
ከ 7 ሰአት በፊት
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጉ የአማፂዎች ትብብር ቡድን ከዛሬ ማክሰኞ፣ጥር 27/2017 ዓ.ም የሚጀምር የሰብዓዊ የተኩስ አቁም አውጇል።
በሩዋንዳ እንደሚደገፍ የሚነገረውን ኤም-23 አማፂ ያቀፈው ቡድኑ በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ግዛቶችን መቆጣጠሩን ተከትሎ የተኩስ አቁም ለሰብዓዊነት ሲል ማወጁን ገልፆል።
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ትልቅ ግዛት በሆነው ጎማ በቅርቡ የተቀሰቀሰው ግጭትን ተከትሎ ቢያንስ 900 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን እና 2,880 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል።
የቡድን ሰባት እና የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ጥቃቱን በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ አላስፈጊ ጥሰት በማለት አውግዘውታል።
‘የኮንጎ ወንዝ ትብብር’ በሚል የሚጠራው የአማፂ ቡድኖች ሕብረት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የኮንጎ መንግሥት የአየር ጥቃቶችን በመፈፀም ሰዎችን እየገደለ ነው ሲልም በመግለጫው ከሷል።
ቡድኑ ምንም እንኳ ባለፈው ሳምንት ሌሎች ግዛቶችን ለመቆጣጠር እንደሚገሰግስ ቢናገርም የያዘው ግዛት ላይ በመፅናት ተጨማሪ አካባቢዎችን እንደማይቆጣጠር በመግለጫው አክሎ ገልጿል።
“ንፁሃንን እና የያዝነውን ስፍራ ለመጠበቅ እና ለመከላከል ቁርጠንነታቸውን ደግመን እንገልፃለን” ሲል ቡድኑ ተናግሯል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በቀጠናው ግጭት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ኤጄንሲ አዲሱ የጎርጎሮሳዊያን 2025 ከገባ ወዲህ ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ አስታውቋል።
- የሕክምና ማኅበረሰቡን ያስደነገጠው የዶ/ር አንዱዓለም ዳኜ ግድያከ 8 ሰአት በፊት
- የብልፅግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ የትኞቹን የሥራ አስፈጻሚ አባላት በአዲስ ተካ?3 የካቲት 2025
- በቀውስ ውስጥ የምትገኘው የዲሞክራቲክ ኮንጎዋ ቁልፍ ከተማ ጎማ ከከባድ ጦርነት በኋላከ 8 ሰአት በፊት
የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት እና የአገሪቱ ጦር አዛዥ ፖል ካጋሜ የሩዋንዳ ወታደሮች በሪሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንዳሉ አላውቅም ብለዋል።
“የማላውቃቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ነገር ግን በኮንጎ ሩዋንዳን የሚያስጨንቃት ችግር አለ? እና ሩዋንዳ ራሷን ለመጠበቅ ምንም ታደርጋለች? ብለህ መጠየቅ ከፈለግክ መቶ በመቶ ብዬ እመልሳለሁ” ሲሉ ሰኞ ዕለት ለሲኤንኤን ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ሩዋንዳ ከእርምጃዋ እንድትገታ ጫና እንዲደረግ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ፓትሪክ ሙያያ ሩዋንዳ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል።
“ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ሩዋንዳን ለማስቆም ጠንካራ እርምጃ [መወሰድ አለበት]። ምክንያቱም በአፍሪካ እና በቀጣናችን ሰላምን ለማፅናት ከተፈለገ ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
“ማዕቀብ ትንሹ ነው” ሲሉም ሚኒስትሩ አክለዋል።
የሩዋንዳ እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መሪዎች ለቀጣናዊ የሰላም ጉባኡ የፊታችን አርብ በታንዛኒያ እንደሚገናኙ ይጠበቃል።
የሦስት አስርት ዓመታት የግጭት ታሪክ ከጀርባቸው የያዙት አገራቱ ባለፈው ዓመት ካደረጓቸው ንግግሮች በመነሳት አርብ የሚጀምሩት ድርድር ለወራት ሊዘልቅ እንደሚችልም ተነግሯል።