በአሜሪካ የተነሳው ተቃውሞ

ከ 5 ሰአት በፊት

የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት የሆነውን ዩኤስ ኤይድ ከውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ጋር ለማዋሐድ መወጠኑን ተከትሎ ሰኞ ዕለት ሠራተኞች ዋሽንግተን ከሚገኘው የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት እንዳይገቡ ተከልክለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዎ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት የተራድኦ ድርጅት ( ዩኤስ ኤይድ) ተጠባባቂ ዳይሬክተር እንደሆኑ ለሪፖርተሮች ተናግረዋል።

የዲሞክራት ሕግ አውጭዎች እርምጃው ድሆችን እና የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ እንዲሁም በዓለም አቀፍ የአሜሪካን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ዝቅ የሚያደርግ ነው በሚል “ሕገ ወጥ፣ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ” ብለውታል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና አማካሪያቸው ባለፀጋው ኤለን መስክ የተቋሙ ጠንካራ ተቺዎች ናቸው።

ሰኞ ዕለት በዋይት ሀውስ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኤጄንሲው “በአክራሪ ግራ ዘመም አብዶች” እየተመራ ነው ያሉ ሲሆን፤ ተቋሙ “ከፍተኛ ማጭበርበር” ሲፈፅም ነበርም ብለዋል። ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ ስም ወይም ዝርዝር መረጃም አልጠቀሱም።

ዩኤስኤድ እ.አ.አ በ1961 በፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ የተመሰረተ እና ከ10 ሺህ በላይ ሠራተኞች ያሉት ተቋም ነው።

68 ቢሊዮን ዶላር ከሆነው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ወጪ ውስጥ የዩኤስኤድ በጀት 40 ቢሊዮን ዶላር ነው።

ተቋሙ በመላው ዓለም መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች፣ ለረድኤት ድርጅቶች እና ቡድኖች ለእርዳታ ቢሊዮኖችን ያከፋፍላል።

“ሙሉ ለሙሉ ተጠሪ ያልሆነ” ሲሉ ተቋሙን የገለፁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዎ አብዛኞቹ የድርጅቱ ስራዎች እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

“የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊስ አካል ይሆናል። ነገር ግን ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር መጣጣም አለበት” ብለዋል።

አዲሱ አስተዳደር እነዚህን ለውጦች እንዴት አድርጎ ለመፈፀም እንዳሰበ ግልፅ አይደለም።

እርምጃው ይፋዊ ያልሆነውን የወጪ ቅነሳ ተቋምን የሚመሩት ኤለን መስክ የትራምፕ አስተዳደር ዩኤስኤድን ለመዝጋቱ ወጥኗል ማለታቸውን ተከትሎ የመጣ ነው።

በሳምንቱ መገባደጃ የተቋሙ ሁለት ከፍተኛ የደኅንነት ባለስልጣናት ያለ ፍላጎታቸው እረፍት እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን፤ የዩኤስኤድ ድረ-ገፅ መዘጋቱም ታውቋል።

ሰኞ ዕለት የተቋሙ ሠራተኞች ስራ እንዳይገቡ የተነገራቸው ሲሆን፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች የስራ ኢሜላቸውን እንዳይጠቀሙ ታግደዋል።

የዩኤስኤድ መስሪያ ቤት መግቢያ ላይ የዲሞክራቲክ ሕግ አውጭ የሆኑት ክሪስ ቫን ሆለን እርምጃው ሕገ ወጥ እና የአገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነት የሚጎዳ ነው ብለዋል።

በሌላ ጎን እርምጃው በኤለን መስክ የንግድ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነው በሚል የሕግ አውጭዎች ተቃውመውታል።

ኤለን መስክ የመንግሥት መዋቅር አካል ያልሆነ ቅልጥፍናን የሚከታተል ተቋምን እየመሩ ሲሆን በፕሬዝዳንት ትራምፕ የመንግሥትን ወጪ ለመቀነስ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል።

የዚህ ተቋም ሕጋዊነቱ እና የመንግሥት ተቋማትን የመዝጋት ስልጣን ግልፅ አይደለም።