ኮንጎ

2 የካቲት 2025, 09:55 EAT

ከምሥራቃዊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተገኘ የታንታለም ማዕደን የአብዛኛዎቻችን ሰልክ ተሠርቷል።

አሁን በአካባቢው ጦርነት ተነስቷል። ተንቀሳቃሽ ስልክን ጨምሮ ሌሎችም ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እንዲሠሩ የሚያስፈልገው ታንታለም በቦታው በስፋት ይገኛል።

በተለይም ኃይልን አምቆ የመያዝ አቅሙ ስልክ ቻርጅ ተደርጎ የሚቆይበት ምክንያት ነው።

ይህ ማዕድን በሩዋንዳ፣ ብራዚልና ናይጄሪያም ይገኛል። 40 በመቶው የሚገኘው ግን በኮንጎ ነው።

ኤም23 (M23) ዋነኛ የማዕድን ማውጫ ቦታዎቹን ተቆጣጥሯል።

ለወራት የቀጠለ ግጭት በአካባቢው ነበር። በዋነኛዋ የንግድ ቀጠና ጎማ አማጺያኑ ጥቃት ሲፈጽሙ ነው ዜናው በስፋት የተሰማው።

ከሩዋንዳ የምትዋሰው ጎማ ከተማ ማዕድን በዋነኛነት የሚወጣባትና የሚነገድባት ቦታ ናት።

ኤም23 አምና በአካባቢው ተስፋፍቷል። ታንታለም የሚገኝበትን አካባቢ መቆጣጠሩም ተገልጿል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሌሎች አማጺያን እንደሚያደርጉት ሁሉ ኤም23 የተነሳው የተጨቆነ ጎሳን መብት ለማስከበር በሚል ነበር።

ከዚህ ቀደም ማዕድን በዋናነት የሚወጣበትን ሩባያ ከተማ በቁጥጥር ሥር አውሏል።

በአካባቢው የተለያየ ጎሳ አባላት ናቸው ማዕድን የሚያወጡት። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ስለሚሠሩ የተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ ይገባሉ፤ በመሬት መንሸራተትም ይጎዳሉ።

ማዕድን የሚወጣበት መንገድ ጤናንም የሚጎዳ ነው።

አማጺያኑ ሩባያን ሲቆጣጠሩ “እንደ መንግሥት ያለ” መዋቅር መዘርጋታቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጿል።

ፈቃድ የተሰጣቸው ነጋዴዎች ብቻ ናቸው በአካባቢው እንቅስቃሴ የሚያደርጉት።

ታንታለም የሚገኝነትን ኮልታን ማዕድን ላገኘ አካል በአንድ ኪሎግራም 7 ዶላር ያስከፍላሉ።

በዚህ መንገድ ኤም23 በወር 800,000 ዶላር እንደሚያገኙ የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።

ገንዘቡ አመጹን የሚደግፍ ነው።

ኮንጎ

ኤም23 የሚቆጣጠረው ማዕድን እንዴት ወደ ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር እንደሚገባ ግልጽ አይደለም።

ለጥያቄው መልስ ኤም23ን የምትደግፈው ሩዋንዳ ናት ይላል የመንግሥታቱ ድርጅት።

ዕውቅና የሚሰጥበት መንገድ ኢኖቬቲቭ ቲን ሰፕላይ ቼን ኢንሽየቲቭ ይባል። ለስልክና ሌሎች ኤሌክትሮኒክሶች ጥቅም የሚውለው ማዕድን በግጭት ከሚናጡ አካባቢዎች አለመወሰዱን ማረጋገጫ ነው።

በአሜሪካና የአውሮፓ ኅብረትም ተመሳሳይ ስምምነት አለ። ቲን፣ ታንታለም፣ ቱንግቲን እና ወርቅ የሚሸምቱ ተቋማት ግጭትን ለማባባስ የሚውል ገንዘብ ፈሰስ እንዳያደርጉ የሚያደርግ ነው።

ሆኖም ግን ዕውቅና የሚሰጥበት አካሄድ ተተችቷል።

አይፒአይኤስ በተባለ ተቋም የደኅንነትና የሃብት ጥበቃ ባለሙያ ኬን ማታይሰን እንደሚለው፣ በየቦታው ውስን ማዕድን መኖሩ ለአካባቢው አስተዳደር ለመቆጣጠር ከባድ ያደርገዋል።

ኮንጎ

ዕውቅና የሚሰጠው አካል የትኛው ማዕድን ከየት እንደወጣ መግለጫ ቢለጥፍም ማዕድኑ ሲጓጓዝ በትክክል ከየት እንደመጣ አይታወቅም። ሌላው ችግር ሙስና ነው።

“የመንግሥት ተቋማት ማዕድን ከየት እንደመጣ የሚገልጸውን መለያ ለነጋዴዎች እንደሚሸጡ ይሰማል። ሠራተኞች በአግባቡ ስለማይከፈላቸው ነው ይሄን የሚያደርጉት። ነጋዴዎቹ መለያውን ገዝተው ማዕድኑ ላይ ይለጥፋሉ” ይላል ባለሙያው።

ተቋሙ ግን ይህንን ክስ ከዚህ ቀደም አስተባብሏል። በገለልተኛ ወገን ኦዲት እንደሚደረግና ለበርካታ ድሃ አርሶ አደሮች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ ገልጿል።

ስልክ

የተመድ ባለሙያዎች ወደ ሩዋንዳ የሚሄደውን ማዕድን ይከታተላሉ። ኤም23 ሩባያ ከተማን ከያዘ በኋላ ማዕድን ማውጣቱ ቀጥሏል።

ሩዋንዳ የራሷ የኮልታን ማዕድን አውጥታ ከኮንጎ ከሚሄደው ጋር ሲደባለቅ “የንግድ መስመሩን እንደሚያዛባ” ባለሙያዎች ይናገራሉ።

“አብዛኛው የንግድ ትስስር በኤም23 በኩል ነው የሚካሄደው። ወደ ሩዋንዳ ይላካል። የኮንጎ አለመረጋጋት ሩዋንዳን እንደሚጠቅም አይተናል” ይላል ባለሙያው።

የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መረጃ እንደሚያሳየው የሩዋንዳ ኤክስፖርት ከ2022 እስከ 2023 በ50% ጨምሯል።

የሩዋንዳ መንግሥት ቃል አቀባይ ዮላንዴ ማኮሎ ግን በአገራቸው ያለውን ማዕድን እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ።

“በምሥራቅ ኮንጎ ለመብታቸው የሚታገሉ ሕዝቦች ያሉበትን ሁኔታ ከጥቅም ጋር ማስተሳሰር ጨለምተኛ ነው ” ብለዋል።

የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ የተመድ ባለሙያዎችን ግምገማ አጣጥለዋል።

በምሥራቅ ኮንጎ ለዓመታት ከቀጠለው ግጭት ማን እያተፈ ነው የሚለው አጠያያቂ ሆኖ ቀጥሏል።

የከንጎ መንግሥት አምና በፈረንሳይ በከፈተው ክስ አፕል “በግጭት አካባቢ ማዕድን” መጠቀሙን ለፍርድ ቤት አስታውቋል።

አፕል ግን የቀረረበትን ክስ አጣጥሎ ግጭት እየበረታ ሲሄድ ከኮንጎና ሩዋንዳ ማዕድን አለመውሰዱን ገልጿል።

የሌሎች ቴክኖሎጂ ተቋማት አቋም እስካሁን ስላልታወቀ ኤም23 የአካባቢውን ማዕድን እየሸጠላቸውም ሊሆን ይችላል።