
ከ 6 ሰአት በፊት
ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ልገሳ በሚታገዘው ሰሜናዊ ሶሪያ የሚገኘው አልሆል የስደተኞች መጠለያ ካምፕ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች “ሥራ አቁሙ” የሚል ትዕዛዝ ተላለፈላቸው።
በጦርነት የተፈናቀሉ በአብዛኛው ሴቶች እና ህጻናት በሚገኙበት እና 40 ሺህ ተፈናቃዮችን በያዘው የስደተኞች መጠለያ ላሉ ሠራተኞች ትዕዛዙ አስደንጋጭ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ በግዙፉ መጠለያ ጣቢያ የውሃ፣ የንጽህና አጠባባቅ እንዲሁም የጥበቃ ሥራዎች መስተጓጎላቸውን ከፍተኛ የረድዔት ሠራተኛ ተናግረዋል።
በሶሪያ ሰሜናዊ ምሥራቅ የሚገኘው አልሮጅ የተሰኘው ሌላው ማዕከል በዚህ ድንገተኛ ትዕዛዝ ሥራ ካቆሙት መካከል አንዱ ነው። የአይኤስ (ኢስላሚክ ስቴት) ተጠርጣሪዎች በሁለቱ ማዕከላት አቅራቢያ ተይዘው ይገኛሉ።
ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን በተመለሱባት በመጀመሪያዋ ዕለት አገራቸው ለውጭ አገራት የምትሰጠው እርዳታ “አሜሪካ መጀመሪያ” ከሚለው ፖሊሲያቸው ጋር ይጣጣም እንደሆነ መገምገም አለበት በሚል እንዲቆም አዘዋል።
የዓለማችን ቀዳሚ ዕርዳታ ለጋሽ የሆነችው አሜሪካን እየመሩ ያሉት ትራምፕ ያስተላለፉትን ትዕዛዝ አንድምታ ለመረዳት የእርዳታ ባለሥልጣናት እና ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ቀናትን መጠበቅ ነበረባቸው።
ሆኖም ባለፈው ሳምንት የወጣ የአሜሪካ መንግሥት የውስጥ ማስታወሻ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ የውጭ እርዳታዎች ለ90 ቀናት እንዲቆሙ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ይፋ አድርጓል።
ይህ ትዕዛዝ ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ እንዲሁም ለእስራኤል እና ለግብፅ ከሚሰጠው ወታደራዊ ድጋፍ በስተቀር ሁሉም የውጭ ልገሳዎች እንዲቆሙ ያዛል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ የውጭ ፖሊሲያቸው ውጤታማነት እና ወጥነት እስኪገመገም ድረስ የውጭ የልማት ድጋፍ እንዲቆም ያሳለፉትን የሥራ አስፈጻሚ ትዕዛዝን የተከተለ ነው።
በተለያዩ አገራት በአሜሪካ እርዳታ የሚንቀሳቀሱ ፕሮጀክቶች ሥራቸውን እንዲያቆሙ ማስታወቂያዎች ይደርሱ ጀመር። የውሃ፣ ንጽህና፣ ክትባት፣ ጤና ፕሮጀክቶች በጊዜያዊነት ቀጥ አሉ።
የዓለማችን ትልቁ የረድዔት ድርጅት ብራክ (BRAC) በአራት አገራት ባቋረጣቸው ፕሮግራሞች ምክንያት 3.5 ሚሊዮን ሰዎች እንደሚጎዱ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ይህ የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ “በረድዔቱ አቅርቦቱ ዘርፍ እንደ ርዕደ መሬት ነው የተሰማን። የሕይወት አድን ፕሮግራሞች ምስቅልቅላቸው ወጥቷል” ሲሉ አንድ አንጋፋ ዓለም አቀፍ የረድኤት ሠራተኛ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የውጭ እርዳታ እንዲቆም ድጋፋቸውን እየሰጡ ያሉ አካላት አሜሪካ 70 ቢሊዮን ዶላር በማውጣት ከምዕራባውያኑ አገራት በበለጠ ከባድ ሸክም ተጭኖባታል ይላሉ።
የአሜሪካ መንግሥት በውጭ አገራት ከፍተኛ ወጪ እያወጣ ነው ብለው የሚከራከሩ አካላት ይህ ገንዘብ አገር ውስጥ ሊውል ይገባው ነበር ይላሉ።
አስተዳደሩ በአሜሪካም ቢሆን ጽንስ ማቋረጥን፣ የቤተሰብ ምጣኔን እንዲሁም ብዝኃነትን ማስፋት የሚሉ ፕሮግራሞችን እንደሚቃወሙ ግልጽ አድርጓል። ከዚህም ጋር በተያያዘ የውጭ እርዳታን ማገድም ወጪዎች ያለ አግባብ የሚወጡበትን ለመቅረፍ ዋነኛ ተግባር ነው ይላል አስተዳደሩ።
“እያንዳንዷ የምናወጣት ዶላር፣ የምንደግፋቸው ፕሮግሞች፣ የምንከተላቸው ፖሊሶች በምክንያት ሊሆኑ ይገባል” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩቢዮ ተናግረዋል።
እነዚህ ልገሳዎችን “አሜሪካን ደኅንነቷ የተጠበቀ ያደርገዋል? ጠንካራ ያደርጋታል? ወይስ ያበለጽጋታል?” ሲሉ ሩቢዮ ይጠይቃሉ።
- ከቢቢሲ አማርኛ ዜና እና ታሪኮች በቀጥታ እንዲላክልዎ የዋትስአፕ ቻናላችን አባል ይሁኑ5 ታህሳስ 2024
- የአሜሪካ እርዳታ መቋረጥ በኢትዮጵያ በሚካሄዱ የጤና እና የሰብዓዊ እርዳታ ሥራዎች ላይ ምን ያስከትላል?31 ጥር 2025
- የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ዕርዳታ እንዲቆም መወሰኑን ሾልኮ የወጣ ማስታወሻ አሳየ25 ጥር 2025

በዚህ የእርዳታ መታገድ ምክንያት የተቋረጡ ፕሮግራሞች መጠነ ሰፊ ናቸው። ከአሜሪካ የገንዘብ ልገሳ ጋር በተሳሰረው የዓለም የረድዔት ሥርዓት ውስጥ ሰፊ ድንጋጤ እና ትችትን አስነስቷል።
ተጨማሪ የገንዘብ ልገሳ እንዳያጡ የፈሩ የረድዔት ሠራተኞች ስጋቶቻቸውን በይፋ ከመናገር ቢቆጠቡም አንዳንዶች ይህንን ለመተቸት ወደ ኋላ አላሉም።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የኤችአይቪ ሥርጭትን ለመከላከል የሚሠራው የአሜሪካው ተቋም ፔፕፋር ሠራተኞች ወደ ሥራ ኮምፒውተሮቻቸው አካውንት መግባት እንደታገዱ በአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የቀድሞ የዓለም ጤና ድርጅት ረዳት አስተዳዳሪ ዶ/ር አቱል ጋዋንዴ ተናግረዋል።
የያኔው ፕሬዚዳንት ቡሽ ነበሩ በአውሮፓውያኑ 2003 የፕሬዚዳንቱን የአደጋ ጊዜ የኤድስ ድጋፍ ዕቅድ (ፔፕፋርን) ይፋ ያደረጉት።
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ዶክተሮች እና ነርሶችን ጨምሮ ከ250 ሺህ በላይ ሠራተኞቸን በ55 አገራት ቀጥሮ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቶችን እንዲሁም ወሳኝ በሽታውን የመከላከል ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።
ፔፕፋር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት በመታደግ እንዲሁም የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭትን በመግታት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
“ፕሮግራሙ ተቋርጧል፣ አገልግሎቶች ቆመዋል” ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት ዶክተር ጋዋንዱ በዓለማችን በኤችአይቪ ለተያዙ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች አገልግሎት የሚሰጡ ክሊኒኮች ከፍተኛ ተጽእኖ ደርሶበቸዋል ብለዋል።
በሶሪያዎቹ አልሆል እና አልሮጅ የመጠለያ ጣቢያዎች የውጭ አገራትን ዜጎችን ወደ አገራቸው በመመለስ በአውሮፓ የሰላም ተቋም የሚሠሩት ፖል ጆርዳን በዋሽንግተን የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት አብዛኛው ፕሮግራማቸው ወዲያውኑ ቆሟል ብለዋል።
ለሦስት ወራት ግምገማው እስኪካሄድ ድረስ የመጠለያ ጣቢያዎቹ አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገቡ እንደተደረጉ ለዩናይትድ ኪንግደም የፓርላማ ኮሚቴ ባደረጉት ገለጻ አስረድተዋል።
ባለፉት ቀናት ምግብ እና ሌሎች መሠረታዊ ፍጆታዎች ወደ መጠለያ ካምፖቹ መግባት አቁመዋል ብለዋል። ማክሰኞ፣ ጥር 20/2017 ዓ.ም. በርካታ የረድዔት ድርጅቶች የአሜሪካ መንግሥት የሚሰጣቸውን እርዳታ እንዳያቆም ከፍተኛ ጩኸት ማሰማታቸውን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይህ ዕግድ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ለመገደብ አንዳንድ ሙከራዎችን ማድረግ ጀምሯል።
በዚህ ዕግድ ያልተካተተው ሕይወት አድን ሰብዓዊ እርዳታ ከአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ባለፈ ሕይወት አድን መድኃኒቶችን፣ የህክምና አገልግሎቶችን፣ ምግብ፣ መጠለያ እና ሌሎች መሠረታዊ አቅርቦቶችን እንዲያካትት ተደርጓል።
ይህ እንደገና የተሻሻለው መመሪያ የፔፕፋር አንዳንድ ፕሮግራሞች እንደገና እንዲጀምሩ ቢያግዝም የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቶች ሥርጭት በዚህ ሽፋን ስለመካከታቸው ግልጽ አይደለም።
በባይደን አስተዳደር በዩኤስኤይድ በከፍተኛ ኃላፊነት የተሾሙት ዶ/ር ጋዋንዱ በምዕራብ አፍሪካ የኤምፖክስ (የዝንጀሮ ፈንጣጣ) ወረርሽኝ፣ የፌንታንይል አደንዛዥ ዕጽ ሥርጭትን መግታት ጨምሮ ሌሎች በአሜሪካ እርዳታ የሚደገፉ ፕሮግራሞች ዕጣ ፈንታቸው አልታወቀም ብለዋል።
እነዚህን ፕሮግራሞች አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበለት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ቃል አቀባይ “የቀረቡልንን ጥያቄዎች በሙሉ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እየገመገምን ነው። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ የአገሪቱን ጥቅም የማስጠበቅ ዋነኛ ኃላፊነት አለበት” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በሶሪያዎቹ አልሆል እና አልሮጅ መጠለያ ጣቢያዎች የዕርዳታ ሥራን የሚያስተባብረው የአሜሪካው ተቋራጭ ብሉሞንት ሰኞ ምሽት ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ “ወሳኝ ተግባራትን” ለሁለት ተጨማሪ ሳምንታት እንዲሠራ ትዕዛዝ እንደመጣለት አስታውቋል።
ቢቢሲ የሶሪያ መጠለያ ጣቢያዎችን አስመልክቶ ለውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በጠየቀበት ወቅት “ወሳኝ ሥራዎች” እንዲቀጥሉ የብሔራዊ ደኅንነቱ ፈቃድ ቢሰጥም ይህ ሶሪያን ስለማካተቱ ያለው ነገር የለም።
ይህ መሥሪያ ቤቱ ያወጣው ፈቃድ “ጽንስ ማቋረጥ፣ የቤተሰብ ምጣኔ ጉባኤዎችን፣ አስተዳደራዊ ወጪዎችም፣ የርዕዮተ ዓለም ፕሮግራሞችን፣ ፆታ የመቀየር ቀዶ ህክምናዎችን ወይም ከሥርዓተ ጾታ ጋር በተገናኘ አካታችነትን” አይመለከትም ብሏል።
ዋሽንግተን ውስጥም የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ዋና መሥሪያ ቤት በእርዳታ እገዳው እንደተረበሸ ነው።
ሠራተኞቹ ከመመሪያው ውልፍት እንዳይሉ እንዲሁም ስለ ዕገዳው ከመሥሪያ ቤት ውጪ እንዳይናገሩ ጥብቅ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።
እነዚህን መመሪያዎች መጣስ “የዲሲፒሊን ቅጣት” እንደሚያስከትልም የውስጥ ማስታወሻው በጥብቅ ማስጠንቀቁን አሳይቷል።
ስማቸው ያልተጠቀሱ ሠራተኞች የፕሬዚዳንቱን የሥራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ለመቀልበስ ሞክረዋል በሚል የተከሰሱ ሲሆን፣ በርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሥራቸው ፈቃድ እንዲወስዱ ተደርገዋል።
በኤጀንሲው አዳራሾች በአንድ ወቅት በተለያዩ አገራት የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን ያሳዩ የነበሩ የተሰቀሉ ምሥሎችም አሁን ባዶ ሆነዋል።

በዓለም ረድኤት ድርጅቶች ዘንድ ከፍተኛ ወቀሳ እና ትችት መጠናከሩን ተከትሎ ረቡዕ፣ ጥር 21/2017 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለ90 ቀናት ግምገማ እንዲደረግ በሚል የውጭ እርዳታ እንዲቆም የተላለፈው ውሳኔ “ለአሜሪካ እና ለሕዝቦቿ ትርፍ እያመጣ ነው” ብሏል።
“ብክነትን ከስር መሠረቱ እየተከላከልን ነው። የማይሆኑ ፕሮግራሞችን እየከለከልን ነው። ከአገራዊ ጥቅማችን ጋር የሚጻረሩ ተግባራትን እያጋለጥን ነው። እነዚህ ፕሮግራሞች በዚያው እንዲቀጥሉ ቢደረጉ ኖሮ ይህንን ማከናወን አይቻልም” ብሏል።
የተወሰኑ ፕሮግራሞችን ከማጠፍ ይልቅ ሁሉም የውጭ እርዳታዎችን በጊዜያዊነት እንዲቆም ለምን አስፈለገ ለሚለው ውሳኔም መሥሪያ ቤቱ በሰጠው አስተያየት “በሥራ ላይ ያሉ ፕሮግራሞችን መገምገም አይቻልም ምክንያቱም በመንግሥትም ሆነ ከመንግሥት ውጪ ያሉ አካላት ዶላር መፍሰሱን እስከ ቀጠለ ድረስ የፕሮግራሞቻቸውን ዝርዝር መረጃዎች ለማጋራት አይፈልጉም” ብሏል።
አክሎም “የሕይወት አድን ፕሮግራሞች ከሆኑት ውጪ ያሉ ፕሮግራሞችን በጊዜያዊነት ቆም በማለት መመርመር ብክነትን ለመከላከል ብቸኛው መንገድ ነው” ብሏል።