
ከ 5 ሰአት በፊት
የበረዶ ኳስ ጨዋታ (ሆኪ) መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ካናዳዊያን የአሜሪካን ብሔራዊ መዝሙር እንዳይዘመር አወኩ።
ካናዳዊያኑ ደጋፊዎች ይህን ያደረጉት የዶናልድ ትራምፕን የታሪፍ ጭማሪ በመቃወም ነው።
በካናዳ ዋና ከተማ ኦቶዋ እየተካሄደ በነበረው የብሔራዊ ሆኪ ሊግ የአሜሪካ ቡድን ተጋጣሚ ሆኖ ቀርቦ ነበር። በዚህ ወቅት ነው ብሔራዊ መዝሙር በተቃውሞ የታወከው።
ትናንት እሑድ በነበረ ሌላ የብሔራዊ ቅርጫት ኳስ ማኅበር ግጥሚያ ወቅት የቶሮንቶ ራፕሮረስ እና የሎስ አንጀለስ ክሊፐርስ ቡድኖች ሊጋጠሙ ሲል በነበረው የብሔራዊ መዝሙር ሥነ ሥርዓት ካናዳዊያን በተመሳሳይ ተቃውሟቸውን ገልጠዋል።
ብሔራዊ መዝሙሩን ስታቀርብ የነበረችው የ15 ዓመቷ አዳጊ ድምጽ በተቃውሞ ድምጽና ጉርምርምታ ታውጦ ነበር።
ወትሮ ጥብቅ ወዳጅ በሆኑት ካናዳዊያንና አሜሪካዊያን ዘንድ እንዲህ ያለ ተግባር የሚታሰብ አልነበረም።
ተንታኞች ይህ የሚያሳየው ካናዳዊያን በትራምፕ የታሪፍ ጭማሪ ምንኛ እንደተቆጡ ነው እያሉ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በካናዳ ምርቶች ላይ የ25 % ጭማሪ ማድረጋቸው የንግድ ጦርነት እንዳይፈጥር ተሰግቷል።
ከነገ ማክሰኞ ጀምሮ ከካናዳ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ማናቸውም ሸቀጦች የ25 % ታሪፍ የሚታከልባቸው ሲሆን በነዳጅ ላይ ደግሞ የ10% ታሪፍ ይደመራል።
ይህ የካናዳን ወጪ ንግድ ክፉኛ እንደሚያመሰቃቅል ይጠበቃል።
ትራምፕ ካናዳ ከዚህ አላስፈላጊ ታሪፍ ለመገላገል ከፈለገች የአሜሪካ 51ኛ ግዛት እንድትሆን ጋብዘዋል። ይህ ሐሳባቸው ቀደም ሲል እንደ ዋዛና ንግግር ማዋዣ ተደርጎ ሲወሰድ ቢቆይም አሁን አሁን የትራምፕ ንግግር ቧልት እንዳልሆነ እየታየ ነው።
የንግድ ዘርፍ ተንታኞች እንደሚሉት ካናዳ በምላሹ የምትጥለው ታሪፍ የአሜሪካዊያን ተጠቃሚዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ቢያስከትልም፣ በጠቅላላው የንግድ ጦርነቱ ክፉኛ የምትጎዳው ግን ካናዳ ትሆናለች።
ይህ ታሪፍ ለወራት ከዘለቀ የካናዳ ምጣኔ ሃብት ጨርሶ ሊሟሽሽ ይችላል ይላሉ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ የዘርፉ አዋቂዎች።
- ትራምፕ በሶማሊያ የኢስላሚክ ስቴት ታጣቂዎች ላይ የአየር ደብደባ መፈፀማቸውን አሳወቁ2 የካቲት 2025
- ካናዳ አሜሪካ ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ እንደምትጥል የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር አስታወቁ2 የካቲት 2025
- ዓለም አቀፉን የእርዳታ ሰንሰለት በቀናት ውስጥ ቀጥ ያደረገው የአሜሪካ ውሳኔከ 6 ሰአት በፊት
ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ለሕዝባቸው ባደረጉት ስሜት የተሞላበት ንግግር “በዚህ ውሳኔ ብዙ ሰው ይጎዳል-አውቃለሁ። ሆኖም ካናዳዊያን አንዳችን ለሌሎቻችን የምንቆምበት ጊዜ አሁን ነው” ሲሉ ሕዝቡ እንዲደጋገፍ ተማጽነዋል።
የቱሩዶን ስሜታዊ ንግግር ተከትሎ ካናዳዊያን በማኅበራዊ ሚዲያ የአሜሪካንን ምርቶች ላለመግዛት ከፍተኛ ዘመቻ ከፍተዋል።
ሌሎች ካናዳዊያን ደግሞ ወደ አሜሪካ የሚያደርጉትን የሽርሽር ጉዞ መሰረዛቸውን በስፋት እየጻፉ ነው።
ካናዳ በድምሩ የ105 ቢሊየን ዶላር ምርቶች ላይ ታሪፍ ጥላለች።
አሜሪካ ከየትኛውም አገር ከምትገዛው ነዳጅ የበለጠ ከካናዳ የምትገዛው ይበልጣል።
ቀጣይ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱት የወግ አጥባቂው ፓርቲ መሪ ፒር ፖሊየቭ የትራምፕ እርምጃ “ፍርደ ገምድልና ኢ- ፍትሐዊ” ሲሉ ተችተውታል።
ትራምፕ ይህን እርምጃ ለ6 ወራት ካጸኑት በካናዳ ከፍተኛው የምጣኔ ሃብት ቀውስ ሊፈጠርና የሥራ አጥ ቁጥር ወደ 7በመቶ ሊያድግ እንደሚችል ተፈርቷል።
ይሁንና አሜሪካ በካናዳ ላይ ይህን ድንገተኛ ውሳኔ የወሰነችው ካናዳ ወደ ድርድር እንድትመጣ ለማስገደድ ሳይሆን እንዳልቀረ ይገምታሉ፤ የፖለቲካ ሳይንስ ተንታኞች።
ትራምፕ አደገኛ እንደሆነ የሚነገርለትና ከህመም ማስታገሻነት አልፎ ሱስ የሚያሲዘው ፌንተነል መድኃኒት በብዛት ከካናዳ ወደ አሜሪካ እንደሚገባ ይናገራሉ።
ትራምፕ ሌላ የሚያነሱት ሕገ ወጥ ድንበር ማቋረጥን ነው። ፌንተነል እና ሕገ ወጥ ድንበር ማቋረጥን ለማስቀረት የሰሜንና የደቡብ ጎረቤቶቻቸው የሆኑትን ካናዳና ሜክሲኮን በታሪፍ ማስጨነቅን ምርጫቸው አድርገውታል።
ካናዳ በበኩሏ ፌንተነል አደገኛ መድላኒት ከካናዳ ወደ አሜሪካ የሚገባው ተደምሮ ከ1በመቶ እንኳ አይሞላም ትላለች።
የሰዎችን ዝውውርን በተመለከተ የድንበር ጥበቃውን ለማጠናከር ደግሞ 1 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ በጀት እመድባለሁ ብላለች።
ሆኖም ይህ ትራምፕን ብዙም አላረካቸውም።
በተጨማሪም ትራምፕ አሜሪካ በየዋህነት በጎረቤቶቿ እየተበዘበዘች ኖራለች ብለው ያምናሉ።
ጎረቤቶቿ ፍትሐዊ ባልሆነ መልኩ ከአሜሪካ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፤ አሜሪካ ማግኘት ያለባትን ትርፍ እያገኘች አይደለም፤ ሌሎች ግን ተጠቃሚ ሆነዋል ይላሉ።
ትራምፕ ትናንት እሑድ ‘ትሩዝ ሶሻል’ ላይ እንዲህ ጽፈዋል፣ “አሜሪካ የካናዳ ምርቶችን አትፈልግም፤ አሜሪካ ካናዳን ለመደጎም ቢሊዮን ዶላር ታፈሳለች። ይህን ድጋፍ ብናቆም አሜሪካ እንደ አገር መቆም አትችልም።”