ሳሙኤል
የምስሉ መግለጫ,በዱባይ የግንባታ እና የጽዳት ሥራን የሚሠራው ሳሙኤል አሁን ወደ ፋሽን ሞዴልነት ዘርፍ እየገባ ነው

2 የካቲት 2025

ዱባይ ከገባ ወራት ናቸው የተቆጠሩት። ተወልዶ ያደገው ቡራዩ ነው። በኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርስቲ ቢዝነስ ማኔጅመት ተማሪ ነበር። አቋርጦ ወደ ዱባይ አቀና። ዱባይ ሄዶ በግንባታ ተቋም ውስጥ ተቀጠረ።

ሳሙኤል ባይሳ ቱፋ ይባላል። አንድ ላምቦርጊኒ መኪና ሲመለከት ሕይወቱ በዚያ ምክንያት እስከ ወዲያኛው እንደሚለወጥ አልገመትም።

ዱባይ የሄደው ገንዘብ ተበድሮ በብዙ መከራ ነበር። ዱባይ ግን ያልጠበቀውን ዕድል ይዛ ጠበቀችው።

“የድሃ ልጅ ነኝ። ቤተሰብ ከእኔ ይጠብቃል። እኛ አገር ደግሞ ከተመረቁ በኋላ ያለው ሁኔታ ይታወቃል።”

በዱባይ ከአንድ ጓደኛ ውጭ ማንም አልነበረውም። ለቤተሰቡ ሲል ግን ስደትን መረጠ።

ታይገር በሚባል ተቋም ተቀጠረ። የጽዳት፣ ሲሚንቶ የማቀበል እና ሌላም ሥራ በተቋሙ ይሠራል።

ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ዱባይ ሲያቀና “ትልቅ ተስፋ ይዤ ነበር” ይላል።

ቤተሰቡ ትምህርቱን በማቋረጡ ደስተኛ ባይሆንም ዱባይ የሄደው “ቤተሰቤን አሳርፍበታለሁ። እግዚአብሔር ትልቅ ነገር ያሳየኛል” ብሎ ከልቡ በማመን እንደነገር ይናገራል።

ታይገር ኩባንያ ክፍያው 900 ድርሃም ነው። ከዚያ ላይ ለመታወቂያ እና ለምግብ ተቀናንሶ ወደ 800 ድርሃም ይደርሰዋል።

እንዲህ እንዲያ እያለ ቆየ።

ከዕለታት አንድ ቀን ከሥራ ወጥቶ በዱባይ ጎዳና እየኳተነ ሳለ ላምቦርጊኒ መኪና ተመለከተ። ደነገጠ። ምን ጉድ ነው ደግሞ ይሄ ብሎ ፈዝ’ዞ ቀረ።

“በጣም ነው እኮ የሚያምረው” ሲል መኪናውን እንዳየው የተሰማውን ልዩ ስሜት ይገልጻል።

ሳሙኤል የሚሠራው የዓለም ረዥሙ ሕንጻ ቡርዥ ኻሊፋ ያለበት አካባቢ ነው። እዚያ ደግሞ እንዲህ እንደ ላምቦርጊኒ ያሉ ቅንጡ መኪናዎች የሚርመሰመሱበት ሰፈር ነው።

“አተኩሬ አየሁት። አልጠገብኩትም። በጣም ደስ ስላለኝ ዝም ብዬ አተኩሬ አየሁት” ይላል።

ሳሙኤልና ካሜሮናዊው ሞዴል ኤሪክ ፊት
የምስሉ መግለጫ,ሳሙኤል እና ካሜሮናዊው ሞዴል ኤሪክ ፊት

ሳሙኤል ላምቦርጊኒውን ሲመለከት ለካንስ ላምቦርጊኒውም ሳሙኤልን እየተመለከተ ነበር።

“እኔ ያየሁት መኪናውን ነው። ለካ ከውስጥ ሆኖ ባለመኪናው እኔን እያየኝ ነበር። እኔ አላወቅኩም።”

”ምን ታያለህ?” ብሎ ጠየቀኝ።

“‘ይሄን መኪና አይቼ የማውቀው ፊልም ላይ ብቻ ነው። ውድ ስለሆነ እኛ አገር የለም’ አልኩት።”

”እውነትህን ነው?”

መኪናው በጣም እንደሚያምር ደግሞ ደጋግሞ ነገረው። ባለመኪናው በተራው በሳሙኤል መገረም ተገረመ።

ወደ መኪናው ጠጋ እንዲል ጋበዘው። ”አሁንስ ደስ ይላል?” ብሎ ጠየቀው።

”በጣም እንጂ!”

የበለጠ ሲጠጋ መኪናውን ከፍቶ እንዲገባ ጋበዘው።

ሳሙኤል “በጭራሽ” አለ። አላደርገውም ብሎ ቆመ። እየተግደረደረ አልነበረም። ከልቡ ነው እምቢ ያለው።

ሆኖም መግባት ሳይፈልግ ቀርቶ አልነበረም። ነገር ግን የለበሰው ልብስ ላምቦርጊኒዋን እንዳያቆሽሻት ስጋት ገብቶታል።

“‘ኮንስትራክሽን ስለምሠራ አቧራ ነኝ። በዚያ አቧራ መኪናው ውስጥ መግባት አልችልም’ አልኩት።” ይላል።

እንዲገባ አጥብቆ ሲያበረታታው ግን መኪናውን ከፍቶ ገባ። ማውጋት ጀመሩ።

”ከየት አገር ነህ?”

”ከኢትዮጵያ”

ሹፌሩ “መኪናውን በደንብ ስለምነዳ ተዘጋጅ” ሲል ሳሙኤልን አስጠነቀቀው።

”ችግር የለም” አለ ሳሙኤል፣ ቆፍጠን ብሎ።

“በሚያስፈራ ስፒድ ሲነዳው ግን ፈራሁ።”

በእርግጥም የመኪናው ፍጥነት ሳሙኤልን በጣም አስፈርቶት ነበር። ነፍሱ ልትወጣ! ላምቦርጊኒው ክንፍ አውጥቶ የበረረ ያህል ተሰማው።

“ፈርቼ ነበር – በጣም ፈርቼ ነበር” ይላል፤ ”ወዲያው የምሞት ነበር የመሰለኝ።”

ፍጥነቱ ሲከብደው ”በቃ አውርደኝ” ብሎ ጮኽ።

ሹፌሩ ካወረደው በኋላ መንገዱን ቀጠለ።

ለካንስ ይህ ሁሉ ድራማ በድብቅ እየተቀረጸ ነበር። ሳሙኤል ይሄን በጭራሽ አላወቀም።

የተቀረጸው ተንቀሳቃሽ ምሥል ‘ፕሪሚየም ኢን ዱባይ’ በሚባል ገጽ ተለቆ ምን ያህል ሰው እንዳየው እና ምን ያህል ዝነኛ እንደሆነ ሳሙኤል አልሰማም።

እሱ ወደ ሥራው፣ ወደ ሕይወቱ ተመልሷል። ወደ ኮንስትራክሽኑ ገብቷል።

ሳሙኤል

ከስድስት ቀናት በኋላ ያልጠበቀው ነገር ተከሰተ። ስልኩ ጠራ።

ኤሪክ የሚባል ካሜሩናዊ ነበር የደወለለት። የሚኖረው እንደ ሳሙኤል ዱባይ ነው።

በአምስት ቀን ውስጥ በኢንስታግራም ላይ 1.2 ሚሊዮን ሰዎች ያዩት ቪዲዮ ኤሪክ ዘንድ ደርሷል።

ኤሪክ ሳሙኤልን በእግር በፈረስ ፍለጋ ገባ።

ከሳሙኤል ጋር ተገናኙ።

ጠፍቶ እንደተገናኘ የእናት ልጅ ሳሙኤልን አቅፎ ሰላም አለው። ታሪኩንም አጫወተው።

ካሜሮናዊው ኤሪክ የሳሙኤል ነገር ሕይወቱን መልሶ አሳይቶታል።

እሱም ከስምንት ዓመት በፊት ዱባይ ሲመጣ ላምቦርጊኒ መኪና አይቶ ደንግጦ ነበር። “በየመንገዱ ፈዝዤ እቀር ነበር” አለው።

ሳሙኤልም መኪናውን ሲያይ ያሳየውን መገረም የተረዳው ኤሪክ በታላቋ የዓለም የንግድ እና የባለጸጎች ከተማ ዱባይ የፋሽን ሞዴል ነው።

ከእራሱ ታሪክ ጋር የሚመሳሰለውን የሳሙኤልን ቪዲዮ ከተመለከተ በኋላ እሱን ለማግኘት ብዙ ደክሟል።

በመጨረሻም እንዴት እንዳገኘው ነገረው።

ሳሙኤል በቪዲዮው ላይ የለበሰው የሥራ ልብስ ነበር እንዲያገኘው የረዳው። የልብሱ ደረት ላይ በነበረው የድርጅቱ ስም (ባጅ) አማካኝነት ነው የፍለጋ ፍንጭ ያገኘው።

እንጂማ ሁለቱ የአፍሪካ ልጆች ተለያይተው ቀርተው ነበር።

“ሲያገኘኝ ወንድሙን እንዳገኘ ሰው በጣም አቀፈኝ። ደነገጥኩና እኔም አቀፍኩት” ይላል ሳሙኤል።

ኤሪክ እና ሳሙኤል ከተገናኙ በኋላ ብዙ አወሩ። አብሮት እንዲሠራ ጠየቀው።

ሌላ ቪድዮ ሠሩ። ተወደደ። ስፖንሰሮች አብረዋቸው ለመሥራት ጠየቋቸው። የቀን ሠራተኛው የሳሙኤል ሕይወቱ የለውጥ መንገድ መያዝ ጀመረ።

ሳሙኤል ባይሳ

ኤሪክ መጀመሪያ ያገኘው ቀን የተወሰነ ገንዘብ ሰጥቶት ሊረዳው እንደሚፈልግ ነግሮት ነው የተለያዩት። ኤሪክ እንደ ሳሙኤል ሁሉ ዱባይ ውስጥ ጽዳት ከመሥራት ተነስቶ ነው ታዋቂ ሞዴል የሆነው።

ኤሪክ ታዋቂ ሞዴል ከመሆኑ በፊት የነበረው ሕይወት እና የሳሙኤል ሕይወት ተመሳሳይ ስለሆነ ለሳሙኤል ልዩ ቦታ እንዲኖረው ሳያደርግ አልቀረም። ‘እንደ ወንድም’ ነው የሚመለከተው። አብረው መሥራት ጀመሩ።

ዱባይ የሚሠሩ የስፖርት ልብሶች ላይ ማስታወቂያ ከሠሩ በኋላ ሳሙኤል ቀስ በቀስ ታዋቂ ሆነ።

“ፎቶ ስነሳ ስታይሌን ወደዱት። ብዙ ሰውም ሪአክት አደረገ። የኤሪክ ጓደኞች ሞዴሎችም ነበሩ። ፎቶው ለሞዴል ይሆናል አሉኝ” ይላል ሳሙኤል።

የሞዴሎች ውድድር የሚካሄድበት ገጽ ላይ ፎቶውን አካተቱት።

ሳሙኤል ሞዴል ስለመሆን በህልሙም በእውኑም አስቦ ባያውቅም ‘ጥቁር አሜሪካዊ ሞዴል ትመስላለህ’ ብለው ሌሎቹ ሞዴሎች ሲያሞግሱት ተገረመ።

‘ሊቪንግ ኢን ዱባይ’ በሚል አንድ ዝነኛ መሰናዶ ላይ ከተለቀቀ በኋላ በቲክቶክ እንዲሁም በኢንስታግራም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ተመልካች እንዳገኘ ይናገራል።

“እዚህ አገር ብዙ ዓመት ቆይተው በሞዴሎች ውድድር ለመሳተፍና ዕድሉን ያላገኙ ብዙ ሰዎች አሉ። ሳሚ እንኳን ደስ አለህ፤ ሞዴል ሆነሀል። ብዙ ሰዎች ለማስታወቂያ ይፈልጉሃል ሲል ኤሪክ ነገረኝ” ሲል ሳሙኤል ለቢቢሲ ተናግሯል።

የሞዴል አካዳሚዎች እና ሌሎችም ተቋማት አብረውት ለመሥራት ጥያቄ እንዳቀረቡለትም ይናገራል። የኢትዮጵያ የሪል ስቴት ተቋማትም ከእዚህ ውስጥ ይገኙበታል።

አሁን ሳሙኤል በድንገት ባየው ላምቦርጊኒ መኪና ምክንያት ባልጠበቀው መንገድ ሞዴል ለመሆን መንደርደር ጀምሯል።

ከግንባታ ተቋሙ ወጥቶ ወደ ሞዴልነት ሙሉ በሙሉ ለመግባት እየተዘጋጀ እንደሆነ ይናገራል።

“እግዚአብሔርን አመልከዋለሁ፤ እንደሚረዳኝም አምናለሁ፤ ከልቤ” ይላል ደጋግሞ ፈጣሪውን ስላደረገለት ነገር ያመሠግናል።