
2 የካቲት 2025
የታሪኩ መነሻ አንድ እርዳታ ጠያቂ የጻፈችው ኢሜይል ነው። ታሪኩ ከስድስት ዓመታት በኋላ በማጭበርበር እና በመድፈር የተከሰሰ ሰው 12 ዓመታት ታስሮ ተጠናቋል።
በስተመጨረሻ ድል የተገኘው ሴቶች ባደረጉት ትግል ነው።
ወደ ታሪኩ መነሻ እንሂድ። በአውሮፓውያኑ 2017 አንድ ሴት ለጋዜጠኛ ኢሜይል ትልካለች።
ክሪስቶፈር ሀርኪንስ የተባለ ሰውን ቲንደር በተባለው መተግበሪያ ላይ ከተዋወቀች በኋላ 3,247 ፓውንድ እንደሰረቃት ተናገረች።
ለዚህ ዘገባ ሊሳ ብለን የምንጠራት ሴት እንዳለችው ክሪስቶፈር ሽርሽር ሄደው የፍቅር ጊዜ እንዲያሳልፉ ገንዘብ ጠየቃት።
ገንዘቡን ከሰጠችው በኋላ ድምጹ ጠፋ። ሌላ ሰውንም እንዳያጭበረብር ብላ ነው ታሪኳን ያጋራችው።
ስኮትላንድ ፖሊስ ጋር ብትሄድም ጉዳዩ መፍትሔ አላገኘም።
- በርካቶች የሚበለጽጉበት የኢንተርኔት ማጭበርበሪያ ዘዴዎች7 ሰኔ 2021
- ለኢንስታግራም ‘ፕራንክ’ ሙሽራ ሆና ተውና ጋብቻው የእውነት ሆኖ የተጭበረበረችው ‘ሙሽሪት’11 ጥር 2025
- ቲክቶከሮች ለምን ያለቅሳሉ? ከምራቸው ነው? ለምንስ አሳዛኝ ይዘት የበለጠ ይመርጣሉ?25 ጥር 2025

ክሪስቶፈር ሊሳን ሲተዋወቃት ከፍተኛ ፍቅር በማሳየት ነበር የቀረባት። ገንዘቡን እስከሚወስድ ድረስ መልካምነቱን ቀጥሏል።
በ30ዎቹ ዕድሜ የምትገኘው ሊሳ የተጻጻፉትን የዋትስአፕ መልዕክት አጋልጣለች።
ሊሳ ታሪኩን ለጋዜጠኛ መናገሯን ስትነግረው ታሪኩ ካልታተመ ገንዘቡን እንደሚመልስላት ተናገረ።
ገንዘቡን ለመመለስ ተስማምቶ ከሊሳ ጋር ተቀጣጠረ። የቢቢሲ ጋዜጠኛም አብራት ሄደች።
ገንዘቡን በፖስታ አስቀምጦ እሱ ግን ሊገኝ አልቻለም።
ከቢቢሲ ጋዜጠኛ ካትሪካ ስቱዋርት ጋር በስልክ ሲያወራ ምን እንደሚል ለመረዳት አልቻለችም ነበር።
“አንድ ነገር ይልና ጥያቄ ሲጠየቅ ያለውን ይለውጣል። ሌላ ነገር ደግሞ ይላል። የሚመርጣቸው ሴቶች ጎበዝ እና ተናጋሪ ናቸው” ትላለች።
የቢቢሲ ጋዜጠኛ እንዴት ግለሰቡ እንዳጭበረበረ እና እስከ አካላዊ ጥቃት እንደደረሰ ትናገራለች።

ክሪስቶፈርን የሚያውቅ አንድ በ20ዎቹ ዕድሜ ክልል ያለ ሰው እንደሚለው ሰውየው አደገኛ ስለሆነ ጥንቃቄ ያሻል በማለት ተናገሯል።
ሰዎች ላይ አካላዊ ጥቃት እንደሚያደርስም ገልጿል።
ክሪስቶፈር በመላዋ እንግሊዝ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ነው ሴቶችን የሚያጭበረብረው።
ሽርሽር እንሂድ ብሏት 1,600 ፓውንድ አጭበርብሯል። በስሙ ገንዘብ እንድትበደር ጫና ቢያሳድርም እሺ አላለችም።
ቢቢሲ ከ20 በላይ ሴቶች በዚህ ግለሰብ መጭበርበራቸውን አውቋል። አካላዊ እና ወሲባዊ ጥቃት ያደረሰባቸውም እንዳሉ ተናግረዋል። ፖሊስ ጉዳዩ የሲቪል ጉዳይ ነው ከሚል በዘለለ መፍትሔ አልሰጠም።
የስኮትላንድ ፖሊስ ለቢቢሲ ጋዜጠኛ ደወለ።
“ግለሰቡ ላይ ምርመራ ስለምንጀምር ስለእሱ መጻፍ ማቆም ትችያለሽ ወይ? አሉኝ። ከዚያም መጻፍ አቆምኩ። ፖሊስ እኔን ካዋራኝ በኋላ ቃለ ምልልስ ያደረግኩላቸው ብዙ ሴቶች በይፋ ክስ መሠረቱ። ሒደቱ ረዥም እንደሆነ ቢያውቁም ተጠያቂ እንዲሆን ለማድረግ ትግል ጀመሩ” ትላለች።
ምርመራው ተጀምሮ ለወራት ምንም ስላልተሰማ ሴቶቹ ተጨንቀው ነበር።
በ2019 ሲታሰር ግን ጭንቀታቸወ ቀለለ።
በ2020 መባቻ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ከለንደን ተደወለላት።

“ከክሪስቶፈር ጋር በአምስት ኮከብ ሆቴል እንደቆየች የደወለችው ሴት ነገረችኝ። ሐሰተኛ ስም መጠቀሙን የሆቴሉ ሠራተኞች ሲነግሯት ጉግል አደረገችው። ስለእሱ የጻፍኳቸውን ዘገባዎች አገኘቻቸው። በጣም ፈርታ ነበር የደወለችልኝ። ወደ ሆቴል ክፍሉ ገብታ ትክክለኛ ስሙ ክሪስቶፈር እንደሆነ ከመታወቂያው አይታ ከሆቴሉ ወጣች” ትላለች ጋዜጠኛዋ።
የለንደን ፖሊስ በቁጥጥር ሥር እንዲያውለው አደረገች።
ከመታሰሩ በፊት ወደ ቢቢሲ ደውሎ ጋዜጠኛዋ ስሙን ለማጥፋት እየሞከረች እንደሆነ ተናገረ።
ሆኖም ግን የዓይን እማኞች የሰጡት ምስክርነት ከዚህ የተለየ ነበር። ጋዜጠኛዋ የፍርድ ሒደቱን እንዲህ ነው የምትገልጸው።
“ጥንካሬያቸው እና ድጋፋቸው ረድቶኛል። ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲቀርብ አንድ ቀን ሳልዘል ተገኘሁ። ቀድሞ ከነበረው ሰውነቱ ቀንሷል። ስለ መልኩ የሚጨነቅ ሰው ቢሆንም ፍርድ ቤት ሲቀርብ ሱፉ ሰፍቶት ነበር። የማይመሳስ ጫማ እና ካናቴራ መልበሱም ያስጨንቀው ነበር። በመድፈር፣ በአካላዊ ጥቃት፣ ያለ ፈቃድ ቪድዮ በመልቀቅ፣ በማስፈራራት እና በመበዝበዝ በቀረቡበት 19 ክሶች ጥፋተኛ ተባለ።”
ዘጠኝ ሴቶች ከ214,000 ፓውንድ በላይ ማጭበርበሩን አምኗል። በመጨረሻም የ12 ዓመታት እስራት ተፈርዶበታል።
“ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሲያሳልፍበት ‘ይሄ የሆነው ባንቺ ምክንያት ነው’ አለኝ። ተሳስቷል። ይሄ የሆነው በጀግና ሴቶች ምክንያት ነው። ሳይፈሩት ከሰውታል። ለዓመታት ሳይታክቱ ተከታትለው ለፍርድ አቅርበውታል።”