እኔ የምለዉ የኢትዮጵያ ልሂቃን የፖለቲካ ባህል

አንባቢ

ቀን: February 2, 2025

ከዕልቂትና ከውድመት አዙሪት እንዴት እንውጣ?

በሰለሞን ኃይለ ማርያም (ዶ/ር)

መግቢያ

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል በኢትዮጵያ አጠቃላይ ዕድገት ላይ ምን ያህል በጎ ያልሆነ ተፅዕኖ እንዳሳደረና ይህም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማኅበራዊ፣ እንዲሁም የሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ እየተሻሻለ ከመምጣት ይልቅ እየደቀቀ እየማቀቀና እየኮሰሰ እንዲሄድ ማድረጉን በማመላከት የፖለቲካ ባህላችንን ለማረቅ፣ ለማስተካከል፣ ብሎም ለመቀየር ምን ማድረግ እንደምንችል ለመወያየት ነው፡፡ በተጨማሪም የፖለቲካ ባህል ለሰላም ወይም ለግጭት ዋና መንስዔ በመሆኑ፣ የፖለቲካ ባህላችንን ማረቅና ማስተካከል ጊዜ የሚሰጠው አይደለም፡፡ ላለፉት አሥር ዓመታት በተለይም ደግሞ ከለውጡ በኋላ በኢትዮጵያ ልሂቃን መካከል ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውስ ከዋና ዋናዎች ምክንያቶች መካከል የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል  አንዱ እየተደረገ ሲነሳ ይስተዋላል፡፡ ለመሆኑ የፖለቲካ ባህል ምንድነው? የፖለቲካ ባህልን መቀየር ይቻላል? ከተቻለስ በምን ፍጥነት? ሌሎች የዓለም አገሮች የተሳሳተ ያሉትን የፖለቲካ ባህል እንዴት ነው የቀየሩት? በመቀየራቸውስ ምን አገኙ? በማለት የመወያያ ሐሳብ ለማቅረብ ነው፡፡

የፖለቲካ ባህል ምንድነው?

የፖለቲካ ባህል በፖለቲካ ሳይንስ ውስጥ የቆየ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ጥንታዊ ፈላስፎች  እነ ሞንተስኬ፣ ፕሌቶ፣ ሶቅራጦስ፣ አርስቶትልና ሌሎችም ስለፖለቲካ ባህል የራሳቸውን ሐሳብ አስቀምጠዋል፡፡ ይሁንና  የፖለቲካ ባህልን  በፖለቲካ ሳይንስ ውስጥ በስፋት ጥናትና  ምርምር ማድረግ  የተጀመረው  እ.ኤ.አ. በ1963 አሜሪካዊ የፖለቲካ  ሳይንስ ሊቃውንት አልመንድና ቬርባ በእንግሊዝ፣ በአሜሪካ፣ በጣሊያን፣ በምዕራብ ጀርመንና በሜክሲኮ የፖለቲካ ባህል ላይ ጥናት በማድረግ በተለይም ዴሞክራሲ ላይ በማተኮር  ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ካሳተሙ በኋላ ነው፡፡

የፖለቲካ ባህል ማኅበረሰቡ በአገሪቱ ስላለው  የፖለቲካ  ሥርዓት  የሚጋራው አስተሳሰብና ምልከታ ጠቅላላ ዕይታ ነው፡፡ የፖለቲካ ባህል አንድ ማኅበረሰብ  የፖለቲካ ሥርዓቱ እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው በማለት የሚሰጠው ብያኔ ነው፡፡ ለምሳሌ  ሉሲያን  ፓይ የተባለው የአሜሪካ ፖለቲካ ባህል ተመራማሪ የፖለቲካ ባህል የአንድ ማኅበረሰብ  መሠረታዊ እምነት፣ ስሜትና ልማድ፣ እንዲሁም ዕውቀት የተጣመረበት በአንድ አገር ያለው የፖለቲካ ሒደት መደላድል ነው በማለት የፖለቲካ ባህልን ይተረጉማል፡፡ በተጨማሪም የፖለቲካ ባህል ዜጎች በአገራቸው ስላለው የፖለቲካ ሥርዓት ያላቸው እምነት፣ ልማድ፣ አስተሳሰብና ስሜት ነው በማለት ያጠቃልላል፡፡

የፖለቲካ ባህል በሁለት አልፎ አልፎም በሦስት ይከፈላል፡፡ የአጠቃላይ የማኅበረሰቡ የፖለቲካ ባህል፣ የልሂቃን የፖለቲካ ባህል፣ እንዲሁም የተቋማት የፖለቲካ ባህል በማለት መክፈል ይቻላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የሚነሱ ጉዳዮች በአጠቃላይ ወይም በአብዛኛው የልሂቃን የፖለቲካ ባህል ናቸው፡፡ ይህንን በአጽንኦት አንባብቢያን ልብ እንዲሉልኝ እሻለሁ፡፡ በልሂቃን የፖለቲካ ባህልና በአጠቃላይ የሕዝቡ የፖለቲካ ባህል መካከል የሰፋ ልዩነት እንዳለ መገንዘብ ያሻል፡፡

የፖለቲካ ባህልም ሆነ በአጠቃላይ ባህል የምንለው በጊዜ ሒደት የተሠራና እየዳበረ የሚሄድ ነው፡፡ ባህል ስንፈጠር አብሮን የተወለደ አይደለም፡፡ በታሪክ በፖለቲካ ክስተቶች፣ በአገሪቱ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እውነቶችና ሁነቶች ላይ ተመሥርቶ የፖለቲካ ባህል ይሠራል፡፡ ማንኛውም ባህል ሰው ሠራሽ ነው፡፡ ተፈጥሯዊ የሚባል ባህል የለም፡፡ በእርግጥ የፖለቲካ ባህልን ለመፍጠር፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ  ለማስረፅና የፖለቲካ ባህል ሆኖ እንዲወጣ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን  አዲስ የፖለቲካ ባህል መፍጠር  የማይቻል አይደለም፡፡  በቻይና፣ በህንድ አዲስ የፖለቲካ ባህል መፍጠር  እንደሚቻል ታይቷል፡፡ በአሜሪካና በካናዳም በተመረጡ ጉዳዮች የተፈጠሩ የፖለቲካ ባህሎች አሉ፡፡ በጥልቀት  ሲታይ  በኒውዚላንድ፣ በአውስትሪሊያ፣ በጃፓን፣ በአሜሪካና  በካናዳ አዳዲስ የፖለቲካ ባህሎች ተፈጥረዋል፡፡ ሲንጋፖር የዕድገት ማማ ላይ የወጣችው በአዲስ  የፖለቲካ ባህል ነው፡፡

በአገራችንም ቢሆን ነጋድራስ  ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ‹‹መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር››  በሚለው  መጽሐፋቸው ቀጣይነት ያለው የመንግሥት አስተዳደር መጥፋት  ለኢትዮጵያ  ኋላቀርነት መንስዔ ነው የሚል ሐሳብ ሲያንፀባርቁ፣ ስለፖለቲካ ባህላችን መናገራቸው ነበር፡፡ የቀደሙ ምሁራኖቻችንና አስተዋይ ኢትዮጵያውያን  ለኢትዮጵያ  መጎሳቆል የማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት፣ መቆሚያ  ላጣው ግጭትና  ዕልቂት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል መሆኑን በገደምዳሜው ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ የኢትዮጵያ  የፖለቲካ ባህል ለአገራችን ሕዝቦች ነቀርሳ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን  ይህ ነቀርሳ  የማይነቀል፣ የማይታወቅና ፈጽሞ የማይቻል አይደለም፡፡ ችግሩ ከታወቀ መፍትሔው የማይቻል አይደለምና፡፡

በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ ድረ ገጽ ላይ ‹‹Amhara, Oromo, and Tigray Political Cultures and Challenges of Political Stability in Ethiopia: 1991–2017›› በሚል ርዕስ በዚህ ዓመት በታተመው የጥናት ጽሑፍ መሠረት የኢትዮጵያ ልሂቃን የፖለቲካ ባህል ተብለው ከሚለዩት መካከል ባለፈ ታሪክ  አለመግባባት፣ እርስ በርስ መወነጃጀል፣ ኃላፊነት አለመወሰድ፣ ሁሉንም ችግር የሌላው አድርጎ ማቅረብ፣    የመንግሥት ሥልጣን ለማግኘት ሕግን መጣስ፣ የመንግሥት ሀብት ዝርፊያ፣ የአስተዳደር  በደል፣  የተሳሳተ  ፖሊሲ  ላይ ድርቅ  ማለት፣ ከፋፍለህ ግዛ የፖለቲካ  መሣሪያን መጠቀም፣ ገዥ ልሂቃን የመንግሥትና የሕዝብ ሀብትን እንደ ግል ንብረት መጠቀም፣ ስም ማጥፋት፣ የፖለቲካ ሥልጣን ተቀናቃኝን እንደ ጠላት ማጥቃት፣ የመደራደርና የሰጥቶ መቀበል  ባህል አለመኖር፣ የፖለቲካ ሥልጣን ለማግኘት ወይም  በፖለቲካ  ሥልጣን  ለመቆየት የኃይል አማራጭን መጠቀም፣  በፖለቲካ  ጉይዳ የእርስ  በርስ  ጦርነት ቢነሳ፣ አንዱ ጎሳ በሌላው ላይ ቢነሳ ያበጠው ይፈንዳ ማለት፣ ሥልጣን  ለመያዝ  አንዱን ዘውጌ በሌላው ዘውጌ ላይ ማነሳሳት፣ አንዱን ሃይማኖት በሌላው ላይ ማስነሳት፣  ‹‹ዜሮ ሰም ጌም›› ወይም ሁሉንም ለብቻዬ በማለት ሌላውን  ማግለል፣ የእኔ ለእኔ የእናንተ ለእኛ በሚል የፖለቲካ ቀመር መንቀሳቀስ ናቸው፡፡  በዚህ ጽሑፍ የምናየው ስም ማጥፋትን፣ ተቀናቃኝን ማጥቃትንና የመደራደርና የሰጥቶ መቀበል  ባህል አለመኖርን  ይሆናል፡፡

ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም የሕይወት ታሪካቸውን ባሰፈሩበት ‹‹አቶ ባዮግራፊ›› መጽሐፍ፣ በቅርቡ ታደለች ኃይለ ሚካኤል ‹‹ዳኛው ማነው?››፣ ዶ/ር መላኩ ተገኝ ‹‹ከሰንጋ ተራ እስከ አምስተርዳም››፣  አማረ ተግባሩ (ዶ/ር) ‹‹ኃይሌ ፊዳና የግሌ ትዝታ››፣ ቡልቻ ደመቅሳ ‹‹My Life My Vision for the Oromo and Other Peoples of Ethiopia›› በሚለው የእንግሊዝኛ መጽሐፋቸው፣ ሕይወት  ተፈራ ‹‹ማማ በሰማይ›› እና ሌሎችም ብዙ መጻሕፍት አስከፊ የፖለቲካ  ባህላችን ዋጋ እንዳስከፈለንና መቀየር እንዳለበት በቀጥታ ባይሆን በተዘዋዋሪ አስገንዝበዋል፡፡ በሕይወት  ተፈራ መጽሐፍ ላይ የደራሲዋ ዋና ጀግና  የሆነው ጌታቸው ማሩ ከፓርቲው  የተለየ ሐሳብ  በመያዙ ብቻ መገደሉ፣ ኃይሌ ፊዳ የገበሬ ልጅ ሆኖ ሳለ የፊውዳል ልጅ ነው እየተባለ ከፍተኛ የስም ማጥፋት እንደደረሰበት አማረ (ዶ/ር) ያብራራሉ፡፡ እንዲህ  ያሉ ፖለቲካዊ  ግድያዎችና ስም ማጥፋቶች በኢትዮጵያ ታሪክ ተዘርዝረው አያልቁም፡፡ ይህንን  ለአገራችን የዕድገት መሰናክል የሆነ የፖለቲካ ባህላችንን  ነቅለን ካላስወገድነው እንዴት ከረሃብ፣ ከልመና፣ ከድህነትና ከኋላቀርነት ልንገላገል እንችላለን? ብሩህ፣ ብርቱና በሳል የፖለቲካ መሪዎችን ስም እያጠፋን፣ እየገደልንና በአጭሩ እየቀጨን ምን ዓይነት የፖለቲካ መሪ ልንፈጥር ነው? ከላይ አንደተገለጸው የፖለቲካ  ባህል ሰፊና ውስብስብ ነው፡፡ ወደ ሰፊውና ውስብስቡ ገብቼ ቀልጬ ሳልቀር  ወደ ተነሳሁበት አንድ ፍሬ ወደ ሆነው ለዛሬ ወደ የማቀርበው የፖለቲካ ባህላችን ላይ ላተኩር፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ሥር የሰደደና የቆየ ቢሆንም፣ ከቅርቡ ተነስተን ወደፊትም ወደኋላም እያልን እናያለን፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ስንልም እጅግ ሰፊና ፈርጀ ብዙ በመሆኑ የየትኛው ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ባህል የሚል ጥያቄም የሚያስነሳ በመሆኑ፣ በማዕከላዊ መንግሥት የፖለቲካ ባህል እሱም ቢሆን የልሂቃን የፖለቲካ ባህል ላይ አተኩረን አንኳር አንኳሩን ለማየት አንሞክራለን፡፡ ከእነዚህ አንኳር ጉዳዮችም መካከል ሥልጣን ይዞ ለመቆየትና ወደ ሥልጣን ለመምጣት በሚደረገው ትግል ላይ እንዴት መቻቻል የጎደለው አርቆ አስተዋይነት የሌለበት ስለአገሪቱ፣ ስለሕዝቡ ሰላም፣ የዕለት ተዕለት ኑሮና ዕድገት ላይ ደንታ የለሽ ትንቅንቅ እንደሚደረግ፣ ይህም ያስከተለው ጥፋት ዕልቂትና መከራን ለማየት፣ ለመዳሰስና ለማወያየት እሞክራለሁ፡፡

ስም የማጥፋትና የማጥቃት የልሂቃን የፖለቲካ ባህል

 በኢትዮጵያ የልሂቃን የፖለቲካ ባህል ወደ ፖለቲካ ሥልጣን ለመምጣት ወይም ደግሞ ሥልጣንን ይዞ ለመቆየት እንደ መሣሪያ ከሚጠቀሙባቸው ብዙ ነገሮች መካከል የፖለቲካ  ባላንጣን፣ የፖለቲካ ተቀናቃኝን ስም ማጥፋት አንዱ ነው፡፡ አንደኛውን ከሰው ፍጡር አሳንሶ ማሳየት፣ አውሬ ማድረግ፣ ማጥላላትና ይውደም ‹‹ቀይ ሽብር ይፋፋምበት››፣ ‹‹ፀረ›› እንደዚህ ነው ማለት፣ ‹‹ውጉዝ ከመአሪዎስ›› ማለትና እሱ እንደዚህ ነው፣ አሸባሪ፣ ወዘተ በማለትና አሉታዊ ፍረጃ በመስጠት ከጨዋታው ውጪ እንዲሆን ማድረግ ይባስ ብሎም መግደል፣ ማስወገድ፣ እንዳይሞት እንዳይሽር ማድረግ የተለመዱ ናቸው፡፡ ታዲያ ይህንን የልሂቃን የፖለቲካ ባህል በሕግ ለመከላከል አለመቻል፣ ሕግ ወይም የፍትሕ ተቋማት ነፃ፣ ገለልተኛና በከፍተኛ የሞራል ልዕልና መመራት አለመቻላቸው ትልቁ ስብራት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ልሂቃን ወደ ፖለቲካ ለመምጣት ወይም በፖለቲካ ሥልጣን ለመቆየት የማያደርጉት ነገር የለም፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግር በእርግጥ ተደርጎ አያውቅም በማለት የሚከራከሩ ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ሕጋዊነት ራሱን ችሎ ሌላ ውይይት የሚያስፈልገው በመሆኑ አሁን ወደተነሳሁበት ስም ማጥፋት ልመለስ፡፡ ልጅ እያሱ ሕጋዊ  የምኒልክ ወራሽ ሆነው ሳለ ልጅነታቸው፣ ምክር አልሰማ ማለታቸው፣ ለፖለቲካ ባላንጣዎቻቸው አጋልጦ ሰጥቷቸው ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የሚሆን  የማይሆን ስም በመስጠት ከሥልጣናቸው እንዲሰናበቱ፣ ይህም አልበቃ ብሏቸው ጨርሰው  እንዲጠፋ  አድርገዋቸዋል፡፡ የእሳቸው ከሥልጣን መነሳት ብቻ ሳይሆን በዚህ ሳቢያ ጦርነት ተደርጎ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡ የአገር ንብረት ወድሟል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በኃይል ሥልጣንን መንጠቅ ወደ ሥልጣን መፈናጠጥ እንደሚቻል፣ ቀጣይ በሆነ ሁኔታ ሥር እንዲሰድ ሌላ የፖለቲካ ባህል ችካል ሆኗል፡፡ ይህ የቅርብ ታሪካችን  የሕጋዊ መሪን ቦታ ለመውሰድ የፖለቲካ ተቃናቃኞች ስም በማጥፋት፣ በማጠልሸትና በማንቋሸሽ  የፖለቲካ ድጋፍ በማሰባሰብ  ሥልጣንን በአቋራጭ የማግኘት  የፖለቲካ ባህል እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደተቻለ  አመላካች ነው፡፡ በተጨማሪም ይህንን ሕጋዊ ያልሆነ አካሄድ የሚከላከል፣ በሥርዓት የሚዳኝ የሚጠብቅ ይህ ነው የሚባል ነፃ፣ ገለልተኛ፣ የተጠናከረና ዘላቂ የሆነ መንግሥታዊም ሆነ ማኅበረሰባዊ ተቋም  በኢትዮጵያ የሌለ በመሆኑ፣ ይህ የግጭት አዙሪት የሆነ  የልሂቃን  የፖለቲካ  ባህል ያለ ከልካይ እንዲቀጥል ዕድሉ ተከፍቶለት ቆይቷል፡፡  ወደ ፖለቲካ ሥልጣን ለመምጣት ወይም የፖለቲካ ሥልጣን ይዞ ለመቆየት በሚደረገው ትግል ላይ የሚደረግ ስም ማጥፋት በአብዛኛው በሐሰትና በውሸት ላይ ተመርኩዞ ነው፡፡

ተፈሪ [ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ] ወደ ሥልጣን መንበር ለመምጣት እየተደላደሉ ባሉበት ወቅት  አሁንም ቦታው ይገባኛል በማለት ክርክሩ ቀጥሎ ነበር፡፡ ልጅ እያሱ ተሽረው ወይዘሮ ዘውዲቱ ንግሥተ ነገሥታት ሲባሉ ባለቤታቸውም ጉግሳ ወሌ ወደ ንግሥናው ይጠጋሉ የሚል ግምት ነበር፡፡ ይሁንና ጉግሳ አዲስ አበባ ሲመጡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል እንደገና በይፋ ተከሰተ፡፡ ንግሥቲቱ ያላሉትን፣ ‹‹እግዚአብሔር እኔን  ሴቲቱ መርጦ ለዚህ ክብርና ዙፋን ካበቃኝ ለብቻዬ እንጂ  ከባል ጋር መኖር የለብኝም፤›› ብለዋል ተብሎ  ንግሥቲቱ ከራስ ጉግሳ እንዲለያዩ ተሴረ፡፡ ራስ ጉግሳም ወደ አባታቸው አገርና ግዛታቸው ወደ ጎንደር  ከመመለስ ይልቅ ወደ አማራ ሳይንት በሹመት ተላኩ፡፡ የሸዋ መኳንንት ሸር ያስቀየማቸው ራስ ጉግሳ ለበቀል መነሳሳታቸው የጊዜ ጉዳይ ነበር፡፡ ተፈሪ ወደ ሥልጣን መንበር ለመምጣት እየተደላደሉ ባሉበት ወቅት ራስ ጉግሳ ወደ አመፅ ገቡ፡፡  በኢትዮጵያ ያሉ የጣሊያን ወኪሎች፣ በኋላ ሸርተት  ቢሉም የትግራይ  መሣፍንቶች፣  የጎጃሙ  ራስ ኃይሉ ጭምር የአመፁ ተባባሪ ለመሆን ተዘጋጅተው  ነበር፡፡  እዚህ ላይ ቆም ብለን  እንድናስብ የሚያስፈልገው ሁልጊዜ ሕግና ሥርዓት ሲጣስ፣ አመፅ ሲነሳ  የውጭ ጠላቶቻችን  ለአመፁ ገንዘብና መሣሪያ ለማቀበል ዝግጁ መሆናቸውንና የአገራችን የፖለቲካ ባላንጣዎችም ስለአገሪቱ፣ ስለሕዝቡ፣ ስለውጭ ጠላቶቻችን  የተደበቀ ሴራ ደንታ ሳይኖራቸው መተባበራቸው፣ መሣሪያውንም ገንዘቡንም መቀበላቸው ነው፡፡

የሆኖ ሆኖ ራስ ጉግሳ ወሌ (አባ ደልድል) ልክ ተፈሪና የተፈሪ ደጋፊዎች በእያሱ ላይ  እንዳደረጉት ሁሉ፣ በተፈሪ ላይ ከማመፃቸው በፊት የስም ማጥፋት ዘመቻ ጀመሩ፡፡ ‹‹ራስ ተፈሪ የካቶሊክን ሃይማኖት  በፈረንሣይ አገር ተቀብሏል፡፡ በዚህ የተነሳ የጥንቱ የጠዋት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ለማፍረስ እየሠራ ነው፡፡ ራስ ተፈሪ አህያና ውሻ እያሳረደ ግብር ያበላል፡፡ እንዲያውም አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ አህያና ውሻ እያረደ እንዲበላ አዋጅ እየተዘጋጀ ነው፤›› በሚል የስም ማጥፋታቸውን አጧጧፉት፡፡ ራስ ጉግሳ ወሎ የወጠኑት አመፃ በወሎ ደላንታ አንቺም በሚባል ሥፍራ በተፈሪ የታዘዙትን  ራስ ሙሌጌታን መቋቋም ባለመቻላቸው ተሸነፉ፡፡  ይህንን ታሪክ  እዚህ ላይ ማንሳቴ ስም ማጥፋት የፖለቲካ ባህላችን መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ  ለማወቅ  አምባሳደር ዘውዴ ‹‹ተፈሪ መኮንን ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ››  በሚል ያሳተሙትን መጽሐፍ ማንበብ ይጠቅማል፡፡

ይህ ስም ማጥፋት ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ሲያጠቃ አፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ እንግሊዝ ስደት ባቀኑበት ወቅት፣ ሲመለሱ፣ እንዲሁም ደርግ ከሥልጣን ሲያወርዳቸው  ተጠናክሮ የቀጠለ የልሂቃን የፖለቲካ ባህል ሆኖ ቆይቷል፡፡

ደርግም በኃይለ ሥላሴ ላይ የሆነውንና ያልሆነውን  እየለጠፈ ሥርዓቱን  ደብዛው እንዲጠፋ ካደረገ በኋላ፣ እሱም በተራው በፖለቲካ ባህላችን የተለመደውን የስም ማጥፋት  ማዝነብ ጀመረ፡፡ የደርግ ተቃዋሚዎችም ደርግን በቀላሉ አልለቀቁትም፡፡ ‹‹ሃይማኖት የለሽ››፣  ‹‹መኃይም››፣  ‹‹ያ ሰው በላ››  እና የመሳሰሉትን በደርግ ላይ በመለጠፍ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ ሕወሓት ጫካ እያለ  ደርግን  ‹‹ያ ሰው በላ››  ሥርዓት በማለት የቻለውን ያህል ሲያወግዝ  ደርግ በበኩሉ ‹‹ገንጣይ አስገንጣይ››፣  ‹‹የእናት ጡት ነካሽ››  በማለት በሰፊው የፕሮፓጋንዳ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሥልጣን ይዞ የፖለቲካ ባላንጣዎቹ እየፈረጠሙና እየተጠናከሩ በሄዱበት በ1997 ዓ.ም. ምርጫ፣ የቅንጀት ደጋፊዎች ሰላማዊ ሠልፍ በሚያደርጉበትና  በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጠራራ ፀሐይ በተገደሉበት ጊዜ ሕወሓት/ኢሕአዴግ  ካድሬዎች ዓይናቸውን በጨው ታጥበው፣ ‹‹የተገድሉት ወጣቶች ባንክ ሊዘርፉ ሲሉ ነው››  በማለት የተለመደ የልሂቃን የፖለቲካ ባህል ተጠናክሮ እንዲቀጥል አድርገዋል፡፡ ተቃዋሚ  የሆኑትን ሁሉ ‹‹አሸባሪ›› በማለት ከሰዋል፡፡

ስም ማጥፋት ወይም ፕሮፓጋንዳ ያለቅጥ ሲጋነንና ዓላማውን ሲስት በጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አይሁዳዊያን ላይ፣ በመጨረሻም በራሳቸው በጀርመኖች ምን እንዳስከተለ ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ በአገራችንም በቅርቡ ለረጅም ጊዜ  በተነሳው ስም ማጥፋት  በመጨረሻ የተዘጋጀለትን ሕወሓትን ስቶ ወይም አትርፎ ሕዝቡን  ሊጎዳ ችሏል፡፡ አሁንም በዘመናችን የጀርመን አክራሪዎች ስደተኞች  መጤዎች፣ የእኛን የአኗኗር ባህሪ የማይቀበሉ ተጠራርገው  ከአገር  ይውጡ በማለት ማሴራቸው እንደ ተደረሰበት ጀርመኖች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተምረው ነፃ፣ ገለልተኛ፣ በሀቅና በፍትሕ ላይ  ብቻ ተመሥርተው ባቋቋማቸው ተቋማት ጀርመን ገና በእንጭጩ የአክራሪዎችን ሴራ በመበጣጠስ በትክክለኛው የዕድገት  ግስጋሴ  እንድትቀጥል ሆናለች፡፡

በአገራችን ያለው የልሂቃን የፖለቲካ ባህል ካለፈው ስህተትና ውድቀት ተምሮ እንደ ጀርመን ነፃ፣ ገለልተኛ፣ በሀቅና በፍትሕ ላይ ብቻ የተመሠረተ ጠንካራ ተቋም ለመመሥረት ባለመቻሉ የፖለቲካ ሥልጣን ለማግኘት በሚፈልጉና  የፖለቲካውን ሥልጣን  ይዘው ለማቆየት በሚታገሉ የፖለቲካ  ልሂቃን  መካከል የሚደረገው ትግል አቅጣጫውን ሲስትና መጠፋፋት፣ ጥሎ ማለፍ፣ ውጉዝ  ከመአርዮስ፣ በለው፣ ግደለው፣ ፀረ እንትን፣ ፀረ እንትን  ሲባል ሃይ የሚል፣ በሕግ አግባብ፣ በሥርዓት፣ በወግና  በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ባለው መንገድ አደብ የሚያስገዛ ሁኔታ የለም፡፡

ይሁንና በቅርቡ በምርጫ ቦርድ፣ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ በአገር መከላከያ የታየው ለውጥ ይበል የሚባልና ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው፡፡ ይህም ዕውቅና ሊሰጠውና ሊቀጥል የሚገባ አርዓያነት ያለው አቅጣጫ ነው፡፡

ያለ መደራደርና ያለ መወያየት ምክንያት ከየት መጣ?

ከፍተኛ  የስም  ማጥፋት  በሚካሄድበት ወቅት ስሙ በሐሰት ወይም በከፍተኛ  ማጋነን ተዋረድኩ፣ ተሰደብኩ፣ ክብሬ ተነካ የሚለው መንግሥትም ሆነ  የተቃዋሚ  አካል ከስም አጥፊው ጋር ላለመነጋገር፣ ዓይን ለዓይን ላለመተያየት፣ ላለመደራደርና  ላለመወያየት  ምክንያት ያገኛል፡፡  በዚህ ሳንካ የተነሳ  በውይይትና በመነጋገር የአገሪቱን የጋራ ችግሮች ለመፍታት ከመጣር ይልቅ ቂም መቋጠር፣ ጊዜ ጠብቆ ለማጥቃት፣  ለመበቀልና  ሌላ አዙሪት ግጭት ለመፍጠር መሰጠርና መሸመቅ ይጀመራል፡፡ ይህ አዙሪት ለረዥም ዘመን የቀጠለ አሁንም ያለና አንድ ቦታ ካልተሰበረና ካልቆመ፣  እስካሁን  ያለውን ማብቂያና ማለቂያ የሌለው የግጭት  አዙሪት  በፍጥነት እያሽከረከረ በመጨረሻ ወደ መበታተንና  ወደ መፍረስ ይወስደናል፡፡  ይህም ባይሆን  አገራችን  እንዳታድግ፣ ባለችበት እንዳትቀጥል፣  ሁሌ ወደኋላ  የድህነት ምሳሌና አረንቋ እንድትሆን የሚያደርገን የፖለቲካ ባህል ነው፡፡

የፖለቲካ ችግሮችን በመወያየት፣ በመነጋገር፣ ሰጥቶ በመቀበልና በመነጋገር መፍታት ካልተቻለ ማኅበረሰቡ ዕድሜ ልኩን  ለፍቶ ያፈራውን በስንት መከራ በብድርና በልመና የተገኘውን ሀብት በማቃጠል፣ በማውደምና በመበተን  ዕድገትና  ልማት፣ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት አይቻልም፡፡ የውይይት ባህልን በፅኑ መሠረት ላይ መትከል ካልቻልን በፍቅር ወልደን ተንከባክበን ያሳደግናቸውንና ከአብራካችን የወጡ ብርቅ ልጆቻችንን ለጦርነትና ለግጭት መዳረጋችን  አይቀርም፡፡ ልጆቻችን በግጭትና በጦርነት ሲያልቁ ወደ ሌላ ግጭትና ጦርነት መግቢያ  ምክንያት ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ የግጭት አዙሪት ማለት ይኸው ነው፡፡

በመወያየት፣ በመነጋገር፣  በመደራደር፣ ሰጥቶ በመቀበል፣ ከእኔ ይቅር በመባባል ዓለም እንደሚያደርገውና የሠለጠኑ አገሮች እንደሚጠቀሙበት በመወያየት የፖለቲካ  ችግሮቻችንን መፍታት ካልቻልን፣ እኔ ያልኩት ብቻ መሆን አለበት ካልን፣ ከአቋማችን ትንሽ አንኳ ለመንቀሳቀስ ፈቃደኛ ካልሆነ ግን ሁሉን ነገር በኃይል፣ በጉልበት፣ በንዴት፣ በጥላቻ፣ በቂም፣ በክፋትና  እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ ካልን ዘለቄታ ያለው ሰላም፣ ዘላቄታ የለው  ልማት ማምጣት ስለማይቻል በውጤቱ ወጣቶች የሥራ ዕድል ስለማይኖራቸው፣ ሥራ ቢያገኙም የሚረባ ደመወዝ አግኝተው  የተሻለ ሕይወት  መኖር ስለማይችሉ በዚህም የተነሳ ስደት፣ ሥራ አጥነትና ወደ አልባሌ ሱስ መግባት፣ በአጠቃላይ ማኅበራዊ ቀውስ ይፈጠራል፡፡

ሐረገወይን (ፕሮፌሰር) የተባሉ ተወዳጅ የአገራችን ሊቅ፣ ‹‹ጠመንጃ አንስቶ ወደ ጫካ ገብቶ እየዘረፈ መብላት ቀላልና የሰነፍ ሥራ ነው፡፡ እንደ አንድ ገበሬ ጠዋት ተነስቶ አርሶ፣ ጎልጉሎ፣ አርሞና ኮትኩቶ የዘራውን አጭዶ፣ ከምሮ የገበሬ ኑሮ መኖር እውነተኛው ጀግንነትና  የሚያኮራ ሕይወት›› መሆኑን አሳይተዋል፡፡ ይህንን አስተሳሰብ በጥልቀት በመመልከትና በማስረፅ የ‹‹ገዳይ እወዳለሁ፣ የዘራፍ›› ወዘተ ኋላቀር የፖለቲካ ባህላችንን ማለዘብ ቀስ በቀስም የኋላቀርነታችን ምክንያት መሆኑ በማወቅ  የሚገድልን ሳይሆን  የሚሠራንና የሚያድንን የማድነቅና የማሞካሸት የፖለቲካ ባህል መፍጠር አለብን፡፡

የሰው ስም ማጥፋትና ማጠልሸት ምንም ሙያ የማይጠይቅ የሰነፍ ሥራ ነው፡፡ በሕይወታቸው ይህ ነው የማይባል ሥራ ያልሠሩ ዋና ተግባራቸው የሚሠራን ሰው  መሳደብ ነው፡፡ የሚሠራውን የሚደክመውን፣ የሚተጋውን የኋላ ታሪክ በመምዘዝ የአሁን መልካም ተግባርን ለማንኳሰስ፣ ለማጥላላት ይጥራሉ፡፡ አዲስ ሐሳብ ማመንጨት፣ የሚሠራን ሰው ማበረታታት፣ የተሻለ መነገድ ማሳየት ቅንነትን፣ ማስተዋልንና ማሰብን ይጠይቃል፡፡ በአገራችን ያለው የአብዛኛው የልሂቃን የፖለቲካ ባህል መልካም ሐሳብ  ከማመንጨት፣ የተሻለ መነገድ ከማመላከት ይልቅ ማንቋሸሽ፣ ማበሻቀጥና ማጥላላትን የሚመርጥ ይመስላል፡፡ እዚህ ላይ አንባቢያን ልብ እንዲሉ የምሻው ትክክለኛ ያልሆነና አቅጣጫውን የሳተ ሐሳብና ተግባርን መተቸትና እንዲታረም ሐሳብ በማቅረብና በስድብና በማንቋሸሽ መካከል ትልቅ ልዩነት መኖሩን ነው፡፡

በቅን ልቦና ተነሳስቶ ‹‹ይህ አቅጣጫ፣ ተግባር ትክክል አይደለም›› በማለትና በመተቸትና በክፋትና ተንኮል ተነሳስቶ፣ ‹‹ይህ አቅጣጫ፣ ይህ ተግባር ቆሻሻ ነው፡፡ ይህንን አቅጣጫ ያስቀመጠው ድሮ እንዲህ ነበር›› በማለት መካከል የሰፋ ልዩነት አለ፡፡ አንደኛው ተግባሩ ሐሳቡ እንዲሻሻል ሐሳቡና ተግባሩ ላይ ሲያተኩር ሁለተኛው ሐሳቡ እንዲጠፋ፣ ተግባሩ እንዲነቀልና እንዲደመሰስ የሚተጋ ነው፡፡ ሁለተኛው ከሐሳቡና ተግባሩም አልፎ ሐሳቡ ያቀረበው ላይ ያነጣጥራል፡፡ እንግዲህ ለአገራችን ያልበጀው ወደፊትም የማይበጀው  የልሂቃን የፖለቲካ ባህል ሁለተኛው ነው፡፡ በተንኮል፣ በክፋት፣ በግል ጥቅምና ፍላጎት ተነሳስቶ መልካም ለመሥራት የተነሳውን ሰው ስም ማጥፋትና ተግባሩ እንዲኮላሽ የማድረግ  ጥረት አገራችንን  ለዘለዓለም  በድህነት፣ በረሃብ፣ በድንቁርናና በኋላቀርነት እንድትታወቅ ያደረገ የፖለቲካ ባህላችን ነው፡፡ እንዲህ ያለው የልሂቃን  የፖለቲካ ባህል በሕግ ካልተከለከለ፣ በትምህርት ካልተገራ ስለዕድገትና ልማት ማውራት የማይቻል ነው፡፡ የልሂቃን  የአጭር ጊዜ የግል ፍላጎት ከማኅበረሰቡ የረዥም ጊዜ ዘለቄታዊ ፍላጎት ጋር ሲጋጭ በአንድ አገር ውስጥ ውድቀትና ቀውስ ያስከትላል፡፡

በግድያና  በስም ማጥፋት  የፖለቲካ  ሥልጣንን መመኘት አገራችን ወደ መቀመቅ ያወረደና  የደሃ ደሃ ለማኝ ያደረገን የፖለቲካ ባህላችንን ነቅለን ሌላው  ዓለም የደረሰበት የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የልማትና የሰላም የጥበብ ዕርካብ ላይ ለመድረስ  የሚረዳ የተሻለ አዲስ የፖለቲካ ባህል መገንባት ይቻላል፡፡ የግድ በማዋረድ፣ በመሳደብ፣ በሴራና በመጠፋፋት ሥልጣን ካልያዝኩ ብሎ ሙጥኝ የሚባልበት ምንም ዓይነት አመክንዮ የለም፡፡ በተከታዩ ጽሑፍ ሌሎች የዓለም አገሮች የተሳሳተ ያሉትን የፖለቲካ ባህል እንዴት ቀየሩ? በመቀየራቸውስ ምን አገኙ? በማለት የጃፓንና  የቺሊን የፖለቲካ ባህል እናያለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ የልሂቃን የፖለቲካ ባህል ላይ ጥናት ያደረጉ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚየንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው solgosole@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡