ዶናልድ ትራምፕ

2 የካቲት 2025, 08:04 EAT

ዶናልድ ትራምፕ በሶማሊያ የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ጥቃት አቀነባባሪዎች ላይ የአየር ድብደባ እንደተፈፀመ ይፋ አደረጉ።

“እኒህ ዋሻ ውስጥ ተደብቀው የተገኙ ገዳዮች ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቿን ስጋት ላይ ለመጣል ያሰቡ ናቸው” ሲሉ በማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው ፅፈዋል።

“በአየር ድብደባ የሚኖሩበትን ዋሻ አውድመናል፤ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳናደርስ በርካታ ሽብርተኞች ገድለናል” ብለዋል።

የሶማሊያ ፕሬዝደንት ቢሮ የኤክስ ገፅ እንዳለው በሰሜናዊ ሶማሊያ አሜሪካ የአይኤስ መሪዎች ላይ ስለፈፀመችው የአየር ድብደባ መረጃው አለው።

ቢቢሲ ደረሰ የተባለውን ጥቃት በተናጠል ማጣራት አልቻለም።

ትራምፕ በጥቃቱ ተገደሉ የተባሉ ሰዎችን ስም ይፋ አላደረጉም።

ዶናልድ ትራምፕ “ይህ ለአይኤስአይኤስ እና ሌሎች አሜሪካን ለማጥቃት ለሚሞክሩ መልዕክት ነው። ፈልገን አግኝተን እንገድላችኋለን!” ብለዋል።

የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ቢሮ የኤክስ ገፅ እንደፃፈው ፕሬዝደንቱ “ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት በመዋጋት ረገድ የዩናይትድ ስቴትስን የማይናወጥ ድጋፍ አመስግነው የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን ቁርጥኘነት” ይቀበሉታል።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴዝ በለቀቁት መግለጫ “በጥቃቱ በርካታ የቡድኑ አባላት መገደላቸውን አረጋግጠናል። ሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም” ብለዋል።

ሄግሴዝ አክለው እንዳሉት የአየር ድብደባው የአይኤስን “የሽርብ ጥቃት የማቀድና የመፈፀም አቅም የበለጠ የሚያዳክም” እና “አሜሪካ ሁሉም ቢሆን ሽብርተኞችን አሳድ ለማጥፋት ዝግጁ መሆኗን” የሚያሳይ ነው።

ሚኒስትሩ ድብደባው የተፈፀመው ጎሊስ ተራራ በተባለው የሰሜን ምስራቅ የሶማሊያ ግዛት ነው።

ሰሜን ምስራቅ የሚገኘው የፑንትላንድ አስተዳደር “ከፍተኛ የአይኤስ አመራሮችን በገደለው” የአየር ድብደባ የተሳተፉ “ዓለም አቀፍ ወዳጆችን” አመስግኗል።

ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ በተለይ በሶሪያ እና በኢራቅ የተስፋፋው አይኤስ በአሁኑ ወቅት በተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት ተገድቦ ይገኛል።

የአሜሪካ አየር ኃይል

ሶማሊያ የሚገኘው የአይኤስ ክንፍ የተቋቋመው በ2015 ሲሆን የቡድኑ መሥራቾች ከአል-ቃኢዳ የሸሹ እና በሶማሊያ ትልቁ የጂሀድ ቡድን ከሆነው አል-ሸባብ የተውጣጡ ናቸው።

በሶማሊያ የሚገኘው አይኤስ በተለይም በአካባቢው ነዋሪዎች አነስተኛ ጥቃቶችን በማድረስ ይታወቃል ይላል የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ዳይሬክተር ያወጣው መረጃ።

ትራምፕ በመግለጫቸው የቀድሞውን አስተዳደር የወቀሱ ሲሆን ጆ ባይደን በፍጥነት ወደ ተግባር ተስኗቸው ነበር ብለዋል።

በ2023 በባይደን ትዕዛዝ መሠረት የአይኤስ መሪ የነበረው ቢላል አል-ሱዳኒ እና 10 አጋሮቹ በሶማሊያ በሚገኘው ተራራማ ዋሻ ውስጥ መገደላቸው ይታወሳል።

ትራምፕ በ2020 ከሥልጣን ከመውረዳቸው በፊት በርካታ የአሜሪካ ወታደሮች ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ ማዘዛቸው አይዘነጋም። በሁለተኛው ዙር የሥልጣን ዘመናቸውን ከጀመሩ ሁለት ሳምንት ሳይሞላቸው በሶማሊያ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር አዘዋል።

ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በሌሎች ሀገራት ግጭት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ የለባትም ብለው ያምናሉ። ባይደን ደግሞ ከ9/11 ጥቃት በኋላ የአሜሪካ ተሳትፎ መቀነስ አለበት ይላሉ።

ነገር ግን የሶማሊያ ጉዳይ በዋሺንግተን ዘንድ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ይመስላል። አሜሪካ የአል-ሸባብን አቅም ለማዳከም ለበርካታ ዓመታት ስትሰራ ቆይታለች።

ምንም እንኳ ትራምፕ ከሥልጣን ሊወርዱ ጥቂት ጊዜ ሲቀራቸው በሶማሊያ ያሉ የአሜሪካ ወታደሮች እንዲወጡ ቢያዙም በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ወቅት ተደጋጋሚ ጥቃት እንዲፈፀም ትዕዛዝ አስተላለፈዋል።

ባይደን የትራምፕን ትዕዛዝ በማጠፍ የአሜሪካ ወታደሮች በሶማሊያ ሊቆዩ ይገባል ማለታቸው ይታወሳል። ትራምፕ እስካሁን የአሜሪካ ወታደሮች ከሶማሊያ እንዲወጡ ትዕዛዝ አላስተላለፉም።

በመጀመሪያው የትራምፕ የሥልጣን ዘመን ወቅት መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ማርክ ኤስፔር ትራምፕ በአፍሪካ “የአሜሪካ ወታደሮችም ሆኑ ዲፕሎማቶች እንዲኖሩ እንደማይፈልጉ” በመፅሐፋቸው አስፍረዋል።

ትራምፕ በመጀመሪያው የፕሬዝደንትነት ጊዜያቸው ሁለት የሰብ ሰሀራ አፍሪካ መሪዎችን ጋብዘው ቢያነጋግሩም አፍሪካን ጎብኝተው አያውቁም።

ነገር ግን አሁን ቻይና እና ሩሲያ በአፍሪካ ያላቸው ተፅዕኖ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ አህጉሪቱን በተለየ መነፅር ሊመለከቷት ይችላል የሚል ትንታኔ አለ።