የጂቡቲ ካርታ
የምስሉ መግለጫ,ጥቃቱ የተፈጸመው ኤሌዳአር ወረዳ ሲያሮ ቀበሌ

ከ 4 ሰአት በፊት

በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የጂቡቲ መንግሥት ሰነዘረው በተባለው የድሮን ጥቃት ቢያንስ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ጥቃቱ የተፈጸመው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ምሽት ሲሆን፣ በጥቃቱ አንድ ሕጻን መገደሉንም ነዋሪዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው በዞን- አንድ፣ ኤሌዳአር ወረዳ ሲያሮ ቀበሌ እንደሆነ እና ከተገደሉት ሰላማዊ ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች 6 ሰዎች ክፉኛ ቆስለው ዱብቲ ሆስፒታል መግባታቸውን አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የጂቡቲ መንግሥት በበኩሉ ጥቃቱን የፈጸመው በራሱ ግዛት ውስጥ መሆኑን እና፣ ዒላማውያም አሸባሪዎች ባላቸው ላይ እንደሆነ አመልክቷል።

የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤፍ ኤፍ ፒ የጂቡቲን መከላከያ ሚኒስቴር ጠቅሶ እንደዘገበው ጥቃቱ ከድንበር 6 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አዶርታ በተባለ አካባቢ ”በአሸባሪ ቡድን” ላይ የተፈጸመ ነው።

የጂቡቲ መከላከያ ሚኒስቴር አካሄድኩት ባለው በዚህ የድሮን ጥቃት ስምንት አሸባሪዎች ገድያለሁ ብሏል። ይህ ጥቃት ሲፈጸም በጂቡቲ ንጹሐን ዜጎች ላይ አላስፈላጊ ጉዳት መድረሱን አምኖ፣ ነገር ግን ጉዳቱ ምን እንደሆነ በዝርዝር አልገለጸም።

ሆኖም ምርመራ አካሄዳለሁ ማለቱን የዜና ወኪሉ ዘግቧል።

በኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል ስለ ሁኔታው የተጠየቁት የጂቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡማር ጊሌ አማካሪ አሌክሲስ መሐመድ ታጣቂዎቹ “በምህጻሩ ኤፍ አር ዩ ዲ ኤ” የሚባለው ተቃዋሚ ቡድን አባላት ናቸው ብለዋል።

ጂቡቲ ይህን ቡድን በአሸባሪነት ፈርጀዋለች።

ጥቃቱን በተመለከተ ለቢቢሲ የተናገሩ የአፋር ክልል ነዋሪ የድሮን ጥቃቱ ባለፈው ሐሙስ እና ዐርብ መፈጸሙን አብራርተዋል።

“መጀመሪያ ሐሙስ ሌሊት ሦስት ሰው ገደሉ፤ ቀጥሎ ሟቾቹን ሊቀብሩ ዐርብ ጠዋት የተሰባሰቡ ሰዎች ላይ ጥቃት ሰነዘሩ፤ አምስት ሰዎች ሞቱ” ብለዋል።

እኚሁ ምንጭ ሌሎች የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ስድስት ሰዎች ዱብቲ ሆስፒታል ተወስደዋል ህክምና ላይ መሆናቸወቅንም አመልክተዋል።

“ከሟቾቹ መካከል አንዲት ሴት፣ አንድ ሕጻን እና ስድስት ወንዶች ይገኙበታል። ዱብቲ ሆስፒታል ከገቡት ውስጥ ደግሞ አራቱ ሴቶች፣ ሁለቱ ሕጻናት ናቸው” ብለዋል።

ጥቃቱ በጂቡቲ መንግሥት ስለመፈጸሙ ምን ማረጋገጫ አላችሁ? ተብለው የተጠየቁት እኚህ ግለሰብ “አንደኛ የራሳችን መንግሥት በራሱ ዜጎች ላይ ጥቃት ይፈጽማል ብለን አናምንም። ሁለተኛ የጂቡቲ መንግሥት ‘ፍሩድ’ የሚባል የጂቡቲ አፋሮች ቡድን ይኖራሉ ብሎ ስላሰበ የፈጸመው እንደሆነ ሰምተናል” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2022 ይህ ቡድን በጋራብቲሳን የጂቡቲ የወታደር ቀጠና ድንገተኛ ጥቃት ከፍቶ ሰባት የጂቡቲ ወታደሮችን ገድሎ ሌሎች ሰባቶችን አግቶ መውሰዱን የጂቡቲ ባለሥልጣናት ይናገራሉ።

ሰባቱ የታገቱት ወታደሮች ከሳምንታት በኋላ ተለቀዋል።

ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት የኢትዮጵያ መንግሥት እስከአሁን ያለው ነገር የለም።