ዶክተሩን የሚያሳይ የካርቱን ምስል

ከ 5 ሰአት በፊት

ፈረንሳይ በመቶዎች የሚቆጠሩ በአብዛኛው ማደንዛዣ የተሰጣቸው ህጻናት ታማሚዎቹ ላይ ለ25 ዓመታት ያህል ወሲባዊ ጥቃት ፈጽሟል ያለችውን የቀዶ ጥገና ሐኪም ፍርድ ቤት ልታቀርብ ነው።

ጆኤል ለ ስኳዋርኔክ የተባለው ይህ ዶክተር 299 የሚሆኑ ታማሚ ህጻናቱን በመድፈር ወይም ጥቃት በማድረስ ነው በቅርቡ ክስ የሚመሰረትበት።

የ73 ዓመቱ ቀዶ ጥገና ኃኪም እነዚህን ጥቃቶች የፈጸመው በአውሮፓውያኑ 1989 እስከ 2014 ባለው ጊዜ ነው።

በፈረንሳይ ታሪክ ውስጥ በርካታ ህጻናቶች ላይ ጥቃት አድርሷል የተባለው ይህ ዶክተር የፍርድ ሂደት በቅርቡ ይጀመራል።

ግለሰቡ የቀረቡበትን ሁሉንም ክሶች ባያምንም የተወሰኑትን አምኗል።

በሰሜናዊ ምዕራብ ፈረንሳይ ቫኔስ የሚጀመረው የፍርድ ሂደት ለበርካታ ዓመታት የፈጀውን አድካሚ የፖሊስ ምርመራ ተከትሎ ነው።

ዶክተሩ በእነዚህ ህጻናት ላይ ለ25 ዓመታት ጥቃት በሚፈጽመበት ወቅት የስራ ባልደረቦቹም ሆነ የቀጠረው የሆስፒታሉ አስተዳደሮች ከለላ አድርገውለት ነበር ወይ የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም ተብሏል።

ለዚህም መነሻ የሆነው የአሜሪካው የፌደራል ምርመራ ቢሮ ዶክተሩ ህጻናት ወሲባዊ ጥቃት ሲደርስባቸው የሚያሳዩ ድረገጾችን እንደሚጎበኝ ለፈረንሳይ ባለስልጣናት አስጠንቅቀው የነበረ ቢሆንም ግለሰቡ ክስ አልተመሰረተበትም ነበር።

ዶክተሩ ህጻናትን እንዳያክም ወይም እንዳያገኛቸው በርካታ እድሎች እንዳመለጡ ወይም ችላ እንደተባሉ አሳይ መረጃዎች አሉ ተብሏል።

የዶክተሩ የገዛ ቤተሰቡ አባላት በህጻናት ላይ ያለውን ወሲባዊ ዝንባሌ እንዲሁም ጥቃቶችን እንደሚፈጽም ቢያውቁም ማስቆም እንደተሳናቸው ተገልጿል።

“ቤተሰቡ የሚፈጽማቸውን ጥቃቶች በመሸፋፈናቸው ለሁለት አስርት ዓመታት ወሲባዊ ጥቃቶችን እንዲፈጽም በር ከፍቶለታል” ሲሉ በጉዳዩ ላይ የተሳተፉ አንድ የህግ ባለሙያ ተናግረዋል።

በአንዲት ትንሽ ከተማ ታዋቂ እንዲሁም ከፍተኛ ክብር የነበረው ይህ የቀዶ ጥገና ሐኪም ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛል።

ዶክተሩ በቁጥጥር ስር የዋለው በአሁኑ ወቅት በ30ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ የእህቱን ልጆች እንዲሁም በወቅቱ የስድስት ዓመት ህጻን የነበረች ታማሚን በመድፈር ተጠርጥሮ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2020 የ15 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

ዶክተሩ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ፖሊስ ባደረገው ፍተሻ በህጻናት አምሳያ የተሰሩ የወሲብ አሻንጉሊቶች እንዲሁም ከ300 ሺህ በላይ ህጻናት ወሲባዊ ጥቃቶች ሲፈጸምባቸው የሚያሳዩ ምስሎች አግኝቷል።

በተጨማሪም ዶክተሩ ለ25 ዓመታት በህጻናት ታማሚዎቹ ላይ የፈጸማቸውን ወሲባዊ ጥቃቶች በዝርዝር የሚያስረዱ እና በጥንቃቄ የተጠናቀሩ ማስታወሻ ደብተሮች ተገኝተዋል።

ህጻናቱን አልደፈርኩም ወይም ጥቃቶች አልፈጸምኩም ያለው ዶክተሩ ማስታወሻዎቹ በምናብ ያሰባቸውን የሚያስረዱ ናቸው ሲል ክዷል። ግለሰቡ ከ100 በላይ የመድፈር እንዲሁም ከ150 በላይ ወሲባዊ ጥቃቶችን በመፈጸም ክሶች ቀርበውበታል።

በአሁኑ ወቅት በአዋቂነት ዕድሜ ላይ ያሉት የቀድሞ ታካሚዎቹ ህጻናት አንዳንድ ጊዜ ወላጆቻቸው ወይም ሌሎች ዶክተሮች ባሉበት ወቅት እንኳን ምርመራ ለማድረግ ነው ቢልም ያለ አግባብ ይነካካቸው እንደነበር ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ነገር ግን ጥቃቶቹ በሚፈጸሙበት ወቅት በርካቶቹ በማደንዛዣ ስር ስለነበሩ ምን እንደደረሰባቸው እንደማያስታውሱ ተገልጿል። ፖሊስ የዶክተሩን የማስታወሻ ደብተሮች እያጣቀሰ የተፈጸመባቸውን ወሲባዊ ጥቀቶች በነገራቸውም ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ድንጋጤ ውስጥ እንደገቡ ተነግሯል።