
ከ 7 ሰአት በፊት
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጎረቤቶቻቸቸው ካናዳ እና በሜክሲኮ ላይ ሊጥሉት ያሰቡትን 25 በመቶ ታሪፍ ለ30 ቀናት ለማዘግየት ተስማሙ።
የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ከትራምፕ ጋር በስልክ ባደረጉት ቆይታ ስደትን እንዲሁም ፈንታንይል የተሰኘውን አደገኛ አደንዛዥ ዕጽ ለመግታት የሚያስችል የድንበር ማጠናከር ስራ እንደሚሰሩ ተስማምተዋል።
ቀደም ሲል ትራምፕ ከሜክሲኮ ፕሬዚዳንት ክላውዲያ ሺንባም ጋር ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ፕሬዚዳንቷ አገራቸው ከአሜሪካ በሚያዋስናት ድንበር ላይ ወታደሮች በማሰማራት ለማጠናከር ተስማምተዋል።
በምላሹ አሜሪካ ወደ ሜክሲኮ የሚገባውን የጦር መሳሪያ ፍሰት የምትገድብ ይሆናል።
ነገር ግን የአሜሪካ ታሪፍ በቻይ ምርቶች ላይ ከማክሰኞ፣ ጥር 27/ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።
ትራምፕ ከቻይና አቻቸው ጋር በቅርቡ በስልክ ለመወያየት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
አሜሪካ በሚገቡ የቻይና ምርቶች ላይ የሚጣለው 10 በመቶ ታሪፍ የመጀመሪያው እርምጃ እንደሆነ የተናገሩት ትራምፕ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ “ከፍተኛ ጭማሬ” እንደሚደረግበት አስጠንቅቀዋል።
ትራምፕ የሁለቱን የሰሜን አሜሪካ ጎረቤቶቻቸውን ታሪፍ ያዘገዩት አገራቱ በአሜሪካ ምርቶች ላይ አጸፋዊ ታሪፍ እንደሚጥሉ ምላሽ እየሰጡ ባለበት ወቅት ነው።
ሰኞ ዕለት ሁለት ጊዜ በስልክ ያወሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ እና ትሩዶ ድንበሩን የማስጠበቅ ስምምነት ላይ በመድረሳቸው ይህም ለ30 ቀናት ታሪፉን እንዲያዘገየው ማድረጉን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አስፍረዋል።
ሁለቱም መሪዎች ይህንን እቅድ እንደ ድል አይተውታል።
- ዓለም አቀፉን የእርዳታ ሰንሰለት በቀናት ውስጥ ቀጥ ያደረገው የአሜሪካ ውሳኔ3 የካቲት 2025
- ትራምፕ በመሬት ፖሊሲዋ ምክንያት ለደቡብ አፍሪካ የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያቋርጡ ዛቱ3 የካቲት 2025
- የትራምፕ ታሪፍን ተከትሎ በዓለም አቀፉ ገበያ የእስያ ድርሻ አሽቆለቆለ3 የካቲት 2025
“እንደ ፕሬዚዳንት የሁሉም አሜሪካውያንን ደህንነት ማረጋገጥ የእኔ ኃላፊነት ነው። ይህንንም እያደረግኩ ነው። በዚህ የመጀመሪያ ውጤት በጣም ተደስቻለሁ” ሲሉ በማህበራዊ ሚዲያቸው ትሩዝ ሶሻል ላይ ጽፈዋል።
ትሩዶ በበኩላቸው አገራቸው ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ጠባቂዎች የተካተቱበት የ1.3 ቢሊዮን ዶላር የድንበር እቅድን በተመግበር ላይ ናት ብለዋል። በተጨማሪም ከሄሮይን በ50 እጥፍ ይበልጣል የሚባለውን እና ትራምፕ እንደ ትልቅ ስጋት ያዩትን ፈንታንይል የተሰኘውን አደንዛዥ ዕጽ ፍሰት መግታትን አቅዷል።
አብዛኛው ይህ የካናዳ ድንበር የማስጠበቅ ዕቅድ በታህሳስ ወር ነበር ይፋ የተደረገው። በተጨማሪም ከአሜሪካ የጸጥታ ኃይሎች ጋር ቅንጅት መፍጠርን፣ የመረጃ ልውውጥን ማጠናከር፣ በድንበር ላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖችን) ማሰማራት እና ብላክ ሃውክ ሄሊኮፕተሮችን ለቅኝት ማሰማራት የዕቅዱ አካል ነው።
ሜክሲኮ በበኩሏ ታሪፍ ለ30 ቀናት እንዲዘገይ ለማድረግ 10 ሺህ የብሄራዊ ጥበቃ ወታደሮችን ከአሜሪካ ጋር ወደምትዋሰንበት ድንበር ትልካለች።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሺንባም ከአሜሪካ አቻቸው ጋር ያደረጉትን ውይይት የአገራቱን ሉዓላዊነት በታላቅ አክብሮት ባስገባ መልኩ እንደተካሄደ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው ከሜክሲኮ መሪ ጋር ያደረጉትን ውይይት በመልካም ሁኔታ ተካሂዷል ብለዋል።