱ ጋ ነች?

የዓለም አገሮች አካሄዳቸውን አርመውና ኃይላቸውን ለአዎንታዊ ሰላምና ለአረንጓዴ ዓለም ከወዲሁ እስካላሰማሩ ድረስ ፈጠነም ዘገየ ዓለም በሕዝብ ቁጥር መጋሸብ፣ በየብስ እጥረት (በውቅያኖስ መስፋት)፣ በንፁህ ውኃና በምግብ ዕጥረት፣ በድርቅና በጎርፍ ጥፋቶች መጠቃት፣ በአጠቃላይ በአየር ንብረትና በኑሮ መፋለስ መዳፋት አይቀርለትም፡፡ እጥረቶችና ቀውሶቻቸው ደግሞ ቦታ የማይመርጡ ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ በፊት በታየ ቀውስ በሜድትራኒያናዊ አውሮፓ የተቸገሩ አውሮፓውያን ወደ ሰሜን አፍሪካ የተሰደዱበትን ክስተት አስተውለናል፡፡ እንዲህ ያሉት ቀውሶች መባባስ፣ ዓለምን ተባብሮ ወደ እርምት ርብርብ ሊወስድ እንደሚችል ሁሉ የዓለም ጥቂት ጉልበተኞች በስስትና በዘር ትምክህት/ በጉልበት ትዕቢት ተመርተው ሰዎችን እያቃለሉና እያስለቀቁ የተፈጥሮ ሀብቶችን የመያዝ ሽምያ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉበትም ምናልባት ዝግ አደለም፡፡ ለኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሽን ክትባት በተገኘለት ጊዜ ታላላቆቹ አገሮች ማንን ሰውተው ማንን አስቀድመው ለማትረፍ እንደሮጡ አይተናል፡፡ ዛሬ ባለንበት ዓለም ፋሽስታዊ አዚም እያደገ መምጣቱም እጅግም ምርምር የሚሻ አደለም፡፡ የዘር ጥላቻ፣ ኢሰብዓዊ ጭካኔና ስስት ፖለቲካ ሆኖ በ‹ሰለጠነው› ዓለም የማያሳፍር የምርጫ መወዳደሪያ ሲሆንና መንግሥት ቤት ሲገባም እየታየ ነው፡፡ በአሜሪካ በተካሄደ የቅርብ ጊዜ የምርጫ ውድድር፣ ግትልትል ስደተኞች አደረሱ እየተባለ ይቀርብ የነበረው ቅስቀሳ ውድ የቤት እንስሶችን ቀረጠፉ እስከ ማለት የከፋ ነበር፡፡ ሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ ስደተኞች እየሞቱ የሚያልቁበት ክስተት የሚነግረን፣ ድንገተኛ አደጋን ብቻ ሳይሆን፣ የአውሮፓ ዕምቢታ ከባህሩ ጋር ሽርክና መያዙንም ጭምር ነው፡፡ የአውሮፓውያኑ ለስደተኞች በር የመዝጋት ትግል ከዶናልድ ትራምፕ አጥርና መልሶ ከማባረር አጀንዳ ጋር ተዛማጅ ነው፡፡ የዶናልድ ትራምፕ የፓናማ ቦይን ለመቆጣጣር መዛትና ካናዳና ግሪንላንድን መከጀል ክፉ ቀን ቢመጣ ምን ሊከተለን እንደሚችልም ይጠቁማል፡፡ አንዳንዶች ዶናልድ ትራምፕን እጅግ አደገኛ የቀኝ ፖለቲከኛ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ለዚህ የተሳሳተ ግንዛቤ መነሻቸው የዶናልድ ትራምፕ ፍላጎቱን ሳያድበሰብስ በግልፅ የሚናገር መሆኑ ነው፡፡ የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት አጋዥ ከመሆን ፋንታ አስቆማለሁ የሚለው ዶናልድ ትራምፕ፣ ጦርነቱን ሲያፋፍሙ ከቆዩት አውሮፓ ኅብረትና ጆ ባይደን በጥፋት አራማጅነት እንደምን በልጦ? በትራምፕ አቋምና ጦርነቱን ሲያፋፍሙ በቆዩት ኃይሎች አቋም መሀል ያለው ልዩነት የሚያስተምረን በፖለቲካ ቆዳ ላይ ያለ ልዩነትን አልፈን በዓለማችን ላይ እያደገ የመጣ የጨቡዴነትንና የጥፋት ዝንባሌን ማስተዋል እንዳለብን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሆነን ወደፊት ሊመጣ የሚችል አደጋ እኛን አፍሪካውያን በቶሎ ሊያባንነን ይገባል፡፡ ለምን?

ከላይ የጠቃቀስናቸው ድክመቶችና ጥያቄዎች ክፉ ቀን ቢመጣ አፍሪካ ሊወረሩ ከሚችሉ አኅጉሮች አንዷ፣ ምናልባትም ቀዳሚዋ፣ ልትሆን እንደምትችል ይጠቁማሉ፡፡ ከሁሉ ግርም የሚለው ታዲያ፣ ከዚህ አደጋ ለማምለጥ ተባብሮ በመሮጥ ፈንታ፣ ለሩቅና ለቅርብ ጌታ አገሮች ጣቢያ እየሰጡ፣ ከጎረቤቶቿ ጋር ለተሳሰረ ልማትና ዕድገት በተግባር እየሠራች ያለችውን፣ ከዕርዳታ ጥገኝነት በመላቀቅ ትግልና በፈጣን ግስጋሴ አርዓያ የሆነችውንና የልማት አቅሟን ለአፍሪካውያን ለማጋራት የማትሰስተውን ኢትዮጵያን ባህር በር-የለሽ አድርጎ ለማቆየት እንቅልፍ እስኪያጡ የሚሠሩ አፍሪካዊ አገሮችና ልሂቃን መኖራቸው ነው፡፡ አንዲህ ያለው ድርጊት የአፍሪካን መሰናዶ የመተናነቅ ጥፋት አንድ መገለጫ ነው፡፡ እንዲህ ያለው መመቀኛኘት መኖሩና ካደጋ የማምለጥ የተባበረ አኅጉራዊ ጥድፊያ መጉደሉ ተደምሮ ሲታይ፣ አፍሪካችን እንቅልፍ ላይ ነች ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ከእንቅልፍ መንቃት ግን ‹‹ኃያላንን ማመን ቀብሮ ነው! ኃያላንን ማስጠጋት አደጋ ነው! የጦር ጣቢያቸውን ማስነሳት አለብን!…›› የሚሉ ጫጫታ ውስጥ መግባት አደለም፡፡ እንዲህ ያለ ጅልነት ከበፊቱ ይበልጥ እያመሳችሁ የግጭት የሽብር የብጥብጥና የወታደራዊ ፍንቀላ መጫወቻ አድርጉን የሚል ማመልከቻ ማቅረብ ነው፡፡ በጥያቄ መልክ የተጠቃቀሱትን ምናልባታዊ ዕርምጃዎችን እየደጋገሙ ማባዘትም እንዲፈፅሟቸው ከማስታወስ ያነሰ አደለም፡፡ ከእንቅልፍ ባንኖ ከአደጋ የማምለጥ ሩጫ፣ አይመጣምን ትቶ ይመጣልን በያዘ ልባምነት የ2063ን የአፍሪካ ግብ ከታቀደለት ጊዜ ቀደም አድርጎ ለማቅረብ መትጋት ነው፡፡ የ2063 የአፍሪካ መድረሻ ግብ (በአካባቢዎችና በአኅጉር ደረጃ የተሳሰረች፣ ሥነ ምኅዳርን በሚንከባከብ ሁለገብ ዘመናዊ ኢኮኖሚ የተሸጋገረች/ በረሃብ በጦርነት መጎሳቆልና መሰደድን ታሪክ ያደረገች ሰላማዊ አፍሪካ) ግዙፍና ግሩም ዕቅድ ነው፡፡ ጉዳዩ ግን የመንግሥታት መሪዎች ውሳኔ የመሆን ነገር አደለም፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ተሰብስበው የውሳኔውን የጊዜ ቁመት መቀነስ አለመቀነሳቸውን የሚመለከትም አደደለም፡፡ ጉዳዩ ዓለም ዛሬ ያለበትን እውነታዊ አዝማሚያ ተረድቶ በጠባብና በቅርብ አጀንዳዎች ለየብቻ ከመታጠር በመውጣት፣ የተናጠል አጀንዳን ከአኅጉራዊው አጀንዳ ጋር አዋድዶ በትግግዝ መሮጥን የሚመለከት ነው፡፡

የዚህም ሩጫ ይዘት ድኅነትን ረሃብን ትርምስን ግጭትን ጦርነትንና ያካባቢ ብክለትን አንድ ላይ እምቢኝ የሚል ከመሆን ያነሰ አደለም፡፡ እምቢታው ፉከራ አደለም፡፡ ጥፋቶችን የመከላከል፣ የማስቆም፣ የማምከንና ልማቶችን የሁሉ የማድረግ አቅም መፍጠር ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ አጀንዳ 2063 ሕይወት የሚያገኘው፣ የአፍሪካ መንግሥታት ሊቃውንትን ልሂቃንን ፓርቲዎችን ባለሀብቶችንና አገሮችን አንድ ላይ አያይዞ የሚያንቀሳቅስ የፖለቲካና የልማት ሕዝባዊ ተግባር ሲሆን ነው፡፡ በአኅጉር በቀጣናና በአገሮች ደረጃ፣ እዚህ ሒደት ውስጥ ከሆንን፣ የውጭም የውስጥም ጠብ ጫሪዎችን የመገሰፅና የማሳፈር አቅም ይኖረናል፡፡ ግጭቶችን የማስቆምና የጦርነት አደጋዎችን የማስቀረት አቅም ይኖረናል፡፡

አሁን ባለንበት ዕውነታ ግን፣ የ2063 አጀንዳ አኅጉራዊም አገራዊም የፖለቲካና የልማት እቅስቃሴ ገና አልሆነም ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ የድርቅ የረሃብና የተስቦ ወጥመዶች፣ የብድርና የዕርዳታ ጥገኝነት ወጥመዶች፣ የትርምስ የሽብር የግጭት የጦርነትና የመፈናቀል ወጥመዶች እዚህና እዚያ አፍሪካውያንን እያጠመዱ ዛሬም ያዳክራሉ፡፡ በድንበር ዘለልና በጎረቤት ጣልቃ ገብነት ሰላማቸውን እያጡ የማዕድን ዘረፋዎች የሚካሄድባቸው አገሮች በአፍሪካችን ውስጥ አሉ፡፡ የሱዳንን፣ የደቡብ ሱዳንን፣ የኤርትራን የሶማሊያንና የኢትዮጵያን ጉርብትናና የውስጥ ሰላም ለማመስ ከሰሜን አፍሪካ ተነስቶ እንደ ፌንጣ ወዲህና ወዲያ እየዘለለ ደባና ጠብ የሚያደራ አገረ-መንግሥት እየረበሸ ያለው አፍሪካ ቀንድን ብቻ አደለም፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና የዕድገት እድል መተጓጎል፣ የአፍሪካ አኅጉር ሰላምና ልማት መተጓጎልም ነው፡፡

በጦርነት የተጎሳቆለ አገርን ተራፊ ወታደራዊ አውታር ማደባየት ሉዓላዊነትን ማደባየት ነው፡፡ በግርግር መሬት ማስፋት ሉዓላዊነትን መጣስ ነው፡፡ የውጭና የውስጥ ኃይሎች በተቀናበሩበት የውስጥ ጦርነት ጭርንቁሷ በወጣ ድንበርተኛ አገር ውስጥ የራስ ገዝ መፍትሔ ከተተከለ ጣጣው ወደ እኔ አገርም ሊመጣ ይችላልና በሚል ስሌት በተጎራባች አገር ውስጥ የሚኖርን የፖለቲካ አፈታት በጉልበት መቆጣጠር ሉዓላዊነትን መንሳት ነው፡፡ አንድ አገር ከጎረቤቱ ጋር የፀብ/ የንቁሪያ አጀንዳ ካለው አገር ጦር አበራክቶ አስገብቶ አካባቢውን ለውክልና ጦርነት አደጋ ቢያጋልጥ በሉዓላዊ መብቱ መጠቀሙ ነው? ያስገቢውን አገር ሉዓላዊነት ጨምሮ የጎረቤቶቹን ሁሉ ሉዓላዊነትና ሰላም የሚረግጥ ተግባር ዝም ሊባል ይገባል? ይህንን መሰል የትርምስ አደጋ በአፍሪካ የተወሰነ ቀጣና ውስጥ ሽል ለመሥራት ቢሞክር የአፍሪካ ኅብረት እንዴት ያስተናግደዋል? ይቦዝንበታል ወይስ አኅጉራዊ ጣጣዬ ብሎ ‹‹ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ›› በሚባለው ብሂል መፍትሔ ይፈልግለታል? ከአፍሪካ ኅብረት ድርጅት ዘወር ብለን ወደ ምሁራንና ፖለቲከኞች እንምጣ፡፡ የጠቃቀስናቸውን ጣጣዎችና መሰሎቻቸውን ከ2063 ትልም አኳያ እየመዘነ ለመቃወምና ለማቃለል የሚነቃነቅ የምሁርና የፖለቲካ ድምፅ አፍሪካ ውስጥ አለን? ወይስ ባያሌው እያየን ያለነው የ2063ን ግብ ውሉ ካደረገ ልሂቅና ፖለቲካኛ ይልቅ በአጫጭር ዕይታዎች የተበጫጨቀና የጠብ ፊናዎችን የሚያጋፍር ልሂቃዊ እንቅስቃሴ ነው?

አፍሪካችን በ2063 አጃንዳ ላይ አትኩረው በሰላምና በልማት ግስጋሴ ላይ የሚሠሩ ምን ያህል አገረ-መንግሥታትን አበራክታለች? ለዚህም ጥያቄ አፍሪካ ያላት መልስ የሚያሳቅቅ ነው፡፡ መነቃቂያና አርዓያ የሚሆኑ ውስን አገሮች ቢኖሩም በተለመደው የጉስቁልና አዙሪት ውስጥ የሚማሰኑ አገሮች ብዙ አሉ፡፡ ከቀድሞ ቅኝ ገዢው ጉያ ውስጥ ሆኖ የሚፍተለተል አገር፣ ወኔ አግኝተው የቀድሞ ቅኝ ገዢያቸውን ‹የጦር ጣቢያህን ነቅለህ ውጣልኝ› ለማለትና ለማሰናበት የደፈሩ መረጋጋትና ልማት ግን ገና ያልተዋደደላቸው አገሮች፣ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ የህሊና ቅኝ ተገዢ ሆኖ ‹‹የነፃ አውጪነትን›› ወግ ያከናወነና ዛሬም ከነህሊናዊ ቅኝ ተገዢነቱ የአገር ‹‹መሪነት›› ላይ የተዘፈዘፈ ገዢ፣ እነዚህ ሁሉ አሉባት አፍሪካ፡፡ ያገር ‹‹መሪ›› ሆኖ አገሩን ከልማት ግስጋሴ የሰነከለ፣ ከመሰንከልም በላይ፣ ሕዝቡን ለአገር የለሽነትና ለስደት ዳርጎ፣ አገሩን ያንድ ራሱ ነፍስ ማቆያና መቀበሪያ አድርጎ የያዘ፣ ለጠብ ጫሪዎች ሎሌነት እያደረ ያካባቢውን ሰላም በማስጠቃት ገቢ የሚያገኝ … ይህን መሳይ ገዢነት ሁሉ አለባት አፍሪካ፡፡

ይህ ዓይነቱ ገመና ‹በእንቶኔ ክፍለ አኅጉር ውስጥ እንቶኔ በሚባል አገር ውስጥ…› እያልን ጣት የምንጠቋቆምበት ሳይሆን አፍሪካችንን በጥቅሉ በኃፍረት የሚሸነቁጥ ገመና ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ውል ያጣ ውጥንቅጥ ምክንያት ደግሞ ከአፍሪካ ልሂቃን ወደ ኋላ መቅረትና አፍሪካዊ ዕይታን ለማስፋፋት ካለመቻል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ አፍሪካ የ2063 አጀንዳዋን የሚያራምድ ልሂቃዊ ኃይል በአግባቡ ገና አልሰነቀችም፣ አላሰማራችም፡፡

የዛሬው ዓለም፣ ፈጠራን/ፍልሰፋን የምርትና ያገልግሎት ሥራዎችን ሁሉ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መምራትንና ማንቀሳቀስን/ማስተናበርን የሚጠይቅ ሆኗል፡፡ ቴክኖሎጂ ነክ ምርምሮች ፈጠራዎችና ማሻሻያዎች ደግሞ በማያቋርጥ ሩጫ ውስጥ ናቸው፡፡ ከቴክኖሎጂዎች አቢዮት ጋር የቀደመ ትውውቅና ሥርጭት ባለባቸው ያደጉ  አገሮች ሳይቀር፣ የቴክኖሎጂዎች የመሻሻል ፍጥነት ከቴክኖሎጂ ጋር ያደገውን ነባር ትውልድ ጥሎ እያለፈ የሚሄድና ከነባሩ ትውልድ ይልቅ ወጣቱን የሚመርጥ እየሆነ ነው፡፡

ነባሩ (አዛውንቱ) ትውልድ ለፈጣን የቴክኖሎጂ ግስጋሴ ባይተዋር ሆኖ ግራ የመጋባት ክፍተት ውስጥ እንዳይወድቅ የረዳውም ራሱ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ብዙ ሥራዎችን ከሰዎች ላይ ቀንሶና አዝሎ ሊሠራ የሚችለው ‹‹ሰው ሠራሽ አስተውሎት››፣ ‹‹የሰው ሠራሽ አስተውሎት›› መሠረተ ትምሕርትን ከእያንዳንዱ ልሂቅ የሚጠይቅ ሆኗል፡፡ መሠረተ ትምህርቱን በአንድ ወቅት መማርም ለሁልጊዜ ስንቅ አይሆንም፡፡ ‹‹የሰው ሠራሽ አስተውሎት›› ቴክኖሎጂ በየሥራ ዘርፎቹ የራሱን የተወሳሰበ ዕድገት ያሳያልና መሠረተ ትምሕርቱና ልምምዱ ማለቂያ የለውም፡፡

ለ21ኛ ክፍለ ዘመን ቴክኖሎጂዎች እንግዳና ጀማሪ የሆኑ ታዳጊ አገሮች ደግሞ፣ የቴክኖሎጂዎቹ ግስጋሴ በእነሱ እጅ ውስጥ ስላልሆነ (ባያሌው ተቀባይ ናቸውና) አዲስ ብለው ያስገቡትን/የቀሰሙትን በአገራቸው ከማስረፃቸው በፊት፣ እንዲያውም እያስተማሩት ሳሉ አዲስ ፈጠራ መጥቶ የተያያዙትን ቴክኖሎጂ አሮጌ ያደርግባቸዋል፡፡ የተለያየ ዓይነት መተግበሪያዎችን የመቀመር ሙያዊ አቅም እየፈጠርንና አዲስ ዘመን ውስጥ እየገባን ነው ብለው ሲያስቡ የተናጠል ብዙ ሥራዎችን ‹‹በሰው ሠራሽ አስተውሎት›› አካትቶ ትዕዛዝ እየሰጡ መሥራትን የሚያስችል ቴክኖሎጂ ከተፍ ይልባቸዋል፡፡ እናም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገሮች ሩጫቸውን ካላፈጠኑ የቴክኖሎጂዎች የግስጋሴ ፍጥነት በዕድሜ የገፉ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን አገሮችንም ጥሎ የሚሄድ ነው፡፡ የጥሎ ማለፉ ስፋት የ21ኛ ክፍለ ዘመንና የድንጋይ ዘመን ውስጥ የመገኘት ያህል ክፍተት ሊፈጥርም ይችላል፡፡ እናም የ2063 ግብ ተጨባጭነት በአዝግሞት የሚሆን ነገር አይደለም፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡